1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ሕጋዊ ማዕቀፍ የሚሻው የኢትዮጵያና ኤርትራ የንግድ ግንኙነት 

ረቡዕ፣ መስከረም 9 2011

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ እርቅ ካወረዱ በኋላ በድንበር አካባቢ ያለው የንግድ ልውውጥ መነቃቃት ጀምሯል። አገራቱ አጠቃላይ ሥምምነት ቢፈራረሙም የንግድ ልውውጥ፣ የመገበያያ ገንዘብ አጠቃቀም እና የታሪፍ ጉዳይ ሕጋዊ ማዕቀፍ አልተበጀለትም። ባለሙያዎች ጉዳዩ በፍጥነት ተቋማዊ ሊሆን እንደሚገባ ይወተውታሉ።

https://p.dw.com/p/35BuR
Saudi Arabien Äthiopien und Eritrea schließen Freundschaftsvertrag
ምስል picture-alliance/AP Photo/SPA

ሕጋዊ ማዕቀፍ የሚሻው የኢትዮጵያና ኤርትራ የንግድ ግንኙነት 

ከድንበር ግዛት ይገባኛል ውዝግብ ባሻገር ንግድ፣ ቀረጥ እና የመገበያያ ገንዘብ አጠቃቀም ላይ የተፈጠሩ ልዩነቶች ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ ደም አፋሳሽ ጦርነት ገፊ ምክንያቶች እንደነበሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ። አሁን የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደ ደም አፋሳሽ ጦርነት ከመግባታቸው በፊት ሁለቱን ሐገራት የሚያገናኟቸውን የየብስ መንገዶች በይፋ ከከፈቱ በኋላ የሁለቱ አገሮች ዜጎች የሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ መነቃቃት እያሳየ ነው። 

ጤፍ እና በርበሬ ለመሸመት ወደ ትግራይ ከተሞች የዘለቁ ኤርትራውያን ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ በድንበር አካባቢ ምንም እንከን እንዳልገጠማቸው ለትግራይ ቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል። የኤርትራ ሰሌዳ የለጠፉ ተሽከርካሪዎች በትግራይ ከተሞች ጎዳናዎች ብቅ ማለት የጀመሩ ሲሆን የተለያዩ ሸቀጦች ጭነው ወደ አስመራ የዘለቁ ነጋዴዎች መኖራቸውም በማኅበራዊ ድረ-ገፆች የታዩ ምስሎች ጠቁመዋል። 

Grenze zwischen Äthiopien und Eritrea
ምስል Getty Images/AFP/M. Haileselassie

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በአሁኑ ወቅት ግብይታቸው የሚመራበት የሁለትዮሽ የንግድ ሥምምነት የላቸውም። በአሁኑ ወቅት የሁለቱን አገሮች የንግድ ግንኙነት ሊመራ የሚችለው የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪቃ አገራት የጋራ ገበያ (COMESA) ብቻ መሆኑን በሉክዘምበርግ የማክስ ፕላንክ ማዕከል የጥናት ባለሙያ የሆኑት አቶ ሔኖክ ብርሐኑ ያስረዳሉ። 

በዓለም አቀፉ የሕግ እና ፖሊሲ ጥናት ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሼቲል ትሮንቮል የሁለቱ አገራት ዜጎች መገበያየት መጀመራቸውን ካወደሱ ባለሙያዎች አንዱ ናቸው። ትሮንቮል ለDWበኢ-ሜይል በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በንግድ፣ ታሪፍ እና የመገበያያ ገንዘብ ላይ የገቡበት አለመግባባት ለደም አፋሳሹ ጦርነት መነሻ መሆናቸውን አስታውሰዋል። የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ምኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ የመገበያያ ገንዘቦች (ብር እና ናቅፋ) የምንዛሪ ተመን እኩል እንዲሆን መስማማታቸው ከጦርነቱም በኋላ ለነቀፌታ ዳርጓቸው እንደነበር ጠቅሰው አሁንም ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። ትሮንቮል "መልሶ ችግር እንዳይፈጥር በተቻለ ፍጥነት መደበኛ የንግድ እና የመገበያያ ገንዘብ አጠቃቀም ሥምምነት መፈረም እና ስምምነቱ ይፋ ሊደረግ ይገባል" የሚል አቋም አላቸው። የሥምምነቱ ይዘት የሚወሰነው በሁለቱ ወገኖች መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰሩ ተቋማዊ ሊሆን እንደሚገባ ግን በአፅንዖት አሳስበዋል። አቶ ሔኖክ ብርሐኑም የሁለቱ አገሮች የንግድ ግንኙነት ተቋማዊ ሊሆን እንደሚገባ ይስማማሉ። አሁን በድንበር አካባቢ የተጀመረው የንግድ ልውውጥ በመጠኑ አነስተኛ በመሆኑ ጉዳት ባያስከትልም እየጨመረ ሲሔድ ግን ጥንቃቄ እንደሚያሻው አቶ ሔኖክ ያስረዳሉ።

Treffen Diplomaten Eritrea Äthiopien
ምስል Mekmz

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ እና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መስከረም 6 ቀን 2011 ዓ.ም. አጠቃላይ ሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር የሚያስችል ሥምምነት ተፈራርመዋል። ከቀይ ባሕር ዳርቻ በምትገኘው የጅዳ ከተማ ሥምምነቱ ሲፈረም የሳዑዲ አረቢያው ንጉስ ከነ አልጋ ወራሻቸው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ እና የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋቂ ማኅማት ከመታደማቸው በቀር ከአስመራው "የሰላም እና የወዳጅነት መግለጫ" እምብዛም የተለየ አይደለም። በሁለቱም ሰነዶች የጦርነት ሁኔታ አብቅቶ "የሰላም እና የወዳጅነት አዲስ ዘመን" መብሰሩ ታውጇል። አዲሱ ነገር በጅዳው ስምምነት ሶስተኛ አንቀጽ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የጋራ ልዩ የኤኮኖሚ ዞኖችን ጨምሮ በጥምረት የመዋዕለ-ንዋይ ሥራዎችን ለመከወን መወሰናቸው መግለፃቸው ነው። ሁለቱ አገሮች እርቅ ማውረዳቸውን ተከትሎ በድንበር አካባቢዎች የተጀመረውን የንግድ ልውውጥ የሚያደንቁት ዶክተር ወንዳፈራሁ ሙሉጌታ የመገበያያ ገንዘብ ገንዘቦች ላይ ያለው የምንዛሪ ልዩነት ትኩረት እንደሚያሻው ይናገራሉ። የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ሁለቱ አገሮች የንግድ ልውውጣቸውን ያለ ታሪፍ በአንድ የመገበያያ ገንዘብ በመጠቀም ሊከውኑ ይችላሉ የሚል ጥቆማ ይሰጣሉ።አቶ ሔኖክም ቢሆኑ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የመገበያያ ገንዘብ አጠቃቀማቸው በሕግ የተቃኘ ሊሆን እንደሚገባ ያስጠነቅቃሉ። ብር እና ናቅፋ ከዶላር እና ሌሎች የመገበያያ ገንዘቦች አኳያ ያላቸው የምንዛሪ ተመን ልዩነት ችግር ሊፈጥር እንደሚችል አቶ ሔኖክ ያስረዳሉ።

Äthiopien Rückkehrer am Flughafen Asmara
ምስል Ethiopian Broadcasting Corporation

ትኩረቷን በንግድ፣ የልማት እና የአፍሪቃ ጉዳዮች ላይ አድርጋ በአማካሪነት የምትሰራው ሉዋም ዲራር በበኩሏ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ተግባራዊ የሚያደርጉት የንግድ ሥምምነት ለሕዝብ እና ሲቪክ ማኅበራት ውይይት ክፍት ሊሆን ይገባል የሚል ዕምነት አላት። በጉዳዩ ላይ ያላትን ሐሳብ በኢ-ሜይል ለDW ያስረዳችው ሉዋም ሁለቱ አገሮች ገደብ እና ክልከላ የሌለበት የንግድ ልውውጥ እንዲኖራቸው ትሻለች። አቶ ሔኖክ በበኩላቸው ነፃ የንግድ ቀጠና መመስረት ሁለቱን አገሮች ተጠቃሚ ለማድረግ አንዱ አማራጭ እንደሆነ ይናገራሉ። ይኸም ቢሆን ግን ጥብቅ ድርድር ይጠይቃል። ዶክተር ወንዳፈራሁ ጠቅላይ ምኒስትር አብይ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከፈረሙት ስምምነት በኋላ ቀሪው ሥራ የባለሙያዎች ነው ባይ ናቸው። የሁለቱ አገሮች ባለሙያዎች በአጭር እና ረዥም ጊዜ ሊሰሩ የሚገቡ ሥራዎችን ሕጋዊ ማዕቀፍ በፍጥነት ማዘጋጀት አለባቸው ብለዋል። 
እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ