1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሕገወጥ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ይዞታና የመሬት ወረራ በአዲስ አበባ

ማክሰኞ፣ ጥር 18 2013

በአዲስ አበባ ከተማ ከ21 ሺህ 600 በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እና ከ13 ሺህ 300 ሚሊየን ካሬሜትር በላይ መሬት በሕገወጥ መንገድ ተይዞ መቆየቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዐስታወቀ፡፡

https://p.dw.com/p/3oRTz
Äthiopien Addis Ababa | Politikerin | Adanech Abiebie
ምስል Seyoum Getu/DW

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ሕገወጥ የመሬት ወረራ፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶችንና ሌሎች መንግስት የሚያስተዳድራቸውን የቀበሌ ቤቶችን ከሕግ አግባብ ውጭ ለግለሰቦች ተላልፈው ተገኝተዋል ነው ያሉት። ባለፉት ሁለት ወራት ከፌራል መንግስት ባለድርሻ አካላት እና ከከተማ አስተዳደሩ አስሩም ክፍለ ከተሞች የተውጣጣው ግብረ ኃይል አካሂዷል በተባለው ጥናት በሕገወጥ መንገድ ከታጠሩት ቦታዎች በተጨማሪ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው 332 ህንጻዎች እና ቤቶች ባለቤት አልባ ሆነው መገኘታቸውንም ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በመግለጫቸው የጥናቱን ውጤት ዋቢ አድርገው አመልክተዋል።

የመሬት ወረራ ጥናቱ ከ1997 ዓ.ም. ወዲህ ተጠናክሮ የቀጠለ ነው ያለው ጥናቱ በከተማዋ አስሩም ክፍለ ከተሞች ከሚገኙ 121 ወረዳዎች በ88ቱ ማለትም በ73 በመቶው የመሬት ወረራ መፈጸሙን አትቷል። የመሬት ወረራው ሃገራዊ ለውጡ በ2010 ዓ.ም ከመምጣቱ አስቀድሞም የነበረ ነው ያለው የከተማ አስተዳደሩ ጥናት ከዚያም በኋላ ተገቢው የወረራው መከላከል ባለመደረጉ ችግሩን ተደራራቢ አድርጎታል ብሏል።

Äthiopien Addis Abeba Motorräder aus Stadt verbannt
ምስል DW/Solomon Musche

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥናቱን ባብራሩበት መግለጫቸው እንዳሉት በየካ ባድሜ ተብሎ በሚታወቅ ስፍራ እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለቡ አከባቢ ብቻ ግንባታቸው ያልተጠናቀቁና ባለቤት ነኝ ብሎ የሚቀርብ ያልተገኘባቸው 264 ህንጻዎች አሉ። በሕገወጥ መሬት ወረራው የሪል እስቴት አልሚዎች፣ ግለሰቦች፣ የመንግስት ተጠሪዎች እና የሃይማኖት ተቋማትም ጭምር መሳተፋቸውም በጥናቱ ላይ ተጠቅሷል።

በመሆኑም ባለቤት አልባ ሆነው የተገኙ ቤቶችና ህንጻዎች እንዲሁም በህገወጥ መንገድ የተያዙት በተለያዩ አከባቢዎች የተያዙ መሬት ወደ መሬት ባንክ እንዲመለሱ አስተዳደራዊ ርምጃ እንዲወሰዱ በማድረግ በድርጊቱ የተሳተፉት ደግሞ በህግ እንዲጠየቁ ለፖሊስ እና ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ተላልፏል ሲሉም ወ/ሮ አዳነች አክለዋል፡፡
ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ጋር ተያይዞም በህገወጥ መንገድ ከተያዙት 21 ሺህ 695 ቤቶች 15 ሺህ 891ዱ መረጃ ያልቀረበባቸው፣ 4530 ባዶ፣ 850 ዝግ የሆኑ፣ 424  በህገወጥ መልኩ በግለሰቦች ተይዘው የሚገኙና 51 ሺህ ቤቶች ከእጣ ውጭ የተላለፉ ናቸው ነው የተባለው፡፡ በመሆኑም እነዚህን እና ሌሎች እጣ ያልወጣባቸው ተገንብተው የተጠናቀቁ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በቅርቡ በህጋዊ መንግድ ለቆጠቡ ባለእድሎች በእጣ ይተላለፋልም ብለዋል ምክትል ከንትባዋ።

በመዲናዋ ከሚገኙ የቀበሌ ቤቶችም ከ10 ሺህ በላይ የሚሆነው በህገወጥ መንገድ ነው ያለው ይህው የጥናት ውጤት በተለይም ከ7 ሺህ በላይ የሚሆነው ውል በሌላቸው ሕገወጥ ሰዎች የተያዙ ስለመሆኑም ነው ያመለከተው፡፡ በመዲናዋ ከሚገኙ ከ25 ሺህ ገደማ የቀበሌ የንግድ ቤቶች ውስጥም ከ4 ሺህ በላይ የሚሆኑቱ በህገወጥ መንገድ የተላለፉ ተብለዋል።
ሥዩም ጌቱ 
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ