ሕወሓት ከ20 መኪና ርዳታ ውጪ አልደረሰንም አለ
ማክሰኞ፣ መጋቢት 27 2014ማስታወቂያ
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ወደ ትግራይ ከገቡ 20 ርዳታ የጫኑ መኪኖች በኋላ ሌላ የደረሰ ርዳታ እንደሌለ በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የሚመራው የትግራይ ክልላዊ መንግስት ዐስታወቀ። የትግራይ ሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ዶክተር አትንኩት መዝገቡ፦ በትግራይ አለ ያሉትን ሰብአዊ ቀውስ ለማቃለልና ለወራት የተስተጓጐለውን የርዳታ አቅርቦት ሥራ ለማካካስ በየቀኑ 300 ርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ትግራይ ክልል ሊደርሱ ይጠበቁ ነበር ብለዋል። ከረዥም የውዝግብ ጊዜ በኋላ 20 ሰብአዊ ርዳታ የጫኑ መኪኖች መቐለ የደረሱት ባሳለፍነው ዓርብና ቅዳሜ ነበር። እነዚህን ተከትለው ወደ ትግራይ ይጓዛሉ ተብለው የነበሩ ሌሎች ርዳታ የጫኑ 35 መኪኖች እስካሁን ወደ ክልሉ አለመድረሳቸው ተገልጿል። እንደ የትግራይ ክልላዊ መንግስት መረጃ በትግራይ 6 ሚልዮን ገደማ የሚሆን ሕዝብ የሕይወት አድን ሰብአዊ ርዳታ ይሻል።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ