1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሕወሓት በነበረባቸው አከባቢዎች የታየው ውድመት

ሐሙስ፣ ኅዳር 23 2014

በአፋር ክልል ሕወሓት ተቆጣጥሯቸው በነበሩ አከባቢዎች የእምነት ተቋማትን ጨምሮ በርካታ የማኅበራዊ መገልገያ ተቋማት ላይ 3 ቢሊየን ብር የሚገመት የንብረት ውድመት መድረሱን የክልሉ ባለስልጣናት ገለጹ።

https://p.dw.com/p/43kj9
Afar-Region in Äthiopien
ምስል picture-alliance / africamediaonline

«3 ቢሊየን ብር የሚገመት የንብረት ውድመት ደርሷል»

በአፋር ክልል ሕወሓት ተቆጣጥሯቸው በነበሩ አከባቢዎች የእምነት ተቋማትን ጨምሮ በርካታ የማኅበራዊ መገልገያ ተቋማት ላይ 3 ቢሊየን ብር የሚገመት የንብረት ውድመት መድረሱን የክልሉ ባለስልጣናት ገለጹ። እንደ ባለስልጣናቱ ገለጻ፦ መንግሥትን የሚፋለሙ የሕወሓት ታጣቂዎች ተቆጣጥረዋቸውት በነበሩ የአፋር ክልል ጭፍራ እና አሳጊታ አከባቢዎች የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች እና የእምነት ተቋማት በታጣቂዎቹ ተዘርፈዋል አለያም ያላቸው የመገልገያ ቁሳቁሶች በሙሉ ወድመዋል። መልሶ የማቋቋም ሥራ እንደሚጀመርም ተገልጿል። 

የክልሉ መንግስት ከፌዴራሉ መንግስት ጋር ሆኖ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን በመጠገን የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ወደየቀየያቸው ከመመለሱ አስቀድሞ አሁን ላይ በአማራ ክልል መሽጓል ያሉትን የሕወሓት ኃይሎች ማስወጣት ላይ ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሰሩም ነው የተገለጸው። የሕወሓት ኃይሎች በአሁ ወቅት ከአፋር ክልል ሙሉ በሙሉ መውጣታቸውንም የገለጹት ባለሥልጣናቱ የኔትዎርክ ጥገና በጭፍራ መጀመሩን እና የኤሌክትሪክ ዝርጋታን ደግሞ መልሶ ወደ አገልግሎት ለማምጣት አማጺያኑን ሙሉ በሙሉ ከአማራ ክልልም እስኪወጡ መጠበቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

የመንግስት ኃይሎች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የሕወሓት ኃይሎችን ተፋልመው ማሸነፋቸውና አሁን ላይ ነጻ ማውጣታቸው በተገለጸበት የአፋር ክልል አከባቢዎች ከፍተኛ የሆነ የንብረት ውድመት መከሰቱን ነው የክልሉ ባለስልጣናት የሚገልጹት። የክልሉ መንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ መሃመድ አህመድ በተለይም ለዶይቼ ቬለ እንዳሉት የእምነት ተቋማትን ጨምሮ በርካታ የማህበራዊ መገልገያ ተቋማት የህወኃት ታጣቂዎች ጥቃት ሰለባ ሆነዋል።

የአፋር ክልላዊ መንግስት ወቅታዊ ትኩረት በአማራ ክልል በተለያዩ አከባቢዎች የሚገኘው የሕወሓት ኃይሎችን መክበብ ነው የሚሉት ደግሞ የክልሉ ጸጥታ አስተዳደር ኃላፊ አቶ ቢላይ አህመድ ናቸው።  እንደ የክልሉ አደጋ ስጋት ማስተባበሪያ ቢሮ ሃላፊ አቶ መሃመድ ሁሴን ገለጻ በአሁናዊው በክልሉ የተካሄደውን ጦርነት ተከትሎ 1.3 ሚሊየን ገደማ ሰዎች ላይ ጉዳት ሲደርስ 3 ቢሊየን ገደማ ንብረት መውደሙን ደግሞ በተደረገ ቅድመ ጥናት መረጋገጡን ነው። 

በክልሉ በጦርነቱ ዳፋ የተጎዱትን አከባቢዎች መልሶ ለመገንባት የክልልና የፌዴራል መንግስታት በቅንጅት እየሰሩ ነው የሚሉት ባለስልጣናቱ ወደተግባሩ መገባቱንም አክለዋል፡፡ አቶ መሃመድ አህመድ። ከባለፈው ዓርብ ጀምሮ አማጺያን መሽገውበት ነበር የተባለው የአሳጊታ ምሽግ መሰበሩን ተከትሎ በአፋር በኩል የመንግስት ሰራዊት የበላይነት ወስደው በርካታ ስፍራዎችን መቆጣጠራቸው መነገሩ ይታወሳል።

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ