1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሕንድ፦የዓለማችን ትልቊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

ዓርብ፣ መጋቢት 18 2012

ሕንድ ውስጥ የኮሮና ተሐዋሲ ያልገባበት ግዛት የለም። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቢያንስ አንድ ቢሊዮን ሰዎችን የሚመለከት ነው። እንዲህ ያለ መጠነ ሰፊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ዐልታየም።

https://p.dw.com/p/3a3cC
Indien Kalkutta | Coronavirus | Aufruhr in Gefängnis
ምስል DW/P. Tewari

ባቡር የለ፤ ታክሲ የለ፤ የአየር በረራ የሚባል የለ

ሕንድ የኮሮና ተሐዋሲን ለመዋጋት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመላ ሀገሪቱ አስነግራለች።  አዋጁ በተወሰነ መልኩ ከማይመለከታቸው አካላት ውጪ በመላ ሀገሪቱ የጸና እንደሚኾን ነው የተገለጠው። ሕንድ ውስጥ የኮሮና ተሐዋሲ ያልገባበት ግዛት የለም። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቢያንስ አንድ ቢሊዮን ሰዎችን የሚመለከት ነው። እንዲህ ያለ መጠነ ሰፊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ዐልታየም።

ባቡር የለ፤ ታክሲ የለ፤ የአየር በረራ የሚባል የለ። ሕንድ ኹሉ ነገሯን ዘጋግታለች። ካለፉት ሦስት እና አራት ቀናት አንስቶ አንድ በአንድ እያለ በመላ ሕንድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል። ሰዎች ወደ ውጪ እንዲሔዱ የሚፈቀድላቸው የምግብ ሸቀጦችን ለመግዛት ወይንም ደግሞ ሐኪም ቤት ቀጠሮ ካላቸው ብቻ ነው። በተለይ በመዲናዪቱ ኒው ዴልሂ ውሳኔው እጅግ ጽኑእ ይመስላል። የኒው ዴልሂ የጤና ሚንሥትር ጄይን ስለ ውሳኔው ሲናገሩ ነዋሪው ፍጹም ሳይደመም አልቀረም።

«ዛሬ ከመድኃኒት መሸጫዎች፤ ከሐኪም ቤቶች፤ ክሊኒኮች እና የመባልእት መሸጫ መደብሮች ውጪ በአጠቃላይ ምንም እንዳይከፈት መወሰኑ ለኹሉም ግልጽ የኾነ ይመስላል። አስረግጬ መናገር የምሻው ውሳኔውን የማይከተሉ በገንዘብ የሚቀጡ ወይንም የሚታሰሩ መኾኑን ነው» 

Indien Coronavirus
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Swarup

በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ላይ ፖሊሶች ጎዳናዎች ላይ ሰዎችን በቆመጥ ሲነርቱ የሚታይባቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎች ተሠራጭተዋል። ከመላው ሀገሪቱ የወጡ መሰል ቪዲዮዎች  ማኅበራዊ መገናኛ አውታሩን አጨናንቀዋል። አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በብርቱ የጎዳው የእለት ጉርሳቸውን ለማግኘት በየጎዳናዎቹ የሚንከራተቱትን ምንዱባኖች ነው። የህንድ ጋዜጠኞች በርካታ መንገደኞች ከኒው ዴልሂ ወደ ሀገሪቱ የተለያዩ የገጠር መንደሮች ሲያቀኑ የሚያሳዩ ፎቶዎችን አንስተዋል። እነዚህ ሰዎች ወደ ገጠሪቱ ክፍል አቅንተው እዚያ በሚኖሩ ቤተሰቦቻቸው ዘንድ ተሐዋሲው እንዳይሰራጭ ለማድረግ ታስቦም ነበር አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነገሩ። ተሐዋሲው በገጠሪቱ ክፍል ከተስፋፋ ጥፋቱ የከፋ ነው የሚኾነው።   

በከተሞች ውስጥ አብዛኛው ነዋሪ በተቻለው መጠን እቤቱ ውስጥ ለመቆየት ጥረት እያደረገ ነው። ከፖሊተከኞች አንስቶ እስከ ታዋቂ የቦሊውድ የፊልም ባለሞያዎች ነዋሪው ራሱን ከተሐዋሲው እንዴት መከላከል እንዳለበት የሚያስገነዝቡ መልእክቶችን በተንቀሳቃሽ ምስሎች ያስተላልፋሉ። 

የሕንድ ጠቅላይ ሚንሥትር ናሬንድራ ሞዲ አሠሪዎች ለሠራተኞቻቸው ደመወዝ መክፈል እንዲቀጥሉ ጥሪ አስተላልፈዋል። የቦሊውድ ተዋንያን በተለያየ አቅጣጫ ኅብረተሰቡን ለማስገንዘብ ጥረት እያደረጉ ነው። በሕንድ ፊልም ስሙ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ዝነኛው ተዋናይ ሻህ ሩቅ ካህን አዝናኝ እና አስቂኝ በኾነ መንገድ ስለ ኮሮና ተሐዋሲ ገለጣ አድርጓል።  

Indien Kalkutta Coronavirus
ምስል DW/P. Tiwari

በሕንድ ለማመን በሚያስቸግር ኹኔታ የተዛቡ እና የሐሰት መረጃዎች እየተሠራጩ በመኾኑ ነዋሪው ከኮሮና ተሐዋሲ ያድነኛል በሚል የላም ሽንት ለመጠጣት ሲረባረብ ተስተውሏል። ያም በመኾኑ ሻሩቅ አዝናኝ በኾነ መንገድ ሰዉ መንግሥትን ወይንም ባለሥልጣናት የሚሉትን መስማት እንዳለበት በመግለጥ ከኮሮና እንዴት ራስን መጠበቅ እንደሚገባ እና ምልክቶቹም ምን እንደሚመስሉ ማብራሪያ ሰጥቷል። 

ከዚያም ከፊልሞቹ ምርጥ ምርጥ ትእይንቶችን እየመረጠም አሳይቷል። ኮሮና ተሐዋሲ በርካታ ነዋሪ ባላት ሕንድ ውስጥ እንደ ሱናሚ በርካቶችን ሊቀጥፍ ይችላል ሲሉ ባለሞያዎች ከወዲሁ ስጋታቸውን ገልጠዋል።  ያም በመኾኑ ብዙዎች ከፊታቸው የተደቀነው ን ፈተና ለመጋፈጥ የተቻላቸውን ጥረት እያደረጉ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ የሀገሪቱ ዕውቅ ተዋንያን ኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲጨብጥ እየተረባረቡ ነው። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ