1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሂደት ተጨማሪ ድጋፍ መጠየቁ

ረቡዕ፣ መስከረም 2 2011

ኢትዮጵያ በጀመረችዉ የዲሞክራሲ ጉዞ ላይ ተጨማሪ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ያስፈልጋታል ተባለ። ለውሁዳን  ሕዝቦች መብት የሚሟገተው  የጀርመን ድርጅት ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ የአዉሮጳ ኅብረት ከአፍሪቃ ስደተኞች እንዳይመጡበት ከፈለገ ኢትዮጵያ ስርዓተ ዴሞክራሲን ለመትከል የምታደርገውን ጥረቷን በይበልጥ መደገፍ አለበት።

https://p.dw.com/p/34lnu
Deutschland Gesellschaft für bedrohte Völker Logo

«አውሮጳውያን ፖለቲከኞች በአካባቢው ምን እየተካሄደ እንደሆን በጥንቃቄ የማጤን ስሜት ይጎድላቸዋል ።»

በኢትዮጵያ በወቅቱ የተነቃቃውን የስርዓተ ዴሞክራሲ ሂደት ማጠናከር ካለፉት አሰርተ ዓመታት ወዲህ ውዝግብ ያልተለየውን  የአፍሪቃ ቀንድ ለማረጋጋት ወሳኝ ርምጃ ሊሆን እንደሚችል ገዜልሻፍት ፉር በድሮህተሜንሽን(Gesellschaft für bedrohte Völker) የተባለው ለውሁዳን ሕዝቦች መብት የሚሟገተው  የጀርመን ድርጅት አስታወቀ። ድርጅቱ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫው የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ሂደት በወቅቱ በይበልጥ መደገፍ  አስፈላጊ ነው ያለበትን ምክንያት የድርጅቱ ኃላፊ ኡልሪኽ ዴሊዩስ ለDW አስረድተዋል።
« በአፍሪቃ ቀንድ ጠቅላላው በአሁኑ ጊዜ ታሪካዊ  ክስተት ታይቷል። ባካባቢው ካለፉት አሰርተ ዓመታት ወዲህ ለታዩት ውዝግቦች  መፍትሔ ለማግኘት ጥሩ እድል ፈጥሯል። በተለያዩ ቡድኖች መካከል፣ በኢትዮፕያ እና በኤርትራ፣ በኤርትራ እና በሶማልያ መካከል መቀራረብ ታይቷል። በኢትዮጵያም  በጣም አስፈላጊ፣ ግን በተለያዩ ሁኔታዊች ስጋት የተደቀነበት ዴሞክራሲያዊ ሂደት ተጀምሯል። በአሁኑ ጊዜ የብዙ ታዋቂ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች እና የመንግሥት ተቺዎች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል። ይህ ሁሉ ለአዲስ ጅምር ጥሩ እድል ይዟል።»
ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ብዙ ስቃይ፣ የመብት ጥሰት፣ ጦርነት ፣ የብዙዎች ስደት እና ሽሽትን ያስተናገደውን የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ችግሮችን ለማስወገድ የሚያስችለው አጋጣሚ በወቅቱ ተፈጥሯል።  በኢትዮጵያ ወደ ዘጠኝ ሺህ የሚጠጉ እስረኞች፣ ጥቂት የማይባሉ የፖለቲካ እስረኞች ጭምር  የተፈቱበት ድርጊት አዲስ ጅምር ለማነቃቃት ወሳኝ ርምጃ መሆኑ አይካድም የሚሉት ኡልሪኽ  ዴልዩስ፣ በሀገሪቱ የተፈጸመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት መለስ ብሎ በማየት የመብት ጥሰት ፈጻሚዎቹ በፍርድ ሊጠየቁ እንደሚገባ አሳስበዋል፣ ይህ ኢትዮጵያን የሚጠብቃት ቀጣይ ተግዳሮት  ነው ያሉት ዴልዩስ ኢትዮጵያ በመጀመሪያ  በዴሞክራሲያዊ ሂደቱ ላይ የተጋረጡባትን ብዙ ችግሮች እንድታሸንፍ  ተጨባጭ ርዳታ ማግኘት ይኖርባታል ብለዋል። ግን እንደሚታየው ይህን ድጋፍ ከጀርመንም ሆነ  ከአውሮጳ ህብረት በወቅቱ እያገኘች እንዳልሆነ ዴልዩስ በቅሬታ ገልጸዋል።
« የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከጥቂት ጊዜ በፊት አፍሪቃ ነበሩ፣ ግን የጎበኙት ምሥራቅ አፍሪቃን ሳይሆን ምዕራብ አፍሪቃን ነው። እና ይህን ዓይነቱን ነገር ስመለከት፣ አንዳንዴ ፖለቲከኞች በአካባቢው ምን እየተካሄደ እንደሆን በጥንቃቄ የማጤን ስሜት ይጎድላቸዋል ወይም ስላካባቢው ምን ያህል እውቀት አለ ብዬ እንዳጠያይቅ ያደርገኛል። በወቅቱ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድን እና ለውዝግቦች መፍትሔ ለማስገኘ።ት የጀመሩትን ጥረታቸውን የመደገፊያ ወሳኝ ጊዜ አሁን  ነው። ለዚሁ ጥረታቸውም በጣም ብዙ ርዳታ ያስፈልጋል፣ ግን ርዳታው ገንዘብ ብቻ መሆን የበትም። ጥረታቸው ይሳካ ዘንድ የአውሮጳ ህብረት መንግሥታት ከጎናቸው እንደሚቆሙ ፣ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን፣ እንዲሁም፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ፍትሓዊ ድንበር ያረጋገጠች ኢትዮጵያን ማየትን የመሳሰሉ ፍላጎቶችም እንዳላቸው የሚጠቁም ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። »
ኡልሪኽ ዴልዩስ እንደሚሉት ባለፉት ጊዚያት ከአውሮጳውያን ፖለቲከኞች ጋር ውይይት ባደረጉበት ጊዜ ሁሉ የታዘቡት አንድ ነገር፣ አውሮጳውያኑ  በኢትዮጵያ ለሚታየው ሁኔታ ሳይሆን የዩኤስ አሜሪካ፣ ሩስያ እና ቱርክ መሪዎች ለሚወስዷቸው አሳሳቢ ላሉዋቸው ጉዳዮች ትኩረት አለመስጠታቸውን ነው። እና ይህ ለምን ሆነ ሲሉም አጠያይቀዋል።
«  በኢትዮጵያ ባለፉት ወራት የተካሄደውን አስገራሚ ሁኔታ ማንም እያየው አይደለም። ለዚህም የኢትዮጵያን ጉዳይ ጆሮ ዳባ ያለው የአውሮጳ እና የጀርመን ፖለቲካ  ተጠያቂ ነው። ባንድ በኩል ከአፍሪቃ የሚታየውን ስደት እና ፍልሰት ለመታገል ፍላጎት እንዳለ ይናገራሉ። ግን አፍሪቃ ውስጥ አዎንታዊ ድርጊት ሲታይ፣ ያኔ ከአውሮጳ አንድም አበረታቺ ርምጃ አይመጣም።»
 የአውሮጳ ህብረት በርግጥ ከልብ ከአፍሪቃ ወደ አውሮጳ የሚፈልሰውን ስደተኛ  ቁጥር ለመቀነስ ከፈለገ ኢትዮጵያን ፈጣን በሆነ የተጠናከረ መንገድ መደገፍ አለበት። በዚያ ስለተጀመረው ዴሞክራሲያዊ ሂደት በይበልጥ መጠቆም እና ማጠናከርም እንደሚገባው ኡይሪክ ዴልዩስ አመልክተዋል።

Äthiopien Kality Gefängnis
ምስል DW/Y. G. Egziabher
Asmara - Premierminister Abiy Ahmed mit somalischem Präsidenten Formajo und Präsident Isaias
ምስል Prime Minister's Office/F. Arega

አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ