1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለኢሕአዴግ አባልነት ወረፋ የያዙት ፓርቲዎች

ሐሙስ፣ መስከረም 24 2011

የጋምቤላ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና የሐረሪ ክልሎችን ላለፉት 28 ዓመታት ገደማ ያስተዳደሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከአጋርነት አልፎ አባል ለመሆን በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ገዢው ግንባር አምስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአባልነት ለመቀበል እየተሰራ ነው ያለው ጥናት አለመጠናቀቁን አስታውቋል። 

https://p.dw.com/p/35zrL
EPRDF Logo

በሐዋሳ ከተማ በመካሔድ ላይ በሚገኘው ጉባኤ ኢሕአዴግ አጋር ብሎ የሚጠራቸውን አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች በአባልነት ባይቀበልም "የተለየ" ያለውን አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ አስታውቋል። በመክፈቻው ንግግር ያደረጉት የግንባሩ ሊቀ-መንበር ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ በኢትዮጵያ በነበረው ፖለቲካዊ ቀውስ ሳቢያ አጋር ተብለው የሚጠሩትን ፓርቲዎች አባል ለማድረግ የሚከናወን ጥናት አለመጠናቀቁን ገልጸዋል። 

ጠቅላይ ምኒስትሩ "ፓርቲያችን በታሪክ አጋጣሚ የአራት ድርጅቶች ጥምረት ሆኖ ቢመሰረትም አጋር ፓርቲዎችን ወደ ግምባሩ ለማስገባት ፍላጎት እንደነበረው የሚታወቅ ነው። ሆኖም ጉዳዩ ሳይሳካ ለረዥም ጊዜ ቆይቶ በ10ኛው ጉባኤ ወቅት ይኸ ጉዳይ ተጠንቶ መቋጫ እንዲያገኝ አቅጣጫ ተቀምጦ የነበረ ቢሆንም ከጉባኤው በኋላ የነበረው አገራዊ ሁኔታ ይኸን ለመከወን የሚያስችል ስላልነበረ ጥናቱ ተጠናቆ ለዚህ ጉባኤ ሊቀርብ አልቻለም" ሲሉ ተናግረዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ በኢትዮጵያ በነበረው አገራዊ ሁኔታ ተስተጓጉሏል ያሉት ጥናት ቢጠናቀቅ ኖሮ የአምስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአባልነት ጉዳይ ምላሽ ያገኝ ነበር። 

አምስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቤኒሻንጉል ጉምዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉህዴፓ)፣ የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋህዴን)፣ የሶማሌ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶህዴፓ)፣ የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) እና የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ (ሐብሊ) ናቸው። 

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ተወካይ አምባሳደር ሐሰን አብዱልቃድር እርሳቸው የሚመሩትን ጨምሮ አጋር ተብለው የሚጠሩት አምስት ፓርቲዎች "በሀገራዊ ጉዳዮች እና ውሳኔዎች በቀጥታ ተሳታፊ" እንዲሆኑ ሚናቸውን መለየት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። አምባሳደሩ "የአብዴፓ እና የሌሎች አጋር ድርጅቶች ሚና አጋር ከሚለው ስያሜ ወጥቶ በሀገራዊ ጉዳዮች እና ውሳኔዎች በቀጥታ ተሳታፊ እንድንሆን ይኸ ጉባኤ ታሪካዊ ውሳኔ ያስተላልፋል የሚል ዕምነት አለኝ" ሲሉ ተናግረዋል።  

የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምኅዳር ላለፉት 28 ዓመታት በበላይነት የተቆጣጠረው ኢሕዴግ የሚከተለው አሰራር አጋር የሚላቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር ያገለለ እንደሆነ ተንታኞች ይወቅሳሉ። የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ቻላቸው ታደሰ "በአንድ ፓርቲ በበላይነት በምትመራ አገር ውስጥ የፖሊሲ ሐሳብ ከሥራ አስፈፃሚው ነው የሚመነጨው። ከሥራ አስፈፃሚው የፖሊሲ ሐሳብ ይሔዳል። ያ የፖሊሲ ሐሳብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተመርቶ ነው የምኒስትሮች ምክር ቤት አርቅቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመራው" ሲሉ የኢትዮጵያ መንግሥታዊ መዋቅር የሚከተለውን አሰራር ያብራራሉ። አቶ ቻላቸው "ኢሕአዴግ በምክር ቤት ደረጃ፣ በኮንግረስ ደረጃ፣ በስራ አስፈፃሚ ደረጃ የሚወስናቸው ውሳኔዎች ላለፉት በርካታ አመታት የመንግሥት ፖሊሲ ሆነው ሥራ ላይ ሲውሉ እያየን ነው። እነዚህ አጋር ፓርቲዎች በፖሊሲ አወጣጥ ውስጥ ተሳታፊ አይደሉም" ሲሉ አሰራሩ ፓርቲዎቹን እና የሚመሯቸውን ክልሎች ያገለለ እንደሆነ ተናግረዋል። 

ፓርቲዎቹ እና ክልሎቻቸው በኢሕአዴግ የፖሊሲ አወጣጥ ተሳታፊ ባይሆኑም "ፖሊሲው አበአገር ደረጃ ሲፈፀም ተግባራዊ የሚሆነው ጋምቤላ ክልል ላይ ጭምር ነው። የሚፈጸመው ሶማሌ ክልል ላይ ጭምር ነው" የሚሉት አቶ ቻላቸው በጣም ተጎጂ አድርጓቸዋል ሲሉ ገልጸዋል። 

ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ በመድረኩ ባሰሙት ንግግር "ከዚህ በኋላ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ኢሕአዴግ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጎች ድርጅት መሆን እንዲችል እና አመራር ወይም ሊቀ-መንበር የመሆን መብት እያንዳንዱ ዜጋ እንዲኖረው ከዚያም አልፎ በኢሕአዴግ መሪነት የሐገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር የመሆን ዕድሉን እንዲጎናፀፍ ይኸ ጉባኤ የተለየ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል" ብለዋል። 

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ