1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለአጣዳፊ ተቅማጥ እና ተውከት ጥንቃቄ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 18 2011

ኢትዮጵያ ውስጥ የአጣዳፊ ተቅማጥ እና ተውከት በሽታ በየጊዜው ይከሰታል። የጤና ባለሙያዎች በንጽሕና ጉድለት ምክንያት እንደሚከሰት የሚያሳስቡት ይኽ በሽታ ኅብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንደሚያደርግ ይመክራሉ።

https://p.dw.com/p/3L4gK
Afrika Cholera Symbolbild Jemen
ምስል picture-alliance/dpa/M. Mohammed

«በሽታው ተገቢው ክትትል ከተደረገ መዳን ይችላል»

አጣዳፊ ተቅማጥ እና ተውከት የሚያስከትለው ኮሌራ በዋና ከተማ አዲስ አበባ 9 ክፍላተ ከተሞች እንዲሁም በኦሮሚያ፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች መከሰቱ ተገልጾ ኅብረተሰቡ ጤናውን እንዲጠብቅ ማሳሰቢያ እየተሰጠ ነው። በበሽታው ከ500 የሚበልጡ ሰዎች መያዛቸው፤ የሞቱትም ከ15 እንደሚበልጡ ተነግሯል። ባለፉት ሳምንታት በተለይ በሽታው በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል መስፋፋቱን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ተቋም ባለፈው ሳምንት አመልክቷል። በአንድ ከተማ ወይም አካባቢ በሽታው መከሰቱ በይፋ ከታወቀ ኅብረተሰቡ ሊያደርጋቸው የሚገባቸው ጥንቃቄዎች  አሉ።

ሙያዊ ምክር እንዲለግሱ የጠየቅናቸው በኢትዮጵያ  የዓለም የጤና ድርጅት የጤና ማበልፀግ ባለሙያ አቶ ዋስይሁን መላኩ፤ በሽታው በተለይ ሰዎች በሚመገቡት ምግብ እና በሚጠጡት ውኃ አማካኝነት ሊተላለፍ እንደሚችል በማስገንዘብ  ኅብረተሰቡ  በሽታውን  ለመከላከል ማድረግ የሚገባውን እንዲህ ይመክራሉ፤

«በተለይ በሽታው የሚተላለፈው ንጽህናው ብቻ ሳይሆን በተለይ የሚጠጣው የውኃ ምንጭ እና ለምግብ፣ ዕቃዎችን ለማጠብ እና ለንጽሕና የምንጠቀምበት ውኃ ስለሆነ በተቻለ መጠን የምንጠጣውን ውኃ እና ለምግብ አገልግሎት እና ለመሳሰሉት ነገር የምንጠቀምበትን የውኃ ማከሚያ ኬሚካሎችን በመጠቀም ውኃውን ንጽሕናውን መጠበቅ እና በንጹሕ ዕቃ ወይም ባልተበከለ በየጊዜው እየታከመ ንጽሕናው በሚጠበቅ ውኃ መጠቀም ይኖርብናል።»

Äthiopien Addis Abeba
ምስል DW/S. Muchie

ስለንጽሕና ሲወሳ ከሁሉ አስቀድሞ መታሰብ ያለበት የአካባቢ ንጽሕና ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ አቶ ዋስይሁን። ሰዎች የሚጠጡትም ሆነ የሚበሉት ንጽሕናው እንዲጠበቅ በየአካባቢው የመጸዳጃ ሁኔታዎች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እና ጽዳታቸውን መጠበቅ እንደሚገባም ያሳስባሉ። ሰዎች በመጸዳዳት  ሂደት ጥንቃቄ  አለማድረጋቸው ሊያስከትል የሚችለውን  የጤና መዘዝ እንዲህ ያስረዳሉ፤

«በአብዛኛው የሚተላለፈው በዚያ በሽታ የተያዘ ሰው አይነምድሩን በትክክለኛ በመጸዳጃ ቤት ከመጠቀም ፈንታ በየአካባቢ የሚያደርገው ከሆነ ከምግብ እና ከመጠጥ ውኃ ጋር ንክኪ ሊፈጠር ይችላል።»

ይኽ በሽታ በሀገሪቱ የዛሬ ሁለት ዓመትም በተለይ በትልልቅ ከተሞች አዲስ አበባ፣ ባሕር ዳር እና በመሳሰሉት ከተሞች ተከስቶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ዋስይሁን፤ በክረምት ወቅት ወይም ወቅቱ ሲቃረብ እንደሚያጋጥምም አንስተዋል። ይህን ታሳቢ በማድረግም በየጊዜው የሚመለከተው የጤና አካል ለኅብረተሰቡ  ተከታታይ የማንቂያ ትምህርቶች ለመስጠት እንደሚሞከሩም ገልጸውልናል።

የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው አጣዳፊ ተቅማጥ እና ተውከት የሚያስከትለው ኮሌራ በሰዓታት ውስጥ ሊገድል የሚችል በሽታ ነው። ጥናቶችን የጠቀሰው የድርጅቱ መረጃ በየዓመቱ ከ1,3 ሚሊየን  እስከ 4 ሚሊየን የሚደርስ ሕዝብ በመላው ዓለም በኮሌራ ይይዛል። በዚህ በሽታም ከ21 ሺህ እስከ 143 ሺህ ገደማ ሕዝብ በመላው ዓለም ሕይወቱን ያጣል። ምንም እንኳን በሽታው ገዳይ ነው ቢባልም ተገቢው የህክምና ክትትል እና ጥንቃቄ ከተደረገ 80 በመቶው ታማሚ እንደሚድንም ነው ያመለከተው የዓለም የጤና ድርጅት የጤና ማበልፀግ ባለሙያው አቶ ዋስይሁን ሰዎች ሊያደርጉት ይገባል ካሉት አንዱ በዚህ በሽታ ለተያዘ ሰው የሚደረገው የቤት ውስጥ ሕክምና አንዱ ነው።

Äthiopien Stadtansicht Mekele
ምስል DW/M. Hailessilasie

በየሳምንቱ ማክሰኞ ስለተከሰተው ተላላፊ በሽታ መግለጫ እንደሚሰጥ የሚገልጸው የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ተቋም ለዛሬ ያለውን መረጃ እንዲያካፍለን ከትናንት ጀምሮ ስንጠይቀን ነበር። የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ከጤና ጥበቃ ጋር በመተባበር ይህን መግለጫ የሚሰጡት አንድ ባለሙያ ብቻ መሆናቸውን በለፅ ዛሬን እንድንጠብቅ ቢነግሩንም ዛሬ የተባሉት ግለሰብ መግለጫ እንደማይሰጡ ለመረዳት ችለናል። የሕዝብ ግንኙነቷ ወ/ሮ ምንትዋብ ግደይ ጋዜጣዊ መግለጫ በጽሔፍ ለመበተን መዘጋጀታቸውን ሆኖም ግን ኢንተርኔት ግንኙነት ባለመኖሩ እንዳልቻሉ ገልጸውልን ከሰዓታት በኋላ በድጋሚ እንድንደውል ቀጥረውን ደጋግመን ብንደውልም ልናገኛቸው አልቻልንም። ከባልደረባቸው እንደተረዳነው የተባለው መግለጫ ዝግጅት አላለቀም። በነገራችን ላይ እንዲህ ያለው የኅብረተሰቡን ጤና የሚመለከት ጠቃሚ መረጃ ለኅብረተሰቡ የማዳረስ ኃላፊነት በጤና ጥበቃ እንደተሰጠው ቢነገረንም የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ግን ከትናንት ከቀትር በፊት ጀምረን በተደጋጋሚ ላቀረብንላቸው ማብራሪያ የመስጠት ጥያቄ ለመተባበር ፈቃደኞች ሳይሆኑልን እንደቀሩ ለመግለፅ እንወዳለን። ከዚሁ ተቋም የመረጃ ምንጮች  በተዘዋዋሪ ለመረዳት እንደቻልነው የኮሌራ በሽታ አዲስ አበባ ውስጥ እየተስፋፋ መሄዱን እና የታማሚዎች ቁጥርም መጨመሩን ነው። ኅብረተሰቡ የግል ንጽሕናውን በመጠበቅ ቀደም ሲል አቶ ዋስይሁን  የገለጿቸውን  አስፈላጊ ጥንቃቄዎች በማድረግ ጤናውን እንዲጠብቅ በማሳሰብ በዚሁ የዕለቱን መሰናዶ እናብቃ።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ