1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወደ አውሮጳ የተመለሱ የቀድሞ የአይ ኤስ ተዋጊዎች

ማክሰኞ፣ የካቲት 6 2010

ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው (በምህፃሩ አይ ኤስ የሚባለው) ቡድን በሶሪያ እና በኢራቅ ከባድ ሽንፈት ከገጠመው በኋላ ለቡድኑ ተሰልፈው ይዋጉ የነበሩ የተለያዩ የአውሮጳ ሀገራት ዜጎች ወደ የሀገሮቻቸው የመመለሳቸው ጉዳይ እያነጋገረ ነው።  ተመላሾቹ በአውሮጳ የሽብር ጥቃት ሊጥሉ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ።

https://p.dw.com/p/2sdIt
Terrorprozess gegen Syrien-Rückkehrer in Frankfurt
ምስል picture-alliance/dpa/B. Roessler

ወደ አውሮጳ የተመለሱ የቀድሞ የአይ ኤስ ተዋጊዎች

በቡድን ስር ለመዋጋት ከጎርጎሮሳዊው 2012 አንስቶ ከአውሮጳ ወደ ሶሪያ እና ኢራቅ የሄዱት ቁጥር 5 ሺህ ይደርሳል።  እስካሁን 1500 እንደሚሆኑ የሚገመቱ «የውጭ አሸባሪ ተዋጊዎች» የሚባሉት እነዚሁ የተለያዩ የአውሮጳ ሀገራት ዜጎች  ወደ አውሮጳ ተመልሰዋል። ከተመላሾቹ አንድ ሦስተኛው ከቤልጂግ ከጀርመን እና ከኔዘርላንድስ የሄዱ መሆናቸውን ባለፈው ሳምንት ብራሰልስ ቤልጂግ ውስጥ ይፋ የሆነ አንድ ጥናት ጠቁሟል።

በተመላሽ የውጭ ተዋጊዎች  ላይ ጥናት በሚያካሂደው ኤግሞንት በተባለው የብራሰልሱ ድርጅት  ዘገባ መሠረት አንዳንዶቹ ተመላሾች ፣ስሜታቸው ተነክቷል ሞላራቸውም ወድቋል። በጦርነት በተካፈሉባቸው ጊዜያት ባዩት እና ባጋጠማቸው ተደናግጠው የመንፈስ ጭንቀት ውስጥ ወድቀው የተመለሱም ጥቂት አይባሉም። ዶክተር ዳንኤል ሃይንከ በጀርመን የብሬመን የወንጀል ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ የኤግሞንቱ የጥናት ተቋም በተመላሽ የውጭ ተዋጊዎች ላይ ባካሄደው ጥናት ከተካፈሉት ተመራማዎች አንዱ ናቸው። በርሳቸው አስተያየት ሞራላቸው የወደቀ እና የመንፈስ ጭንቀት ያደረባቸው ተመላሾች እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።

Frankreich Polizei erschießt Mann vor Pariser Kommissariat
ምስል Reuters/P. Wojazer

« አንዳንዶች እዚያ በገጠማቸው ሁኔታ ቅስማቸው ተሰብሯል። ከአይ ኤስ አስተሳሰብ ለመላቀቅ ይፈልጋሉ። ሌሎች ደግሞ እዚያ ባዩት እና በደረሰባቸው መንፈሳቸው እጅግ በጣም ተረብሿል። በዚህ ሰበብ ጥቃት ወደ ማድረስ እንዳይሄዱ እርዳታ ያሻቸዋል።»

ከነዚህኛዎቹ በተለየ በአውሮጳ ጥቃት የመጣል ዓላማ ይዘው ከሶሪያ እና ከኢራቅ የሚመለሱ አሉ። ከመካከላቸው ብራሰልስ ውስጥ በጎርጎሮሳዊው 2014 በአንድ የአይ ኤስ ተመላሽ አውሮጳ ውስጥ የደረሰው የመጀመሪያው ጥቃት ተጠቃሽ ነው። በዚሁ ጥቃት መህዲ ሜሙቼ የተባለው ተመላሽ ብራሰልስ ቤልጂግ በሚገኝ አንድ የአይሁዶች ቤተ መዘክር ውስጥ ተኩስ ከፍቶ አራት ሰዎች ተገድለዋል። ብራሰልስ ተወልዶ ያደገው ነፍሰ ገዳዩ የቤልጅየም ዜጋ ለአይ ኤስ ሲዋጋ ህይወቱ አልፏል። ከዚያ በኋላ በተመላሽ የቀድሞ የውጭ ተዋጊዎች ሌሎች ጥቃቶችም ተፈጽመዋል። ከነዚህም ውስጥ በህዳር 2015 በፓሪስ ፈረንሳይ እንዲሁም በመጋቢት 2016 ብራስልስ ውስጥ የተጣሉት ጥቃቶች ይገኙበታል። ከዚያን ወዲህ በቀድሞ የውጭ ተዋጊ ተመላሾች አውሮጳ ውስጥ የተጣለ ጥቃት ባይኖርም ስጋቱ ግን እንዳለ ነው።

ከተመላሾቹ አንዳንዶቹ እጅግ አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ እንደ ዶክተር ሃይንከ ። ምክንያት ያሉትም ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላም ከአይ ኤስ አስተሳሰብ መላቀቅ አለመቻላቸው ነው። የቀድሞ የአይ ኤስ ተዋጊዎችን በተመለከተ የአውሮጳ ሀገራት የጋራ ፖሊሲ የላቸውም። እያንዳንዱ ሀገር የራሱን  እርምጃ ነው የሚወስደው። ብሪታንያ ለምሳሌ በውጭ ሲዋጉ የቆዩ ጂሀዲስቶች ተመልሰው ሀገርዋ እንዲገቡ አትፈቅድም። ቤልጂግ ፈረንሳይ እና ጀርመንን የመሳሳሉት ሀገራት ለአይ ኤስ ተሰልፈው ይዋጉ የነበሩ ዜጎቻቸው እንዲመለሱ ቢፈቅዱም የሚቀበሉበት እና የሚይዙበት መንገድ የተለያየ ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከጀርመን ብቻ ወደ አንዲ ሺህ የሚጠጉ ወንዶች እና ሴቶች የጀርመን ዜጎች  ለአይ ኤስ ተሰልፈው ለመዋጋት ሶሪያ እና ኢራቅ ሄደዋል። ከመካከላቸው አንድ ሶስተኛዎቹ መመለሳቸውም ተገልጿል። የጀርመን ዓለም አቀፍ የፀጥታ ጉዳዮች ጥናት ተቋም ባልደረባ ፔተር ሽታይንበርግ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት ወደ ጀርመን ከሚመለሱት አብዛኛዎቹ ይታሰራሉ። ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው መኖር የሚችሉባቸው መርሃግብሮች እንዲካፈሉም ይሞከራል።  

Deutschland 2015 | Prozess gegen ehemalige IS-Kämpfer | Ayoub B.
ምስል picture-alliance/dpa/J. Stratenschulte

« አንድ ሰውሲዋጋ ቆይቶ  ጀርመን ሲመለስ መጀመሪያ ጥብቅ ምርመራ ይካሄድበታል። አብዛኛዎቹ እስር ቤት ይገባሉ። ይህ የሚሆነውም እስላማዊ መንግሥት ሲል ራሱን ከሚጠራው ቡድን ጋር በመሰለፋቸው እና ይህንንም የሚያረጋግጥ ማስረጃ በመኖሩ ነው። ቡድኑን ለቀው የሚመጡም አሉ ። እዚያ ያዩትን እና የሆነውን በምስክርነት ይናገራሉ። ይህን የሚያደርጉት ቁጥር በንጽጽር ሲታይ አናሳ ነው። ከዚህ ሌላ ተመላሾቹ ከጽንፈኛ አመለካከት እንዲላቀቁ እና ከህብረተሰቡም ጋር ተዋህደው እንዲኖሩ ያስችሏቸዋል የተባሉ መርሃ ግብሮች ውስጥ እንዲካፈሉ ይሞከራል። »

ባለፉት ሁለት ዓመታት ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት የደረሰባት ፈረንሳይም በውጭ ሀገራት ሊዋጉ የሄዱ ዜጎችዋን በተመለከተ የምትከተለው መርህ ከጀርመን ጋር ቢመሳሰልም የሚለይበት መንገድ አለ። ከዛሬ 6 ዓመት ወዲህ ከ1500 የሚበልጡ የፈረንሳይ ዜጎች ሶሪያ እና ኢራቅ ውስጥ ለአይ ኤስ ተሰልፈው ተዋግተዋል። እንደ ፓሪስዋ ዘጋቢያችን ሃይማኖት ጥሩነህ ከመካከላቸው በቅርቡ ወደ ሀገራቸው የተመለሱት ቁጥር 200 ገደማ ነው። የነዚህ የቀድሞ ተዋጊዎች መመለስ ፈረንሳዮችን አስግቷል እንደ

ሃይማኖት እንደምትለው የፈረንሳይ መንግሥት ለተመላሽ የቀድሞ የውጭ ተዋጊ ፈረንሳውያን ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል። ከእቅዶቹ ውስጥ ተመላሾቹ ከህብረተሰቡ ጋር መዋሀድ እንዲችሉ መልሶ ማቋቋም ይገኝበታል።ከፈረንሳይ ፖለቲከኞች አብዛኛዎቹ እስር ቤቶች የሽብረተኞች መፈልፈያ ናቸው ሲሉ መንግሥት ተመላሾቹን ማሰሩን ይቃወማሉ። ለዚህ የሚሰጡት ምክንያትም ከዚህ ቀደም ፈረንሳይ ውስጥ የሽብር ጥቃቶች ከጣሉት ውስጥ አብዛናዎቹ ወደ አሸባሪነት የተቀየሩት በእስር ቤት ውስጥ ነው የሚል ነው።

Syrien Frau und Kind eines vermeintlichen IS Kämpfers in Rakka
ምስል Getty Images/AFP/B. Kilic

ወደ ጀርመን ስንመለስ ጀርመን ውስጥ አሁን ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ሶሪያ እና ኢራቅ ለውጊያ የሄዱ ዜጎች የወለዷቸው ልጆች አያያዝ ነው። ለአይ ኤስ ሊዋጉ ከጀርመን ወደ ሶሪያ እና ኢራቅ ከሄዱት 960 የጀርመን ዜጎች 200 ው ሴቶች ናቸው። ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል ከተባሉት ጀርመናውያን የቀድሞ የአይ ኤስ ተዋጊዎች መካከል 50 ያህሉ ሴቶች ናቸው። የጉዳዩ ተከታታዮች እንደሚሉት አጠቃላዩ ቁጥር ባይታወቅም እያንዳንዷ ተመላሽ ሴት ቢያንስ አንድ ልጅ ይኖራታል ተብሎ ይታመናል። እዚያ ተወልደው ካደጉት ልጆች መካከል ከፍ ከፍ ባሉት አስተሳሰብ ላይ የጽንፈኞች ፕሮፓጋንዳ ተጽእኖ ማሳደሩ እንደማይቀር ይታመናል።

ከጀርመን ህብረተሰብ አብዛኛው ልጆቹ እንደ ወላጆቻቸው ጽንፈኛ እንዳይሆኑ ከወላጆቻቸው እንዲነጠሉ እየጠየቀ ነው። ይህ ግን ቀላል እንደማይሆን ነው የሚገመተው።  በውጭ ሲዋጉ ቆይተው በሚመለሱ የአውሮጳ ዜጎች ጉዳይ ላይ የተካሄደው ጥናት እንደሚለው ከተመላሾቹ መካከል 11 በመቶው ወደ አሸባሪነት ተቀይረዋል። ከ100 በላይ የሚሆኑ ተመላሾችም በአውሮጳ ሀገራት ጥቃት የመጣል ሙከራ ማቀዳቸውን ተጠቁሟል። ከዚህ በመነሳትም በጥናቱ ተመላሾችን ከህብረተሰቡ የመዋሀዱ ሥራ እንዲጠናከር ሃሳብ ቀርቧል።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ