ለአንባቢያን «የመጽሐፍት ካፌ»
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 24 2012ማሩ ከልጅነቱ ጀምሮ የማንበብ ፍላጎት እንዳለው ይናገራል፡፡ ከ1500 በላይ መጽሐፍትን ማንበቡንም ከዶይቼ ቬሌ ጋር በነበረው ቆታ አመልክቷል፡፡ እየቀነሰ የመጣውን የማንበብ ልምድ ለመመለስና እስካሁን ያነበባቸውን መጽሐፍት በማጠራቀም “የመጽሐፍት ካፌ” በመክፈት ማንኛውም ሰው በነፃ እንዲያነብብ ሁኔታዎችን አመቻችቷል፡፡
ወጣት ማሩ እንደሚለው አንባቢ ትውልድ እየጠፋ ነው በመሆኑም ይህን ለመመለስ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ይህን ሥራ እንደጀመረው አመልክቷል፡፡ አሁን የንባብ ቦታ የሆነው አካባቢ እጅግ ቆሻሻ የበዛበት እንደነበር የሚናገረው ወጣት ማሩ አሁን አካባቢውን ለመጽህፍት ማንበቢያነት ብቻ ሳይሆን በራሱ ወጪ በማጽዳትና አትክልቶችን በመትል ማራኪ አድርጎታል፡፡
በመጽሐፍት ካፌው ውስጥ ሲያነብቡ ካገኘኋቸው ወጣቶች መካከል ወጣት መዝገቡ ማናዬ አንደገለፀልኝ የወጣት ማሩ ተግባር ለብዙዎቹ አርአያ መሆኑን አመልክቶ በተለያዩ ሱሶች ተጠምደው ሚውሉ ወጣቶች በእንደዚህ ያሉ ቦታዎች ቢውሉ በእውቀት እንደሚታነፁና ከሱሳቸው አንደሚላቀቁ ተናግሯል፡፡
እንግሊዝኛ መጽሐፍትን በብዛት እንደሚያነብብ የገለጸልኝ ወጣት ዮጋሳን ያሲን እዚህ በመዋሉ ከነበረበት ሱስ እየተላቀቀ ነው፡፡ ማንበብ ምሉዕ ደርጋል የሚለው ዮጋሳን የወታቱ የማንበብ ልምድ ገና አልተመለሰም ሲል አስተያየት ሰጥቷል፡፡
ወጣት ማሩ እንደችግር ያነሳው መጽሀፍቶቹን በየቀኑ ወደ ቤት ማመላለስ ለመጽሐፍቱ እንግልት፣ እንደዚሁም በዝናብ ወቅት ለብልሽት እየዳረጋቸው በመሆኑ የሚመለከተው አካል በዚህ ረገድ እገዛ እንዲያደርግለት ጠይቋል፡፡
መጽሐፍትን በቤታቸው ያከማቹ ሰዎችም በውሰት ወይም በስጦታ እንዲያበረክቱለትና ትውልዱን አንባቢ እናድርገው ሲል ጠይቋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ማንተጋፍቶት ስለሺ