1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለአማራ ሕዝብ መብትና ጥቅም ስብሰባ በፍራንክፈርት ከተማ

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 13 2011

“ለአማራ ሕዝብ መብትና ጥቅም መከበር በሰላም የሚታገሉ ግለሰቦችን መግደል ማሰር ማዋከብ እና ማሳደድ መቆም አለበት” ሲሉ በጀርመን የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ የአማራ ብሔር አደረጃጀቶች ጠየቁ። አደረጃጀቶቹ ዛሬ በፍራንክፈርት ከተማ በወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታ ላይ ስብሰባ አካሂደዋል።

https://p.dw.com/p/3MQUe
Deutschland | Meeting "Amhara diaspora organaizations" in Frankfurt
ምስል DW/E. Fekade

ለአማራ ሕዝብ መብትና ጥቅም ስብሰባ በፍራንክፈርት ከተማ

በጀርመን አገር የተለያዩ ከተሞች ነዋሪ የሆኑ የአማራ ብሄር አደረጃጀቶች አባላት ዛሬ ፍራንክፈርት ከተማ በሚገኘው የወጣቶች የስብሰባ ማዕከል ዩጉንድኸር በርገርሃውስ ባካሄዱት የጋራ ስብሰባ በሰኔ 15ቱ ጥቃት በተሰዉት የክልሉ አመራሮችና የአገሪቱ የጦር ሹማምንት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን በመግለጽ ነው ውይይታቸውን የጀመሩት።

ተሰብሳቢዎቹ ከለውጡ በኋላ በአገሪቱ ተከስተዋል ባሏቸው የተለያዩ ብሄር ተኮር የመብት ጥሰቶችና በተለይም መንግሥት "የከሸፈ መፈንቅለ መንግሥት" ካለው ከዚሁ አሳዛኝ ክስተት ወዲህ በአዲስ አበባና በአማራ ክልል እየተፈጸሙ ናቸው ባሏቸው የጅምላ እስራት ግድያና አፈና ችግሮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት እና ምክክር አካሂደዋል።

የስብሰባው ተሳታፊዎች “የኢትዮጵያ መንግሥት የሰኔ 15ቱን ክስተት እንደ ሽፋን በመጠቀም፤ ለሥርዓቱ አስጊ ናቸው የሚላቸውን ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ አመራሮች እና ደጋፊዎች፣ የመብት ተሟጋቾች እንዲሁም ባለሃብቶችን ጭምር ልዩ ልዩ ስም በመስጠት በጅምላ አስሯል፤ አዋክቧል” ሲሉ ወንጅለዋል። ይህን መሰሉ አካሄድ “የተጀመረውን የለውጥ ሂደት የሚያደናቅፍ አደገኛ ተግባር ነው” ሲሉም ተችተዋል።

Deutschland | Meeting "Amhara diaspora organaizations" in Frankfurt
ምስል DW/E. Fekade

ተወያዮቹ የኢትዮጵያ መንግሥት “በሴራ ፖለቲካ አላግባብ አስሯቸዋል” ያሏቸውን የሕሊና እና የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈታ እና የአማራ ብሄርተኝነትን ትግል ለማዳከም በክልሉ እያካሄደ ያለውን ጣልቃ ገብነት በአንድ ወር ውስጥ እንዲያቆም ቀነ ገደብ ሰጥተዋል። ይህ ካልሆነ ግን በመላው ዓለም የሚገኙ የአማራ ዳያስፖራ ተወላጆችን በማስተባበር ዲፕሎማሲያዊ ተጽዕኖዎችን እና የፋይናንስ ዕቀባ ትግሎችን እንጀምራለን ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በዛሬው የፍራንክፈርት ውይይት የተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ለስብሰባው ታዳሚያን ከአዲስ አበባ በስልክ መልዕክት አስተላልፈዋል። ዶ/ር ደሳለኝ የድርጅታቸው አመራሮች፣ በርካታ የአብን አባላት እና አማራዎች በተለይም የሰኔ 15ቱን ክስተት ተከትሎ በማንነታቸው ምክንያት አላግባብ እየታሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። “ይህ አይነቱ የመብት ጥሰት አማራው መብቱን ለማስከበርና እራሱን ከጥቃት ለመከላከል የጀመረውን ሰላማዊ ትግል አያስቆመውም” ብለዋል። 

እንዳልካቸው ፈቃደ 

ተስፋለም ወልደየስ