1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣናት ምህረት ተጠየቀ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 29 2010

የ1983ቱን የደርግ ዉድቀት ተከትሎ ላለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያ በሚገኘዉ የጣሊያን ኢምባሲ በጥገኝነት የሚገኙት ሁለት የደርግ ባለስልጣናት መንግስት ምህረት ተደርጎላቸዉ ወደ ቤተሰቦቻቸዉ እንዲቀላቀሉ ተጠየቀ።

https://p.dw.com/p/34E6r
Äthiopien Urteil Prozess gegen Mengistu und seine Minister
ምስል AP

MMT - MP3-Stereo


 የቀድሞ ከፍተኛ  ባለስልጣናቱ የቅርብ ተጠሪ የምህረት ጥያቄዉን ያቀረቡት የሰዎቹን እድሜ፣ የጤና ሁኔታ እንዲሁም ላላፉት 27 ዓመታት የቆዩበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ግምት ዉስጥ በማስገባት  ነዉ።  
በደርግ መንግስት የዉጭ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩት ሌትናል ጄነራል አዲስ ተድላና ኢታማዦር ሹም የነበሩት ሌትናል ኮለኔል ብርሃኑ ባይህ ላለፉት 27 ዓመታት በጣሊያን ኢምባሲ ተጠግተዉ የቆዩ ሲሆን እነኝህ ሁለት የቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣናት ክስ ተመስርቶባቸዉ በሌሉበት የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸዉ ነበር ሲሉ የሊትናል ጀነራል አዲስ ተድላ የቅርብ ዘመድና የሁለቱም የቀድሞ ባለስልጣናት የቅርብ ተጠሪ ነኝ ያሉት ወይዘሮ አስራትነሽ ከበደ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
ይሁን እንጅ  በ 2003 ዓ/ም ፍርድ ቤቱ ጉዳያቸዉን በድጋሜ በማየት ወደ እድሜ ልክ እስራት አሻሽሎላቸዉ  የነበረ ቢሆንም  የቀድሞ ባላስልጣናቱ ከተጠጉበት  የጣሊያን ኢምባሲ ወጥተዉ የዕስር ቅጣቱን  ለመቀበል  ባለመፍቀዳቸዉ  ላለፉት 27 ዓመታት ከዘመድና ከቤተሰብ ርቀዉ በጥገኝነት ቆይተዋል ብለዋል። የቀድሞ ባለስልጣናቱ ኢምባሲዉ ዉስጥ መቆየት የመረጡበትን ምክንያትም  እንዲህ ያብራራሉ። 
ይሁን እንጅ ባንድ መዝገብ በቀይ ሽብር ወንጀል የተከሰሱ መሰል ባለስልጣናት የእስር ጊዚያቸዉን ሳያጠናቅቁ  ከ6 ዓመት በፊት በአመክሮ በመፈታታቸዉ በወቅቱ  አቤቱታ አቅርበዉ እንደነበር ይናገራሉ።
በቅርቡም በኢትዮጵያ የተጀመረዉን ለዉጥ ተከትሎ  ይቅርታና ምህረት ይደረግላቸዋል በሚል ተስፋ  የአቤቱታ ቅጽ መሙላታቸዉን የተናገሩት ወይዘሮ አስራቴነሽ ነገር ግን በቀይ ሽብር የተከሰሱ ሰዎችን ይቅርታዉ አያካትትም መባላቸዉን ገልፀዋል።
እንደ ወይዘሮ አስራት ነሽ ፤የቀድሞ ባለስልጣናቱ  በጥገኝነት በተቀመጡበት የጣሊያን ኢምባሲ በዓመት ሦስት ጊዜ ብቻ  ከአራት በማይበልጡ ሰዎች ከመጎብኘት ዉጭ ከቤተሰቦቻቸዉ ጋር በስልክም ይሁን በአካል የመገናኔት ዕድል የላቸዉም።ያም መሆኑ የቀድሞ  ባለስልጣናቱ   ከዕስር በላይ የሆነ ከባድ ጊዜ እያሳለፉ መሆኑ አሳዛኝ ነዉ ብለዋል። ከ23 ዓመት በላይ ሊታሰሩ በማይችሉበት ሁኔታ ላለፉት 27 ዓመታት ከሰዉ ተነጥለዉ የሚገፉት ህይወት ከቅጣትም በላይ መሆኑን ተናግረዋል። የተከሰሱበትን ወንጀል ጠበቃ አቁሞ ለመከራከርም ቢሆን ችግር እንዳጋጠማቸዉ ነዉ የሚናገሩት።«ሌላዉ ቀርቶ ዉክልና ሊሰጡም አይችሉም እነሱ።መታወቂያም የላቸዉም ኢምባሲዉ በእንግድነት ነዉ ያስቀመጣቸዉ። እንጅ ጠበቃ ማነጋገር እንኳ ጠበቃዉ ማን ነኝ ይላል። የተወከለበት ነገር ከሌለ።እና በጣም ከባድ ነዉ።»
ማንም ሰዉ ቢሆን ከህግ በላይ ሊሆን አይችልም ያሉት ወይዘሮ አስራቴነሽ ከበደ የሰዎቹን የዕድሜና የጤና ሁኔታ እንዲሁም ያሉበትን  አሳዛኝ ሁኔታ በመረዳት መንግስት ይቅርታ እንዲያደርግላቸዉ ጠይቀዋል።
እሳቸዉ ይህን ይበሉ እንጅ የህግ ባለሙያዉ  ጠበቃ ሽብሩ በለጠ በኢትዮጵያም ይሁን በዓለም አቀፍ ህግ  መሰረት የተከሰሱበት የዘር ማጥፋት ወንጀል  ይቅርታና ምህረት የሚከለክል መሆኑን ያስረዳሉ።
ያም ሆኖ ግን በተከሳሾቹ ላይ ዕስር ለመፈፀም የማያበቃ አካላዊና ሌሎች ሁኔታዎች ካሉ በጠባቡም ቢሆን አነስተኛ ዕድል መኖሩን የህግ ባለሙያዉ ጠቁመዉ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ዝርዝር ነገሮችን በደንብ ማየት እንዳለበት ነዉ ይስረዱት።

Äthiopien Statue kommunistischer Soldaten ind Addis Abeba
ምስል DW/J. Jeffrey
Äthiopien Soldaten marschieren auf dem Revolutionsplatz ein
ምስል DW/J. Jeffrey

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በቅርቡ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫም በቀይ ሽብር ለተከሰሱ ሰዎች የሀገሪቱ ህገ መንግስት ምህረትን እንደሚከለክል መናገራቸዉ ይታወሳል።

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ ያድምጡ።

 

ፀሐይ ጫኔ

አዜብ ታደሰ