1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድሬደዋ ወጣቶች ድጋፍ

እሑድ፣ ሚያዝያ 11 2012

በድሬደዋ ከተማ የሚገኙ ወጣቶች በየአካባቢው ለሚገኙ በርካታ ችግረኛ እና አቅመ ደካማ ሰዎች ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ተረጂዎቹ በተለይ የዛሬውን በዓል  በደስታ እንዲያሳልፉ የገንዘብ ፣ የምግብ እና ሌሎች ድጋፎች ተደርጎላቸዋል።

https://p.dw.com/p/3b96G
Äthiopien Dire Dawa | Unterstützung der Jugend an Ostern
ምስል DW/M. Teklu

ቀድሞም ቢሆን የዕለት ጉርስ ማግኘት ፈተና በሆነባቸው ወገኖች ላይ የኮሮና በሽታ ስርጭት ስጋት ያስከተለው የእንቅስቅቃሴ ገደብ ተደምሮ  ህይወት ፈተና ውስጥ እንዲገባ አድርጓል ፡፡ ይኸው ግድ ያላቸው በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች በችግር ውስጥ የሆኑ ወገኖችን ለመርዳት ሰፊ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
የበሽታው ስርጭት ስጋት እንደወትሮ ስራዬን  እንዳልሰራ አድርጎኛል ያለች የሁለት ልጆች እናት ሳቢያን በሚባለው አካባቢ ያሉ ወጣቶች ስለተደረገላት ድጋፍ ደስተኛ ናት « አስቤዛ ነበር የምሸጠው። አሁን ግን እቤት ነው የምገኘው።» ትላለች። ለአብነት ተዘዋውረን ካየናቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው ሳቢያን የሚገኙ ወጣቶች ከበዓል ባለፈ ለተወሰነ ጊዜ ለአስቤዛነት የሚውሉ  ድጋፎች ሲሰጡ ተመልክተናል፡፡የደገፏቸውን ወጣቶች ያመሰገኑ አንድ እናት  ፤ ችግርን ይብሱኑ ያጠናው በሽታ መፍትሄ እንዲያገኝ ለፈጣሪ ፀሎት እያደረሱ መሆኑን ነግረውናል፡፡ ለሶስት መቶ እናቶች ለተወሰነ ጊዜ የሚሆን የአስቤዛ ድጋፍ ያደረገው የሳቢያን አካባቢ ወጣቶች ጥረትን በሚመለከት አስተባባሪው ወጣት ነፃነት ጥላሁን « በወቅቱ በሽታ ምክንያት ወጥተው አስቤዛ መግዛት የማይችሉ ሰዎች ስላሉ እኛ በጎልበታችን ሳንቲም ያለውም በሳንቲም እያገዘ ነው።» ይላል።
በጎዳና ላሉ ፣ አቅመ ደካማና ችግረኛ ለሆኑ ወገኖች የትንሰዔ በዓልን እንዲያከብሩ ለማስቻል በተለያዩ አካባቢዎች ወጣቶች ያስተባበሯቸው ድጋፎች ተደርገዋል ፡፡ በወጣቶች የጋራ ሀሳብ በየቦታው በሚከናወነው የድጋፍ ተግባር ባለሀብቶች እና ህብረተሰቡ አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆኑ ታውቋል ፡፡ ለነዋሪው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የመስተዳድሩ ምክትል ከንቲባ  አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ ህብረተሰቡ በመረዳዳት እና በመተጋገዝ በዓሉን እንዲያከብር ጠይቀዋል ፡፡ 

Stadt Dire Dawa in Äthiopien
ምስል Hailegzi Mehari


መሳይ ተክሉ
ልደት አበበ