1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለ«ሶስተኛው ምዕራፍ» የቀጠለው ጦርነት

ዓርብ፣ ኅዳር 18 2013

ምዕራፍ ሶስት ዘመቻው ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚንስትሩ የሕወሓት ታጣቂዎች እና አመራሮች በ72 ሰዓታት ውስጥ እጃቸውን እንዲሰጡ ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ መጠናቀቁን ተከትሎ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩ ተነግሯል። ከሕወሓት ወገን የክልሉ ልዩ ኃይልም ሆነ የክልሉ መንግስት ቃል አቃባዮች በኩል የተሰጠው ምላሽ በውግያው እንደሚገፉበት ነው።

https://p.dw.com/p/3lvd7
Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በሚያያዙ ጉዳዮች ላይ በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰጡ አስተያየቶችን  ያሰባሰበው   የዕለቱ ዝግጅታችን ተጀምሯል። 
በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት ኃይሎች እና በህወሃት መራሹ የትግራይ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻዎች መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት 24 ቀኑ ላይ ደርሷል። ጦርነቱ  ከተቀሰቀሰበት ቀን ጀምሮ የማይካድራውን የሰላማዊ ሰዎች ጭፍጨፋን ጨምሮ በሁለቱም ወገን ወታደራዊ ኃይሎች ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ማድረሱ እየተነገረ ነው። የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ ወደ ጎረቤት ሀገር ሱዳን የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ40,000 ማለፉንም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል። ምንም እንኳ ቁጥሩ በገለልተኛ አካል ባይረጋገጥም  በትግራይ ክልል ውስጥም በተመሳሳይ ከከተሞች ወደ ገጠራማ አካባቢዎች የሰላማዊ ሰዎች መፈናቀል እየተነገረ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ሕወሓት «በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ወታደራዊ መንደሮች ላይ ጥቃት በማድረሱ» ባለው በሶስት ምዕራፍ በተከፋፈለ «የመከላከል እና የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ» ሶስተኛው ምዕራፍ ላይ ደርሶ የመከላከያ ሰራዊቱ የመቀሌ ከተማን በመክበብ የሚያደርገው የመጨረሻ የማጥቃት ዘመቻ መጀመሩን ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ይፋ አድርገዋል። 
ምዕራፍ ሶስት ዘመቻው ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚንስትሩ የሕወሓት ታጣቂዎች እና አመራሮች በ72 ሰዓታት ውስጥ እጃቸውን እንዲሰጡ ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ መጠናቀቁን ተከትሎ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩ ተነግሯል። መንግስት የህወሓት ኃይሎች እጅ እንዲሰጡ ሲጠይቅ ከህወሃት ወገን የክልሉ ልዩ ኃይልም ሆነ የክልሉ መንግስት ቃል አቃባዮች በኩል የተሰጠው ምላሽ በውግያው እንደሚገፉበት ነው። ጦርነቱ መቀጠሉ እርግጥ ሆኗል። ይህንኑ ተከትሎ በርካቶች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች  አማካኝነት አስተያየቶቻቸውን አጋርተዋል።
ሃና አርአያ ባሰፈሩት መልዕክታቸው «መቼ ይሆን ችግሮቻችንን ያለጦርነት የመፍታት ዕውቀት የሚኖረን ? በዕድሜዬ የሀገሪቱን ችግሮቻ በሁከት፣በግድያ እና በማፈናቀል ለመፍታት የሞከሩ ሶስት መንግስታት ሲመጡ እና ሲሄዱ ተመልክቻለሁ ። በዚህ ሂደት ተጠቂው ሁል ግዜም ህዝብ ነው  ። ሁሌም ለኢትዮጵያ ለቤ ያዝናል። »ብለዋል።
አክሊሉ አዳነ «በእኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አስተሳሰብ ተቃኝተዉ የተደራጁና እስካሁን የኖሩ፡ ህዝብን የመማገድ ልምዳቸዉን መቸም ብሆን የማይተዉ ባንዳዎች የሰላምና የሰለጠነ እንዲሁም የህዝብን ጥቅም ያስቀደመ ጥሪ እንደማይዋጥላቸዉ እየታወቀም ብሆን መንግስት ግን በሆደ ሰፊነት አሁንም ህግ በማስከበር ርምጃ ዉስጥም ብሆን ሰላማዊ አማራጭን አሟጦ እየተጠቀመ መሄዱ በጣም የሚደነቅና የሰለጠነ አካሄድ በመሆኑ ሁለም ከመንግስት ጎን ሆነን ሌቦች ለህግ እስክቀርቡ ድረስ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥል። » በማለት ጽፈዋል።
 ቴዲ ማን የተባሉ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸው «ሰው ሲቸግረው ልብሱን ይሸጣል፣በጣም ከቸገረው ኩላሊቱን ይሸጣል፤ ሰው ግን ምን ቢቸገር እንዴት የሰው ደም እየፈሰሰ ህሊናውን ይሸጣል?» የሚል ጥያቄያዊ አስተያየታቸውን አስፍረዋል። 
አብዱለጢፍ አብዱልቃድር ደግሞ «እኔ አልገባኝም! በጣም ግራ ገብቶኛል! ኢትዮጵያዊነት ማለት ምን ማለት ነው? ኢትዮጵያዊ የሚባለውስ ማነው? ያልሆነውስ ማነው?ለመደገፍ፣ ለመቃወም፣ ለመውደድ፣ ለመጥላት፣ ለመግደል ለማሰር፣ ለማፈናቀል፣ ወዘተ የኢትዮጵያን ስም ትጠራለህ! ታድያ ለምንድነው ኢትዮጵያን እያልክ ልጆችዋን የምትገድለው፣ የምታስለቅሰው፣ የምታፈናቅለው፣ የምታስረው፣ አንዱ ሲገድል ቆመህ በለው የምትለው?» ሲሉ በደፈናው ጦርነቱ በአጠቃላይ በሀገሪቱ ላይ የሚያደርሰውን ጥፋት በመስጋት ሃሳባቸውን አጋርተዋል።
ተስፋለም ሃይሉ ባሰፈሩት አስተያየታቸው «ከቤት እንዳይወጡ ለተደረጉት የመቀሌ ሕዝቦች ሲባል መንግስት ወደ አፋጣኝ ተግባር  ገብቶ የገዛ ሕዝቡን ከሞት እንዲታደግ ጥሪዬን ማድረግ እወዳለሁ። ባለፈው እጅ መስጫ ጊዜ ብላችሁ የሰጣችሁት 72ሰዓት ለእኔ ለንፁሐኑ ሌላ 72 ሰዓት የረሃብ ጊዜ እንደሰጣችሁ ነበር የቆጠርኩት።» ብለዋል።
አብዱ ሰኢድ ደግሞ «ሕወሓት ጦርነቱን አለማቀፋዊ ለማድረግ ያልሞከረው የለም። ሳምሪ ማይካድራ ላይ የፈፀመው አፀፋዊ ምላሽ በትግራይ ህዝብ ላይ እንዲፈፀም ታስቦ ነበር። በትልቅ ታጋሽነት ወንጀሉን ለአለም ማጋለጥ ተገቢ ነው። »ሲሉ ቀደም ሲል በማይካድራ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ በማውገዝ ሃሳባቸውን አካፍለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለውን መጠነ ሰፊ ጦርነት አስመልክቶ ሊመክርበት ከተሰባሰበ በኋላ ተበትኗል። ምክንያቱ ደግሞ የአፍሪካ ህብረት እና አፍሪካን ወክለው በምክር ቤቱ ተለዋጭ አባል የሆኑ ሀገራት በአፍሪቃ ሕብረት በኩል የተጀመረው መፍትሔ የማፈላለግ ጥረት የተሻለ አማራጭ ሆኖ በመገኘቱ ነው ተብሏል። ባለፈው ማክሰኞ ምሽት የተሰባሰቡት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት አባል ሀገራት የአፍሪካ ህብረት ለሚልካቸው የልዑካን ቡድን ድጋፋቸውን መስጠታቸው ተዘግቧል። የልዑካን ቡድኑ ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ምሽት አዲስ አበባ ደርሰዋል። ዛሬ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ጋር ተገናኝተው መምከራቸውም ተዘግቧል። የልዑካን ቡድኑ ስለ ድርድር ያነሱት ሃሳብ ይኑር አይኑር ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም። የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ የላኳቸው የልዑካን ቡድኑ  ሁለቱን ወገኖች የማሸማገል ተልዕኮ እንዳላቸው ቢነገርም የኢትዮጵያ መንግስት ቀደም ከሕወሓት ጋር እንደማይደራደር አቋሙን ግልጽ አድርጓል። ይህንኑ ተከትሎም የተለያዩ ሃሳቦች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ተስተናግደዋል።
 የሱነህ ወልዴ የተባሉ አስተያየት ስች ባሰፈሩት መልዕክታቸው «ውጤት የሚኖረው መንግስትን ደግፎ ሕግ እንዲከበር እና ንጹሐን በዚህ ጦርነት እንዳይጎዱ ማገዝ ነው ። ከዚሕ ውጪ ከወንጀለኞች ጋር ድርድር ማድረግ ወንጀለኞች ሌላ ተጨማሪ ወንጀል እንዲፈፅሙ እድል መስጠት መሆኑን መረዳት እና ማወቅ አለብን ።» ብለዋል።
 አሸናፊ ግዛቱ ጋቲሶ በበኩላቸው «የአፍሪቃ ሕብረት ግን ማንን ከማን ጋር ነው ማደራደር የሚፈልገው?  አንድን ክልል ከሉዓላዊት ሀገር ጋር የማደራደር ጉዳይ የሥራ አካል መሆንስ ይችላል ወይ ?በሀገሪቱ የሕዝብ ተወካዮችና ፌዴሬሽ ምክር ቤቶች አሸባሪ ከተባለው ቡድን ጋር እንዴት መንግሥትን ላደራድር ይባላል? » በማለት ጠይቀዋል። 
ጂራታ ጂራ የተባሉ ሌላው አስተያየት ሰጭ ደግሞ « ጦርነቱ ምንም ያህል ጊዜ ቢወስድ ዓላማው ሰላም ለማምጣት መሆን አለበት። የተራዘመ ጊዜ ወስዶ  አስከፊ ዋጋ ከተከፈለበት በኋላ ከሚገኘው ሰላም ይልቅ ውጥረቱን አርግቦ የሚገኘው ሰላም ሚዛን ያነሳል እና በዚሁ መንገድ ቢታሰብበት መልካም ነው» ሲሉ  ሃሳባቸውን አጋርተዋል።
በቀለ ወልደ ሚካኤል ደግሞ እንዲህ የሚል መልዕክት አስፍረዋል።«አትዮጵያ ለራሷዋ የውስጥ ጉዳይ ከፈጣሪ በታች የቤት ሥራዋን እስከምትጨርስ የሌሎች ጣልቃ የሚገቡትንም ሆነ ሀሳባቸውን እንደማትቀባል የአትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ፅኑ አቋም መሆን አለበት ። » ብለዋል። 
እሸቱ አያሌው በጦርነቱ ያደረባቸውን ስጋት ሲገልጹ «አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በፍጥነት መፍትሔ ካላገኘ በቀጣዩ ትውልድ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቀላል እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል » ይላሉ ። እሸቱ አያይዘውም ከዓመታት በፊት በዩጎዝላቪያ እንደቀልድ ተጀምሮ የነበረው ጦርነት እንዴት ወደ እርስ በእርስ እንደተሸጋገረ እና ያስከፈለውን ዋጋ እናስታውሳለን፤ አላስፈላጊ ውግያዎችን ማስቀረት ካልቻልን መጪው ጊዜ የአደባባይ ሚስጢር ይሆንብናል»  ሲሉ ስጋታቸውን አካፍለዋል። 
አሳየ ጋሹ በበኩላቸው « ድርድር?» በማለት ጥያቄውን በመንቀፍ ባሰፈሩት አስተያየታቸው « አይ እምየ ኢትዮጵያ ያ ያለቀስሽው እንባ ሳይደርቅ ሌላ እንባ?ፈጣሪ ይድረስልሽ» ይድረስልሽ ብለዋል። በእርግጥ ነው ይህ አስከፊ ጊዜ አልፎ በመላው ኢትዮጵያ የሰላም አየር ይነፍስ ዘንድ ሰላም ወዳዶች መመኘታቸው አይቀርም ። እኛም ሰላም ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን እያልን የዕለቱን ዝግጅት እንቋጭ ። 

UN-Sondersession zum 75. Geburtstag
ምስል Mike Segar/Reuters
Äthiopien | Premierminister | Abiy Ahmed Ali
ምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance
Tigray-Konflikt | Äthiopisches Militär
ምስል Ethiopian News Agency/AP/picture alliance
Äthiopien Pressekonferenz Tigray Defense Forces, Gebre Gebretsdik
ምስል Million Haileselassie/DW
Äthiopien Tigray Konflikt Flüchtlinge
ምስል Mohamed Nureldin Abdallah/Reuters


ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ