1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለምዕራብ ጉጂ ዞንና ጌዲዎ የአስቸኳይ ርዳታ ጥሪ

ዓርብ፣ ሐምሌ 20 2010

በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ጉጂ ዞን የኦሮሞ እና የጌዲዎ ተወላጆች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት ለተፈናቀሉ ወገኖች መርጃ ከ22 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግ ዓለም ዓቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት «IOM» ባወጣዉ መግለጫ አስታወቀ።

https://p.dw.com/p/32Cz0
IOM hat einen Appell für 22.200.000 USD gestartet, um auf die Vertreibungskrise in den Gedeo- und West-Guji-Zonen in Südäthiopien zu reagieren
ምስል Fana Broadcasting Corporate/EBC

ተፈናቃዮቹ የአስቸኳይ ርዳታ ያስፈልጋቸዋል

እንደ መግለጫዉ ከያዝነዉ ዓመት ሚያዝያ ወር ጀምሮ ከአካባቢዉ ላይ ወደ 970 ሺህ ሕዝብ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎአል።  በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂና በደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን አዋሳኝ ቦታዎች ላይ በኦሮሞ እና በጌዲኦ ተወላጆች መካከል ተከስቶ በነበረዉ ግጭት ሳቢያ ከአካባቢዉ  ለተፈናቀሉ ሰዎች  22,2 ሚሊዮን ደላር የአስቸኳይ ርዳታ እንደሚያስፈልግ  ዓለም ዓቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት በምህፃሩ IOM  ለዓለማቀፉ ማኅበረሰብ በያዝነዉ ሳምንት አጋማሽ ላይ ጥሪዉን አስተላልፎአል። ድርጅቱ ይፋ ባደረገዉ መረጃ መሰረት በአጭር ወራት ጊዜ ዉስጥ በምዕራብ  ጉጂና ጌዲኦ መሃል ላይ በተከሰተ ግጭት ወደ 970 ሺህ ኢትዮጵያዉያን ተፈናቅዋል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ በኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት «IOM» የኮሙኒኬሽንስ ጉዳይ ባለሞያ አቶ አለማየሁ ሠይፈስላሴ እንደገለፁት ተፈናቃዮቹ የብርድ ልብስና የመሳሰሉ ቁሳቁሶች ርዳታን በአስቸኳይ ይሻሉ።

«በተከሰተዉ ግጭት ምክንያት ነዉ ወደ 970 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያዉያን የተፈናቀሉት። ይህን ያህል ሰዉ የተፈናቀለዉ ምዕራብ ጉጂና በደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን መሃል ላይ በተከሰተዉ ግጭት ነዉ። ይህ ሕዝብ የተፈናቀለዉ በአጭር ወራት ዉስጥ ስለሆነ፤ እነዚህን ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸዉ ከመመለሳቸዉ በፊት በሚቆዩበት ጣብያ ላይ፤ የተወሰነ ርዳታ እንዲደረግላቸዉ ፤ለምሳሌ የሚለብሱት ብርድልስ የላቸዉም የሚተኙበት ፍራሽም የላቸዉም፤ ልብስም ምግብም የምግብ ማብሰያ ቁሳቁሶችም ስለሌላቸዉ እንዚህን ነገሮች አሟልቶ ለማቅረብ ነዉ ርዳታዉ የተጠየቀዉ።»   

በርካታዉ ተፈናቃይ በአዋሳኝ አካባቢ ከሚገኙ ነዋሪዎች ጋር መጠላላቸዉን የሚያሳየዉ የድርጅቱ መግለጫ፤ ሌሎች አካባቢዉ ላይ በሚገኙ ትምህርት ቤት ቤቶች፤ አጥር ባላቸዉ ተቋማትና በተጀመሩ ሕንጻዎች ዉስጥ ተጠልለዉ እንደሚገኙ ያሳያል።  መንግሥት ለተፈናቃዮች መጠለያ የሚሆን ነገሮችንም አመቻችቶአል ሲሉ አቶ ሰይፈ ስላሴ አክለዋል። 

«በዋነኝነት ለተፈናቃዮች መቆያ እንዲሆናቸዉ መንግሥት ራሱ ለዜጎቹ የመንግሥት ተቋማት የነበሩ ቦታዎችንና ቤቶችን አመቻችቶ ነዉ ለጊዜዉም ቢሆን መጠላያ የሰጠዉ። ግን አካባቢዉ መሰረታዊ የሆኑ ነገሮች የተሟሉበት ስላልሆነ ቦታዉ ላይ ብዙ ሺህ ሕዝብ ለማስተናድ በጣም ከባድ ነዉ። በዚህም የዉጭ ሃገር ርዳታ ወይም የለጋሽ ሃገራት ርዳታዎች ፤ ወይም በጎ አድራጎት ላይ የሚሠሩ አካላቶች ጋር ጥያቄ ማቅረብ አስፈላጊ ይሆናል። ይህ አይነት ሁኔታ በእና ሃገር ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ሃገራት ሲከሰት ፤ ሃገር ዉስጥ የሚፈናቀሉ ሰዎች ላይ መልሶ የሚሰሩ ድርጅቶች ማለትም እንደና አይነት ድርጅቶች ናቸዉ ጥያቄ ቀርቦላቸዉ ሰዎችን በተቻለ መጠን ለማቋቋም የሚረዱት ። እና መንግሥት እንድናግዝ ጠርቶናል እኛም ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመሆን ነዉ እየሰራን ያለነዉ።

እንደ አቶ አለማየዉ ሰይፈ ስላሴ ተፈናቃዮቹ በሚገኙበት አካባቢ በቂ የሆነ የጤና ጥበቃ መከታተያ ሆስፒታልም ሆነ ክሊኒክ ባለመኖሩ ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ይህን ችግር ለመቅረፍና ለተፈናቃዮቹ የተሟላ ግልጋሎት ለመስጠት እየሰራ መሆኑንም ሀላፊዉ ተናግረዋል።

« በኛ ሆነ በመንግሥት በኩል የጤና ጣብያዎችን በማቋቋም ቦታዎችን በማመቻቸት ረገድ የተሰሩ ስራዎች አሉ። በኛ በኩል ተፈናቃዮቹ ምን እንደሚያስፈልጋቸዉ ፤ ቦታዉ ላይ ሄደን ካየን በኋላ ነዉ ርዳታ ያስፈልጋል ብለን ነዉ ይህን ጥሪ ያቀረብነዉ። ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ «ዩኬ ኤድ» የሚባል ድርጅት  100 ቶን የሚያህል የርዳታ የተለያዩ ቁሳቁሶች ገቢ እንዲደረጉ ተደርጓል። ብርድልብስ ፤ መጠለያ ላስቲኮች የመሳሰሉ ቁሳቁሶች ይገኙበታል። አሁን ይህን ነገር ለማሰራጨት እየሰራን ነዉ።»

ተፈናቃዮቹን ወደመጡበት የመመለስ ጥረትስ አለ? ቦታዉ ላይስ ግጭቱ ቆሞአል?

«በመንግሥት በኩል ጥረቶች እየተደረጉ ነዉ። ግን አካባቢዉ ላይ ሰላም ወርዱዋል ሲባል መንግሥት በሚያደርገዉ ዉሳኔ ነዉ ይህ የሚወሰነዉ ፤አሁን የሚታወቅ ነገር የለም። እና ያናገርናቸዉ ሰዎች በፊት የተፈናቀሉ ስለሆኑ ፤ ባለፉት ወራት ዉስጥ ከባድ ሁኔታ አሳልፈዉ እንደመጡ ብቻ ነዉ የነገሩን። አሁን ያለዉን ሁኔታ መንግሥት ነዉ ጉዳዩን አረጋግጦ መወሰንና መረጃዉን መግለጽ የሚችለዉ።»

 

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ