1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለ12ኛ ክልል ሕዝበ ውሳኔ እንዲካኼድ ተወሰነ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 12 2014

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በደቡብ ክልል ሥር የነበሩ 6 ዞኖችና 5 ልዩ ወረዳዎች የፌዴራል ሪፖብሊኩ 12ኛ ክልል ሆነው ለመደራጀት የሚያስችላቸውን ሕዝበ ውሳኔ እንዲያካሄዱ ወሰነ። የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ዛሬ ያሳለፈው ውሳኔ በዎላይታና በጉራጌ ፖለቲከኞች ዘንድ የተለያዩ ሥሜቶችን እያስተናገደ ይገኛል።

https://p.dw.com/p/4Fise
House of federation, Addis Abeba, Ethiopia
ምስል House of federation Ethiopia

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ወስኗል

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በደቡብ ክልል ሥር የነበሩ 6 ዞኖችና 5 ልዩ ወረዳዎች የፌዴራል ሪፖፕሊኩ 12ኛ ክልል ሆነው ለመደራጀት የሚያስችላቸውን ሕዝበ ውሳኔ እንዲያካሄዱ ወሰነ። ምክር ቤቱ ወሳኔውን ያሳለፈው ዛሬ ባካሄደው 6ኛ የፓርላማ ዘመን ፣ 1ኛ አስቸኳይ ጉባኤው ቀደምሲል በዞኖቹና በልዩ ወረዳዎቹ የቀረበውን በጋራ የአንደራጅ ጥያቄን ከመረመረ በኋላ ነው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ዛሬ ያሳለፈው ውሳኔ በዎላይታና በጉራጌ ፖለቲከኞች ዘንድ የተለያዩ ሥሜቶችን እያስተናገደ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ዛሬ ምክር ቤቱ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በጉራጌ ዞን የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉን የክልሉ ኮማንድ ፖስት አስታውቋል፡፡

የፌዴሬሽን ም/ቤት ዛሬ ባካሄደው 6ኛ የፖርላማ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ጉባኤው በደቡብ ክልል በሚገኙ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በቀረበው የአደረጃጀት ጥያቄዎች ላይ በመምከር ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ም/ቤቱ በክልሉ የሚገኙ 6 ዞኖችና 5 ልዩ ወረዳዎች አንድ የጋራ ክልል ለመመሥረት ያቀረቡትን ጥያቄ በአብላጫ ድምጽ ተቀብሎ አጽድቆታል፡፡

በአንድ ክልል ሆነው እንዲደራጁ የተወሰነላቸው የወላይታ ፣ የጋሞ ፣ ጎፋ ፣ ደቡብ ኦሞ ፣ ጌዲኦና ኮንሶ ዞኖችና እንዲሁም የአማሮ ፣ ቡርጂ ፣ ደራሼ ፣አሌና የባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድም በሦስት ወራት ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ በማደራጀት እንዲያስፈጽም ውሳኔ መተላለፉንም የም/ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ተፈራ በዳዳ ለዶቼ ቬለ DW በስልክ ገልፀዋል፡፡ ቀሪዎቹ የሀድያ ፣ ሀላባ ፣ ከንባታ ጠንባሮ ፣ ጉራጌ ፣ ሥልጤ ዞኖችና የም ልዩ ወረዳ  ደግሞ በነባሩ ክልል እንዲቀጥሉ ም/ቤቱ መወሰኑንም ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

House of federation, Addis Abeba, Ethiopia
ምስል House of federation Ethiopia

የዛሬው የፌዴሬሽን ም/ቤት ውሳኔ በወላይታና በጉራጌ ፖለቲከኞች ዘንድ የተለያዩ ስሜቶችን አስተናግዷል፡፡ የአደረጃጀት ጥያቄው በሕዝበ ውሳኔ ምላሽ ይሰጠው የሚል አቋም ሲያራምድ የቆየው የዎላይታ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ግንባር / ዎሕዴግ / ‹‹ ህዝበ ወሳኔ ይካሄድ ›› የሚለውን የፌዴሬሽኑን ውሳኔ እንደሚቀበለው አስታውቋል፡፡ የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ጎበዜ ጉአ እንዳሉት በሚካሄደው ሕዝብ ውሳኔ አማራጭ ውስጥ ሊካተቱ ይገባል ያሏቸውን ነጥቦች ለዶቼ ቬለ DW ገልፀዋል፡፡ ሕዝበ ውሳኔ ማካሄድ በራሱ ችግር የለውም ያሉት የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ጎበዜ ‹‹ ነገር ግን ለውሳኔው የሚቀርቡ አማራጮች ውስጥ ‹‹ የወላይታ ክልል ›› የሚል ሶስተኛ አማራጭ መግባት ይኖርበታል፡፡ ሁለት አማራጮች ብቻ ከሆኑ ገዢው ፖርቲ ባስቀመጣቸው አማራጮች ላይ ብቻ መወሰን ነው የሚሆነው ፡፡ ይህ ዲሞክራሲያዊ አካሄድ አይደለም፡፡ ሁሉም አማራጮች ለውሳኔ ይቅረቡና በእኛ በኩል ሕዝብ የመረጠውን እንቀበላለን ›› ብለዋል፡፡

ዶቼ ቬለ DW በፌዴሬሽን ም/ቤቱ ውሳኔ ላይ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው ሌላው የጉራጌ ዞን ም/ቤት አባል አቶ አንተነህ ተስፋዬ ም/ቤቱ የጉራጌን የክልልነት ጠያቄ በቀጥታ ከመመለስ ይልቅ በቋንቋ ለማለዘብ ሞክሯል ብለዋል፡፡ የጉራጌ ሕዝብ ራሱን በቻለ ክልል መደራጀት እንደሚፈልግ አስቀድሞ አሳውቋል ያሉት አቶ አንተነህ ‹‹ ም/ቤቱ ሕዝበ ውሳኔ ቢካሄድ ከዚህ  የተለየ ውሳኔ እንደማይኖረው የተረዳው ይመስለኛል፡፡ በዚህ መነሻ ጉራጌ በነባሩ ክልል ይቀጥል በሚል የወሰነው የቋንቋ ልዩነት ካልሆነ በስተቀር ያው ክላስተር ማለት ነው፡፡ በእኛ በኩል ጥያቄአችንን አሁንም  የምንቀጥል ነው  የሚሆነው ›› ብለዋል፡፡

የፌዴሬሽን ም/ቤት ዛሬ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በጉራጌ ዞን የእንቅሰቃሴዎች ገደብ መጣሉን የክልሉ ኮማንድ ፖስት አስታውቋል፡፡ ኮማንድ ፖስቱ ዛሬ ባወጣው መግላጫ በዞኑ ከዛሬ ጀምሮ ማናቸውንም ሰልፍ መሰል እንቅስቃሴዎች ማድረግ የተከለከለ ነው ብሏል፡፡ እንዲሁም ባለሁለት እግር ሞተር ሳይክል እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ፣ ባለ ሶስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪዎች ደግሞ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ብቻ እንዲንቀሳቀሱ መወሰኑንም ኮማንድ ፖስቱ በመግለጫው ጠቅሷል፡፡ በተጨማሪም የንግድ ሱቆችና የመንግሥት ተቋማትን መዝጋት የተከለከለ መሆኑንም በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ፎቶ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የተወሰደ

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ