ህወሓት በኢህአዴግ ዉሕደት አቋሙን ለመግለፅ ጉባኤ ሊቀመጥ ነዉ
ሰኞ፣ ኅዳር 15 2012የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል እንዳሉት ህወሓት ከሁለት ሳምንት በፊት በተደረገው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይ የውህድ ፓርቲ ጉዳይ አጀንዳ እንዲሆን አልፈለገም ነበር፡፡ የሀገሪቱ ሰላም፣ ኑሮ ውድነት፣ የሚስተዋለው የሕግ ጥሰትና መጪው ሀገራዊ ምርጫ ጉዳዮች የስብሰባው አጀንዳ እንዲሆኑ በህወሓት በኩል ግፊት መደረጉ የጠቆሙት ዶክተር ደብረፅዮን ይሁንና በአብላጫ ድምፅ ኢህአዴግን የማዋሃድ ጉዳይ ለውይይት እንዲቀርብ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ኢህአዴግን ውሁድ ፓርቲ እንዲሆን እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ በርካታ የሕግና የግንባሩ መተዳደሪያ ደንብ ጥሰቶች ያሉበት ያሉት የህወሓት መሪ ዶክተር ደብረፅዮን "አካሄዱ ኢህአዴግን ውሁድ ፓርቲ ማድረግ ሳይሆን በስመ ውህደት አዲስ ፓርቲ የመፍጠር ነው" ብለውታል፡፡
በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይ የተሳተፉ 7 የህወሓት ስራ አስፈፃሚ አባላት ውህደቱን እንደተቃወሙ የተናገሩት ሊቀ መንበሩ በኢህአዴግ በኩል 6 ተብሎ የተጠቀሰው ስህተት ነበር ብለዋል፡፡
ከውሳኔው በኋላ ከኢህአዴግ ሊቀ መንበር ዶክተር አብይ አሕመድ ጋር ውይይት ተደርጎ "የውህደት አጀንዳው ደግመን እንድናየው ጥያቄ ቀርቦልን ነበር" የሚሉት ዶክተር ደብረፅዮን በህወሓት በኩል ግን የአቋም ለውጥ እንደሌለ ጠቁመዋል፡፡
እንደ ዶክተር ደብረፅዮን ገለፃ ሂደቱ 'ውህደት' ሳይሆን አዲስ ፓርቲ የማቋቋም ስራ ነው ብለውታል፡፡ በተጨማሪም አጋር ተብለው የሚታወቁት ፓርቲዎች በውህደት አጀንዳው ዙርያ አስቀድመው እንዲፈርሙ መደረጉም ጠቅሰዋል፡፡
የግንባሩ ውህደት ጉዳይ የህወሓት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴና ማእከላይ ኮሚቴው እንዳልተቀበለው የጠቀሱት የፓርቲው ሊቀ መንበር አጀንዳው የመጨረሻ ውሳኔ የሚያገኘው ግን በህወሓት ጉባኤ መሆኑ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ህወሓት አስቸኳይ ጉባኤ ለማድረግ ውሳኔ ማስተላለፉ ተጠቁሟል፡፡
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
አዜብ ታደሰ
ተስፋለም ወልደየስ