1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ህወሓት ለባሕር ዳርና ጎንደር ፍንዳታዎች ኃላፊነት ወሰደ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 5 2013

በባህርዳር እና ጎንደር ከተማ ትናንት ምሽት ለተፈጸሙት የሮኬት ጥቃቶች ሕወሃት ኃላፊነቱን መውሰዱንም ዐስታውቋል። ቀደም ሲል መንግስት ጥቃቱን የፈፀመው ሕወሓት እንደኾነ ገልጦ ነበር። ስለትናንት ምሽቱ ፍንዳታ የባህር ዳሩ ወኪላችን ዓለምነው መኮንን ከመንግሥት አካላት ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

https://p.dw.com/p/3lIkL
Äthiopien Bahirdar Covid19
ምስል DW/A. Mekonnen

ለተፈጸሙት የሮኬት ጥቃቶች ሕወሃት ኃላፊነቱን መውሰዱንም ዐስታውቋል

በባህርዳር እና ጎንደር ከተማ ትናንት ምሽት ለተፈጸሙት የሮኬት ጥቃቶች ሕወሃት ኃላፊነቱን መውሰዱንም ዐስታውቋል። ቀደም ሲል መንግስት ጥቃቱን የፈፀመው ሕወሓት እንደኾነ ገልጦ ነበር። ስለትናንት ምሽቱ ፍንዳታ የባህር ዳሩ ወኪላችን ዓለምነው መኮንን ከመንግሥት አካላት ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም። ኾኖም የባህር ዳር ነዋሪዎችን አነጋግሮ ቀጣዩን  ዘገባ ልኮልናል።  

የምሽቱን ጥቃት በተመለከተ አንድ የባህር ዳር ነዋሪ ብርቱ እንደነበረ ተናግረዋል፡፡ የጎንደሩ ነዋሪ እንዳሉት ደግሞ 3 ፍንዳታዎች እንደነበሩና አንዱ ሮኬት 3 ጊዜ ሲፈነዳ መስማታቸውን አብራርተዋል፡፡ ፍንዳታው እስከ 20 ኪሎሜትር ድረስ የመንቀትቀጥ ሁኔታ እንደነበር አመልክተዋል። ከዚህ የበለጠ ሌላ ጥቃት ሊኖር ስለሚችል ህብረተሰቡ ከመደናገጥ ይልቅ ራሱን መጠበቅ እንዳለበት ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የተናገሩት፡፡ 

ፍንዳታው ያስከተለውን ጉዳት ለማወቅ የሚመለከታቸውን የክልል ባለስልጣናት ለማነጋገር ብንሞክርም ስልካቸው አይነሳም፡፡ ሆኖም የአማራ ቴሌቪዥን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያን ጠቅሶ እንደዘገበው ትናንት ምሽት ወደ ባሕር ዳርና ጎንደር ሮኬት መተኮሳቸውንና በዚህም በአውሮፕላን ማረፊያው አካባቢ መጠነኛ ጉዳት መድረሱን ገልጧል፡ መረጃ ማጣሪያው “ስግብግቡ ጁንታ” ብሎ የጠራው ህወሓት በእጁ ያሉትን የመጨረሻዎቹን መሳሪያዎች ጠጋግኖ ሞክሯልም ብሏል፡፡ ይህም ከመሞቱ በፊት የመጨሻውን አቅሙን እየሞከረ መሆኑን ያመለክታል ሲል አመልክቷል፡፡ ዝርዝሩን መርማሪ ቡድን ተመድቦ እያጣራው ሲሆን በቀጣይ የሚገለፅ መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ ማሳወቁን ቴሌቪዥን ጣቢያው ዘግቧል፡፡ 
የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ የክልሉ መንግስት በሚቆጣጠረው የቴሌቪዥን ጣቢያ ጥቃቱን ህወሓት እንደፈፀመው ገልፀዋል፡፡ 

ዓለምነው መኮንን
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ልደት አበበ