1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሃይማኖት በስድስተኛው አገር ዐቀፍ ምርጫ

ዓርብ፣ መጋቢት 17 2013

ቤተ መንግሥቱ ፖለቲካዊ ብሔርተኝነትን በሚያበረታታባቸው ጊዜያት ፖለቲካዊ ብሔርተኝነት ከሚገባው በላይ አንሰራርቶ አሁን ላለንባቸው ግጭቶች የበኩሉን አስተዋፅዖ አድርጓል። አሁን ደግሞ ቤተ መንግሥቱ ፖለቲካዊ ሃይማኖተኝነትን በሚያበረታታበት ወቅት ፖለቲካዊ ሃይማኖተኝነት እያቆጠቆጠ ነው።

https://p.dw.com/p/3rDQn
180621 Kolumne BefeQadu Z Hailu

በፍቃዱ ኃይሉ

ሃይማኖትና መንግሥት በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 27 የተነጣጠሉ ናቸው። አንዳቸው በሌላኛቸው የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አይገቡም። ነገር ግን ፖለቲካው በውስጠ ታዋቂነት ሃይማኖታዊ ትግልም አለው። ይህ ስርዓት ሴኩላሪዝም ይባላል።

አንዳንድ ሰዎች ዜጎች ሃይማኖታቸውን ከፍተኛ ዋጋ በሚሰጡበት አገር ውስጥ ሃይማኖት ከፖለቲካ ስርዓቱ መገለሉ አግባብ አይደለም እያሉ ሲከራከሩ ነበር። በዘንድሮው ምርጫ የፖለቲካ ድርጅት ሆነው የተመሳሳይ ሃይማኖተኞች መሰባሰቢያ የመሰሉ ድርጅቶች እየተከሰቱ ነው። በሌላ በኩል በፊትም ቢሆን የፖለቲካ ድርጅቶች ስለሃይማኖት አያወሩም እንጂ የአንድ እምነት መሰባሰቢያ ነበሩ ይባላል። ይህ አዝማሚያ ፖለቲካው ለሃይማኖት በር እየከፈተ ይሆን ያሰኛል።

በጥቅምት ወር 2012፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "መደመር" የተባለውን መጽሐፋቸውን በሚሊኔየም አዳራሽ ባስመረቁበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ላይ ፈጣሪ ‘ኢትዮጵያን እንደማይጥል’ ከተናገሩ በኋላ፣ "በተደጋጋሚ ፈጣሪ ስንል ሰዎች ይገረማሉ፤ እኛ በማርክ[ስ] እና በሌኒን የእውር አስተሳሰብ የታጠብን ስላልሆንን፣ የፈጣሪን ልዕልና የምናምን ስለሆንን፣ በዚያም የማናፍር መሆናችንን፣ 99 ፐርሰንት አማኝ ያለበት አገር መሪ ሆኖ፣ እምነትን ማራከስ ሕዝብን አለማወቅ ስለሆነ ፈጣሪ ዛሬም ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ" ብለዋል። ይሄ ንግግራቸው በሴኩላሪዝም ለማያምኑ ሰዎች አነቃቂ ሳይሆን አይቀርም።

ጄፍ ሃይንስ የተባሉ ተመራማሪ ስለሃይማኖት እና "ሦስተኛው ዓለም" በሚያወሩበት መጽሐፋቸው መንግሥታት ሃይማኖትን እንዴት እንደሚጠቀሙበት ያስረዳሉ። ይኸውም አገዛዛቸውን ለማስቀጠል፣ ቅቡልነት ለማግኘት፣ ሥልጣናቸውን ተቋማዊ ለማድረግ እና አልፎ ተርፎም ለዜግነት እንደ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ነው።

የሃይማኖት ከቤተ መንግሥት መውጣት

ሃይማኖትና መንግሥት መቀላቀላቸው ሥልጣንን ከማፅናትም ባሻገር ከፍተኛ የጭቆና መሣሪያ ሊሆን እንደሚችል ከኢትዮጵያውያን በላይ ምሥክር የለውም። የኢትዮጵያ ዐፄያዊ አገዛዞች መንግሥታዊ ሃይማኖቶች ነበሯቸው። የመጀመሪያዎቹ ሁለት የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥቶችም የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነትን መንግሥታዊ ሃይማኖት አድርገውት ነበር። የንጉሠ ነገሥቱ ሥልጣን የሚደፈርበት ብቸኛው ምክንያት ሃይማኖታቸውን ከቀየሩ ወይም የሌላ እምነት ተከታይ ጋር በትዳር ከተጣመሩ ነበር።

ይህ መንግሥታዊ ማግለል ለ1966ቱ አብዮት አንድ ምክንያት እንደነበር ብዙ ተጽፎበታል። በዐፄያዊው አገዛዝ የተተካው ደርግ ደግሞ በወቅቱ ፋሽን የነበረውን ማርክሲዝም-ሌኒኒዝም ርዕዮተ ዓለማዊ ቀኖና አድርጎ ተቀበለ። የሃይማኖት እና መንግሥት መነጣጠልንም አበሰረ። ሆኖም ይህ ድርጊት ሃይማኖተኝነትን ከፖለቲከኞች ውስጥ ማስወጣት እንደሆነ አድርገው ያሰቡት ሰዎች አሉ። ለዚህ ከላይ የተጠቀሰው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ንግግር ዋቢ ሊሆን ይችላል። እርሳቸውም ግን ብቻቸውን አይደሉም።

ሃይማኖትን ወደ ቤተ መንግሥት ለመመለስ…

በስድስተኛው አገር ዐቀፍ ምርጫ የእናት ፓርቲ ሦስተኛው ትልቅ ተወዳዳሪ ሆኖ መውጣቱ ለብዙዎች አስገራሚ ሆኖባቸዋል። ይህ ፓርቲ ማነው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ጋዜጠኞች ሲሯሯጡ ፓርቲው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ተቋማትን ተክትሎ ነው የተዋቀረው የሚል ወሬ ተሰማ። የፓርቲው ምክትል ሊቀ መንበር ከኢትዮጵያ ኢንሳይደር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ይህንን ቢክዱም፣ ካሕናትና ዲያቆናትን ለምርጫ ውድድር ማሰለፋቸውን ተናግረዋል። በተጨማሪም፣ ባለፉት 45 ዓመታት ኢትዮጵያ በሃይማኖት የለሽ ፖለቲከኞች በመመራቷ አሁን ላለችበት ችግር ተዳርጋለች ብለው እንደሚያምኑ አመልክተዋል። በሕገ መንግሥቱ ስለተከለከለው የሃይማኖት እና መንግሥት አንዳቸው በሌላኛቸው ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት ጉዳይ ሲጠየቁ፣ ሕገ መንግሥቱ በብዙ መንግዶች ተጥሷል በማለት ይህንኛውም መጣሱ እንደማያሳስባቸው በገደምዳሜ አመላክተዋል።

እናት ፓርቲ ብቸኛው ሃይማኖተኝነትን መሠረት ያደረገ ፓርቲ አይደለም። ነፃነትና እኩልነት ፓርቲም (ነእፓ) ማኅበራዊ መሠረቱ ሙስሊሞች ናቸው እየተባለ ይወራበታል። ከተለመደው ውጪ በርካታ ሙስሊም አመራሮች ይዟል፤ ነገር ግን ይሄ ብቻውን ለዳኝነት ያስቸግራል። ምክንያቱም ሁሉም መሪዎቻቸው ክርስቲያኖች ብቻ የሆኑ በርካታ ፓርቲዎች አሉ። ነገር ግን የክርስቲያን ፓርቲዎች አይባሉም። ነገር ግን ሙስጠፋ አብደላ የተባለ ሰው ፌስቡክ ላይ ያሰፈረውና በሰፊው ተሰራጭቶ የነበረ ጽሑፍ በውስጠ ታዋቂነት ያለውን ግንዛቤ ያስጨብጣል። ጽሐፊው ነእፓን የደገፈበትን ምክንያት ሲገልጽ “…የአማራ ክልል ብልፅግናም ሆነ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች የክልል ምክር ቤት እና የተወካዮች ምክር ቤት ተመራጭ ዕጩዎችን ከማስመዝገብ ጀምሮ ይሁን ከዚያ በፊት በተለያዩ ሚዲያዎችና መድረኮች ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በኢስላም እና በሙስሊም ላይ መገፋት ነበር ብየ ስለማስብ እና ለዚህ ድምፅ ሊሆን ይችላል በሚል ነው” በማለት ምክንያቱ ሃይማኖታዊ እንደሆነ ገልጿል። በማከልም “ሙስሊም ሰብሰብ ሲል ዓይናቸው የሚቀላ፣ ሙስሊሙን በአሻጥር በማግለል የፖለቲካ ቁማር እየተቆመረ ባለበት በዚህ ወቅት ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲን መደገፍ የወቅቱን የአገራችንን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሚዛን ያስጠብቃል ብየ ስለማስብ ነው…” የሚል መልዕክት አስተላልፏል።

ገዢው ብልፅግና ፓርቲም በጠቅላይ ሚኒስትሩ አጠራር ‘በጣም ብዝኃነት’ የሚታይበት ቢሆንም ቅሉ፥ ከሥያሜው ጀምሮ የፕሮቴስታንት እምነት ተፅዕኖ እንዳለበት ሲተች ከርሟል።

እምነትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ጫወታ የሚጫወቱ ድርጅቶች ምክንያታቸው ያለፈው መንግሥታዊ ድጋፋቸውን ማስመለስም ይሁን፣ ያልነበረውን መንግሥታዊ ድጋፍ ለማግኘት ቤተ መንግሥቱን ወደ ቤተ መቅደስነት ለመቀየር የሚደረገው ሙከራ ጥሩ ውጤት አያመጣም።

ቤተ መንግሥቱ ፖለቲካዊ ብሔርተኝነትን በሚያበረታታባቸው ጊዜያት ፖለቲካዊ ብሔርተኝነት ከሚገባው በላይ አንሰራርቶ አሁን ላለንባቸው ግጭቶች የበኩሉን አስተዋፅዖ አድርጓል። አሁን ደግሞ ቤተ መንግሥቱ ፖለቲካዊ ሃይማኖተኝነትን በሚያበረታታበት ወቅት ፖለቲካዊ ሃይማኖተኝነት እያቆጠቆጠ ነው። ከፖለቲከኝነት ይልቅ በሃይማኖተኝነት የምናውቃቸው ሰዎች ወደ ፖለቲካው ገብተዋል። የግል ተወዳዳሪ ተብለው ሲገለጹ ከነበሩት ሰዎች ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪዎቹ የሃይማኖት መሪዎች ናቸው። በቅርቡ ያስተዋልናቸው ግጭቶች ውስጥ ሃይማኖት ከብሔር ቀጥሎ ቦታ እንደነበረው በበቂ ሁኔታ ተዘግቧል። ፖለቲካው እና ሃይማኖቶች በጥንቃቄ የታሰበበት ግንኙነት ካላደበሩ መጪው ጊዜ አደገኛ ነው። 

«በዚህ ሐተታ(ፅሁፍ)የቀረበው አስተያየት የፀሐፊው እንጂ የዶቼቬለ አይደለም።»