1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

MNLA ዘመቻው አበቃ አለ

ሐሙስ፣ መጋቢት 27 2004

ሰሜን ማሊን ከተቀረው ማሊ ለመገነጠል የሚታገለው የማሊ ብሔራዊ ነፃ አውጭ ጦር በእንግሊዘኛው ምህፃር MNLA አማፅያን በሰሜን ማሊ የተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ማብቃቱን አስታወቁ ። እንደ አማፅያኑ አዝዋርድ የሚል ስያሜ የሰጡትን ግዛት ለመመስረት

https://p.dw.com/p/14Yj8
ምስል Reuters

ሰሜን ማሊን ከተቀረው ማሊ ለመገነጠል የሚታገለው የማሊ ብሔራዊ ነፃ አውጭ ጦር በእንግሊዘኛው ምህፃር MNLA አማፅያን በሰሜን ማሊ የተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ማብቃቱን አስታወቁ ። እንደ አማፅያኑ አዝዋርድ የሚል ስያሜ የሰጡትን ግዛት ለመመስረት ያካሄዱት ትግል ግቡን በመምታቱ ውጊያ አብቅቷል ። MNLA በድረ ገፁ ትናንት በአገሩ ሰዓት አቆጣጠር እኩለ ለሊት ላይ ዘመቻው አብቅቷል ሲል መወሰኑን አስታውቋል ። ቡድኑ በዚሁ መግለጫው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአዝዋርድ ጥበቃ እንዲያደርግም ጠይቋል ። የአፍሪቃ ህብረትም ሆነ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰሜን ማሊን መገንጠል አይደግፍም ። ፈረንሳይ በቱአሬጎች ለሚመራው አመፅ መፍትሄው ፖለቲካዊ ድርድር ነው ስትል አስታውቃለች ። በአካባቢው በመስፋፋት ላይ ያለውን አልቃይዳን ለመዋጋት የአካባቢው ሃገሮች በትብብር እንዲንቀሳቀሱ ጠይቃለች ። በሌላም በኩል ፈረንሳይ በኃይል ሥልጣን የያዘውን ወታደራዊ ደርግ ለማስወገድ የአፍሪቃ ኃይሎችን ለመርዳት ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች ።

Mali Putsch Parteien lehnen Treffen mit Putschisten ab Treffen in Bamako
ምስል Reuters

የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አለን ዡፔ ሃገራቸው ለዚሁ ዓላማ ሎጂስቲካዊ እርዳታ እንደምትሰጥ ሆኖም ወደ ቀድሞ ቅኝ ግዛቷ ወታደሮቿን እንደማትልክ ተናግረዋል ። ይህ በእንዲህ እንዳለ በሰሜን ማሊው ግጭት ቁጥሩ ወደ 2 መቶ ሺህ የሚደርስ ህዝብ መፈናቀሉ ተዘግቧል ። ከአካባቢው የተፈናቀሉት እንደሚናገሩት ብዙ ጥፋት ደርሷል ።
« ብዙ ጥፋት ደርሷል ። እዚያ በአካል እስካልተገኙ ድረስ ሁኔታውን መረዳት አይቻልም ። ብዙ ሰዎች ሞተዋል ። ምግብ የለም ፤ እሌክትሬክ የለም ፣ ሌሎችም ብዙ ነገሮች የሉም ። መውጫ መንገድህን ፈልገህ እግዚአብሔርን ማመስገን ነው ። »
ወታደራዊው ደርግ ባማኮ ተረጋግታለች ቢልም በዚያም ቢሆን የፀጥታ ዋስትና አለመኖሩን ይሰማል ። የነዳጅ ዘይት ና የአንዳንድ ሸቀጦች እጥረት ተከስቷል ።

Mali Putsch Putschistenführer Hauptmann Amadou Haya Sanogo in Kati
ሻምበል አማዱ ሳኖጎምስል dapd

በሌላ በኩል ከ 2 ሳምንት በፊት በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዘው የማሊ ወታደራዊ ጁንታ የኃያላኑን ምዕራባውያን መንግሥታት እርዳታ ተማፀነ ። የጁንታው የበላይ ሻምበል አማዱ ሳኖጎ ለሞንድና ሊቤራስዮን ለተባሉት የፈረንሳይ ጋዜጦች በሰጡት ቃለ ምልልስ በቱአሬግ አማፅያን እጅ የወደቀውን ሰሜን ማሊን መልሶ ለመቆጣጠር የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ እገዛ እንደሚያሻቸው አስታወቀዋል ። ሳኖጎ ኃያላኑ መንግሥታት አክራሪዎችን ለመዋጋት ውቅያኖስ ተሻግረው አፍጋኒስታን ድረስ ጦር ማዝመት ከቻሉ እኛስ ጋ መምጣት ምን ያግዳቸዋል ሲሉም ተናገረዋል ። በዚሁ ቃለ ምልልስ ወታደራዊው ደርግ ለማሊ የተሻለው ሁሉ እንዲደርግ እንደሚፈልግም ያሳወቁት ሳኖጎ የሚታወቀው ጠላት ርዐስ ከተማ ባማኮ ስለሌለ ጣልቃ ገብነቱ በሰሜን ማሊ መሆን ይኖርበታልም ብለዋል ።

Mali Schlange vor Bank
ምስል Reuters

የውጭ ኃይላት የቱአሬግ አማጽያን ግስገሳ እንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል ። ያም ሆኖ ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ሳንጎን ለሥልጣን ያበቃውን የዛሬ 15 ቀንኑን መፈንቅለ መንግሥት አውግዟል ። ሳኖጎ በአሁኑ ጊዜ በባማኮ ህይወት እንደ ቀድሞው የቀጠለ መሆኑና ምንም ዓይነት ቀውስ እንደሌለ ፤ ወታደራዊው ደርግም አክብሮት እንደተቸረው ተናግረዋል ። በሰሜን ማሊ ግን ሁኔታው አንገብጋቢ መሆኑን አስረድተዋል ። ሻምበል ሳንጎ በሮች ሁሉ ለውይይት ክፍት መሆናቸውን አስታውቀው ሆኖም በማሊ ሉዓላዊነት ላይ ግን ምንም ዓይነት ድርድር እንደማያካሂዱ አስታወቀዋል ።