#MeToo፤ የፆታ ጥቃትን የሚነቅፈዉ ንቅናቄ  | ባህል | DW | 08.11.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

#MeToo፤ የፆታ ጥቃትን የሚነቅፈዉ ንቅናቄ 

በኢትዮጵያ «ሴት ንጉስ ትዉለድ ጳጳስ አይታወቅም እና ሴትን ማክበር ያስፈልጋል» የሚል የአነጋገር ብሂል አለ። በሴቶች ላይ የሚደርስን የፆታ ጥቃት ደብቆ ማሳለፉ የተለመደ ነዉ። እንደሚወራዉ በኢትዮጵያ ማኅበረሰቡም ሆነ ሚዲያዉ ቦታ የሚሰጠዉ ከሴት ይልቅ ለወንዶች ነዉ? ይህ አሸንፎ ለመዉጣት የሴቶች እንቅስቃሴ ምን መምሰል ይኖርበታል?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:50

«ከወንዶች ይልቅ ሴቶች በሴት ላይ የሚያሳርፉት በደል ይጤን»

በሃገራችን በኢትዮጵያ «ሴት ንጉስ ትዉለድ ጳጳስ አይታወቅም እና ሴትን ማክበር ያስፈልጋል» የሚል የአነጋገር ብሂል አለ። ሴትን የማክበር ባህል ከእናትነት፤ ከእህትነት፤ ከሩህሩህነት፤ ከጀግንነት ከመሳሰሉት ክንዉኖች ጋር የተያያዘ በመሆኑ የሥነ ማኅበረሰብ አጥኚዎች በተለይ ማኅበረሰቡ ክንዉኑን «ኢትዮጵያዊ ጨዋነት» ከሚለዉ መርህ ጋር የሚቆራኝ መሆኑን ይናገራሉ። ነገርን ነገር ያነሳዋል ነዉና በዛሬዉ መሰናዶዬ ባለፈዉ መስከረም ወር መጨረሻ አንድ ዓመት የሆነዉን እና በአሁኑ ወቅት በበርካታ ምዕራባዉያን ሃገራት ተግባራዊ ስላደረጉት #MeToo ስለተሰኘዉ የሴቶች መብት እንዲከበር ስለሚጠይቀዉ እንቅስቃሴ መሰናዶ ይዘናል።

#MeToo በሚል ስያሜ የሚታወቀዉ ንቅናቄ የዛሬ 12 ዓመት ግድም ታራና ቡርከ በተባለች የማህበረሰብ አደረጃጀት ጉዳይ ሠራተኛ እና የኅብረተሰብ ጉዳዮች ተቆርቋሪ ጥቁር አሜሪካዊት ነው። ታራና ይህን ንቅናቄ የጀመረችዉ በራስዋ ላይ በደረሰዉ ጥቃት እና በማኅበረሰቡ ላይ የምታየዉን ችግር ታሳቢ አድርጋ በራስዋ ተነሳሽነት እንደሆነም ተነግሮአል። ቆየት ብሎ ጥቁር አሜሪካዊትዋ የማኅበረሰብ ጉዳይ ተቆርቋሪ ታራና ታዋቂዉ አሜሪካዊ የፊልም ሥራ አዋቂ ሃርቪ ዋይንስቴን በሥራ ገበታ ላይ የሚያደርስዉን የፆታ ጥቃት በዚሁ #MeToo በተሰኘዉ ንቅናቄ ለአደባባይ ማብቃትዋ ጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠዉ ይገባል በሚል ንቅናቄዉ መጠናከሩ ይነገራል። 
ይሁንና  #MeToo የተሰኘዉ ንቅናቄ ባለፈዉ የጎርጎሮሳዉያን ዓመት ጥቅምት ወር በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከተሰራጨ በኋላ ዘመቻዉ በርግጥ በዝያዉ በሰሜን አሜሪካ የተለያዩ ተቋማት እና መስርያ ቤቶችን ጨምሮ በአዉሮጳም የበርካታ የመንግሥትና የግል መሥራያ ቤቶችን ቀልብ ስቦ ተግባራዊ መደረግ ጀምሮአል። የሴቶች እኩልነት በአንፃራዊ ክብር ያገኛል በሚባልበት በሰሜን አሜሪካም ይህ ንቅናቄ ጎልቶ እስኪወጣ እና ተግባራዊ እስኪደረግ ዓመታት አስቆጥርዋል፤ የምትለዉ ስለሠዉ ልጆች መብት የተለያዩ ዝግጅቶችን ለአድማጮች ጆሮ በማድረስዋ የምትታወቀዉ፤ የኢትዮ ዲያስፖራ ሬድዮ ዋና አዘጋጅ ቅድስት ተስፋዬ ወይም ቅድስት አቤኔዘር ናት። እንደ ቅድስት በሃገረ አሜሪካ ይህ ንቅናቄ ከተጀመረ በኋላ በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ ሴቶች ችግራቸዉን በአደባባይ አዉጥተዉ ተናግረዋል፤ እየተናገሩም ነዉ።    


 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ በንግግራቸዉ ሴቶችን ማክበራቸዉ ብሎም ኢትዮጵያዉያን ሴቶች ለሃገራቸዉ እንዲሰሩ ወደ ትልቅ ኃላፊነት ቦታ ማምጣታቸዉ የብዙዎችን ይሁንታ አገኝቶአል። የማኅበረሰብ ጉዳይ አዋቂዎችም እንደሚሉት ሴቶችን በዚህ ሁኔታ ማክበርና ለማኅበረሰቡን የግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅቶችን ካካሄድን ለሴቶች የምንሰጠዉ ክብር ከቃላት በዘለለ ተግባራዊ የማይሆንበት ነገር እንደሌለ ነዉ የሚናገሩት።  
 
በኢትዮጵያ የሴቶች ላይ የሚደርስን የፆታ ጥቃት ሸፍኖ ማለፍ ለሴቲቱ ክብርም ሲባል ብሎም የሴቲቱ ስም እንዳይጠፋ ሲባል እንዲሁም በፍርሃት የተነሳ ተደብቆ ማሳለፉ የአደባባይ ሚስጥር ነዉ። ከዛ በዘለለ ባል ላታገኝም ትችላለች የሚባል አጉል ልማድም አልፎ አልፎ ይታያል። በማኅበራዊ ጉዳይ ላይ በርካታ ጽሑፎችን ለአንባቢ በማቅረባቸዉ የሚታወቁት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እንደሚሉት የሴቶችን አያያዝ በተመለከተ በማኅበረሰባችን ሁለት አይነት ነገሮችን አያለሁ። አንዱ የሴትን አክብሮት እጅግ ከፍ የሚያደርግ፤ ሌላዉ ለሴት ክብር የማይሰጥ ነዉ።   
ዲያቆን ዳንኤል እንደሚሉት ኢትዮጵያዊ ጨዋነት፤ ለተጨቆኑ መቆምን መብትን ማክበርን እዉነተኛ መሆንን ሁሉ ያካታትታል። 
 
በሰሜን አሜሪካ በሥራ ገበታ የሚታየዉን የፆታ ጥቃት ለመታገል ሲባል #Metoo የተሰኘዉ ንቅናቄ መጀመሩ ሰዎች ከሰዎች ጋር የሚያደርጉት የወዳጅነት ግንኙነት እንዲገታ ሆንዋል። በሥራ ገበታም ቢሆን ሰራተኞች በምን ይጋጩ ተብሎ የተቀመጠ ሕግ ነዉ ብለዉ #Metoo ንቅናቄን የሚያጣጥሉ ወገኖች ጥቂት አይደሉም።

በፆታዊ ጥቃት ምክንያት ወንዶች ለፍቅር ግንኙነት ባይሆንም የወደድዋትን ሴት ቁንጅና እንዳያደንቁና እንዳይነግሯት ፤ መዉደዳቸዉን እንዳይገልጹላት ያደርጋል፤ ሲሉ ንቅናቄዉን በመቃወም በርሊን ላይ ጥቂት ሴቶች ለተቃዉሞ ሰልፍ ወጥተዉ ነበር። በኢትዮጵያ  በማኅበረሰባዊ እና በፖለቲካዉ ጉዳይ የሴቶች ተሳትፎ ጎልቶ አለመዉጣት ሴቶች ወንድን ቅድምያ የመስጠት ልማድ ብቻም ሳይሆን ሴቶች ራሳችን ባለመደጋገፋችን ነዉ የሚሉ እንስቶችም አሉ። ጋዜጠኛ ቅድስት አቤኔዘርም በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ።    
 
አለመች ፤ አቀደች ፤ አሳካች፤ ትዊተር በተሰኘዉ የማኅበራዊ መገናኛ ገጽ ሴቶች በማኅበረሰብ ዘንድ የሚያደርጉትን ላቅ ያለ ተሳትፎ አጉልቶ የሚያወጣ ገጽ ነዉ። በርግጥ እንደተባለዉ በኢትዮጵያ ማኅበረሰቡም ሆነ ሚዲያዉም እዉቅና የሚሰጠዉ ከሴት ይልቅ ለወንዶች ነዉ? ይህ አሸንፎ ለመዉጣት የሴቶች እንቅስቃሴ ምን መምሰል ይኖርበታል? #Metoo ስለተሰኘዉ የፆታ ጥቃትን የሚያጋልጠዉ እና የሚቃወመዉ ንቅናቄ ያላችሁን አስተያየት እንድትሰጡን በመጠየቅ ሙሉ መሰናዶዉን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።  


አዜብ ታደሰ


ተስፋለም ወልደየስ 
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች