G-8 መንግሥታትና የአፍሪቃ የልማት ዕጣ | ኤኮኖሚ | DW | 23.05.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

G-8 መንግሥታትና የአፍሪቃ የልማት ዕጣ

ሰባቱን ቀደምት በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ መንግሥታትና ሩሢያን ያሰባሰበው ቡድን፤ የ G-8 መሪዎች ጉባዔ ከአንድ ሣምንት በኋላ በዚህ በጀርመን ይካሄዳል። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እንደተለመደው የአፍሪቃ ልማት ከጉባዔው ዓበይት የአጀንዳ አርዕስት አሁንም አንዱ ነው።

default

የአፍሪቃ ድህነት፤ የልማትና የበጎ አስተዳደር እጦት በተለይ ጎልቶ የተነሣው ከሁለት ዓመታት በፊት ስኮትላንድ-ግሌንኢግልስ ላይ በተካሄደው የ G-8 መንግሥታት መሪዎች ጉባዔ ነበር። በጊዜው በርከት ላሉ ታዳጊ ሃገራት የዕዳ ስረዛ ሲደረግ፤ ቀደምቱ መንግሥታት የልማት ዕርዳታቸውን ከፍ ለማድረግ ቃል መግባታችውም አይዘነጋም። ግን የተባለው ሁሉ ገቢር አልሆነም።

ቡድን 8 የአፍሪቃ ችግር ወይም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዓለም ላይ ድህነትን በግማሽ ለመቀነስ በ 2000 ዓ.ም. ያሰፈነው የሚሌኒየም ዕቅድ በቅርብ የወለደው ስብስብ አይደለም። ምንጩ መለስ ብሎ በ 70ኛዎቹ ዓመታት የመጀመሪያ አጋማሽ ነዳጅ ዘይት እስካስከተለው የዓለም ኤኮኖሚ ቀውስ ድረስ የሚዘልቅ ነው። እ.ጎ.አ. በ 1975 የያኔው የፈረንሣይ ፕሬዚደንት ዢስካርድ ዴ’ኤስታንግ የጊዜዋን ምዕራብ ጀርመን፣ የኢጣሊያን፣ የጃፓንን፣ የብሪታኒያንና የአሜሪካን መሪዎች ጋብዘው በራምቡልዬ ያስተናግዳሉ። እንግዲህ ያኔ ነበር መንግሥታቱ G-6 ቡድንን አቋቁመው በተፈራራቂ ርዕስነት ዓመታዊ ጉባዔ ለማካሄድ የወሰኑት። ከዚያም ካናዳ ስብስቡን በዓመቱ ስትቀላቀል ቡድኑ G-7 በሚል መጠሪያ የዓለም ኤኮኖሚን ችግሮች እያነሣ ሲወያይ፤ ግብ ሲተልም ቆይቷል።

እንደዛሬው ቡድን 8 ሊባል የበቃው ደግሞ በቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም ሳቢያ የኋላ ኋላ ሩሢያን በመጠቅለሉ ነው። ታዲያ ይህ የሃያላኑ መንግሥታት ስብስብ አፍሪቃን ቀደም ካለው ጊዜ ይልቅ በከፍተኛ ደረጃ ማተኮሪያው ሲያደርግ የስኮትላንዱ ጉባዔው የመጀመሪያው ነበር። እርግጥ የበለጸጉት መንግሥታት ከአጠቃላይ ማሐበራዊ ምርታችው 0,7 ከመቶ የምትሆነዋን ድርሻ በያመቱ ለልማት ዕርዳታ በተግባር ለማዋል ቃል ከገቡ ሩብ ምዕተ-ዓመት አልፏል። ግን እስከዛሬ ይህን በሥራ ላይ ያዋሉት ሶሥትና አራት በእጣት የሚቆጠሩ አገሮች ብቻ ናቸው። እነዚሁ ደግሞ ስዊድንንና ኔዘርላድን የመሳሰሉት እንጂ በቡድኑ የተጠቃለሉት ሃያላን መንግሥታት አሜሪካ፣ ብሪታኒያ ወይም ጀርመን አይደሉም።

ወደ ቡድን 8 እንመለስና እነዚህ 14 በመቶው የዓለም ሕዝብ ድርሻ ብቻ ያላቸው ሥምንት መንግሥታት በአጠቃላይ ብሄራዊ ምርት መጠን ሲተመን ግዙፉን ሁለት-ሶሥተኛውን የዓለም ሃብት ይጠቀልላሉ። ይህም ታላቅ ክብደት የሚሰጣቸው ነው። ስለዚህም ከሁለት ዓመታት በፊት ስኮትላንድ-ግሌንኢግልስ ላይ ተካሂዶ የነበረው የስብስቡ መሪዎች ጉባዔ በተለይ ለአፍሪቃ ልማት የተሥፋ ጮራን የፈነጠቀ ነበር። በዕዳ ስረዛና በተጠናከረ የልማት ዕርዳታ የአፍሪቃን ድህነት፣ ኋላ ቀርነትና የበሽታ መቅሰፍት ያለፈ ታሪክ ለማድረግ ብዙ ብዙ ተብሏል። ችግሩ ዛሬም እንዲያልፍ የተፈለገው ታሪክ ሊያልፍ በማይችልበት ሁኔታ መቀጠሉ ነው።

የዘንድሮዋ የ G-8 ርዕስ የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ ሜርክል ትናንት በርሊን ላይ የአፍሪቃን የልማት ሽርክና መድረክ ጉባዔ ሲከፍቱ የዓለም መንግሥታት መሪዎች ለአፍሪቃ የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ ጥሪ አድርገዋል። የአፍሪቃ ችግር መፍትሄ የሚያገኘው በዓለምአቀፍ ጥረት መሆኑን ላስገነዘቡት ለጀርመኗ ቻስስለር ቀደምቱ መንግሥታት ቃላቸውን ማክበራቸው ለዓመኔታና ለተደማጭነታቸውም ወሣኝ ነው። ይህን መሰሉ ጥሪ በመሠረቱ አዲስ ነገር አይደለም። ጥያቄው ምን ግምት ሊሰጠው ይችላል ነው። 31ኛውን የዘንድሮውን የቡድን 8 ጉባዔ የምታስተናግደው ጀርመን ራሷ ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርቷ 0,7 በመቶውን ድርሻ ለልማት ዕርዳታ ለማቅረብ ከዓመታት በፊት የገባችውን ቃል እስከዛሬ ዕውን አላደረገችም። ስለዚህም ለጥሪው ክብደት ለመስጠትም ሆነ ሰሚ ጆሮ ስለማግኘቱም ተሥፋ መጣል ያዳግታል።

የበለጸጉት መንግሥታት የልማት ዕርዳታ አቅርቦታቸውን እስከፊታችን 2010 ዓ.ም. ድረስ በእጥፍ ለማሳደግ የገቡት ቃል ዛሬ ገቢር የሚሆንበት አዝማሚያ ጎልቶ አይታይም። በዓለምዓቀፍ ደረጃ ሲተመን ወደ አፍሪቃ የሚገባው ቀጥተኛ መዋዕለ-ነዋይ ከሁለት በመቶ አይበልጥም። ለዚህም ምክንያቱ እርግጥ ከምዕራባውያን መንግሥታት በኩል አልፎ አልፎ እንደሚነገረው ለካፒታል ባለቤቶች አመቺው ሁኔታ አለመኖሩ ብቻ አይደለም። G-8 መንግሥታት የገቡትን ቃል በዕውነት ገቢር ለማድረግ የሚፈልጉ ከሆነ ሣምንት በዚህ በጀርመን-በሃይሊገንዳም በሚያካሂዱት ጉባዔ ጭብጥ ዕርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል። አለበለዚያ ሃይሊገንዳምም ግሌንኢግልስ፤ ግሌንኢግልስም ሃይሊገንዳም ሆነው ይቀጥላሉ።

የቡድን 8 የእስካሁኑ ሂደት ያላረካቸው ወገኖች የሚፈልጉትና ግፊት የሚያደርጉት ይህ እንዳይሆን ነው። በናይሮቢ የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ቅስቀሣ ቢሮ ሃላፊ ታጁዲን-አብዱል-ራሄም ጉባዔው ጭብጥ ነገር እንጂ እንደገና አዲስ የአፍሪቃ ዕቅድ ይዞ መውጣቱን አይፈልጉም። መንግሥታቱ እንደገና ከሣሃራ በስተደቡብ ለሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል ተጨማሪ ቃል በመግባት ብቻ ከተወሰኑ ነገሩ ከንቱ ነው። ናይጄሪያዊው አብዱል-ራሄም በሌላ በኩል ድህነትን በዓለም ዙሪያ በተሣካ ሁኔታ መቀነስ እንደሚቻል እርግጠኛ ናቸው።

“ቴክኒካዊውን ሁኔታ ሲያጤኑትና የሰውልጅ ባለፉት ዓመታት ያካበተውን ጸጋ ሲመለከቱት በረሃብ የሚሰቃየውን የዓለም ክፍል ለመርዳት ብዙ መንገድ ነው ያለው። ለሁሉም የሚበቃ ምግብ አለ። የሚፈለገው የጠነከረ የፖለቲካ ጥረት ነው”

እርግጥ በርሳቸው አመለካከት ግን ይህ የፖለቲካ ፍላጎት በለጋሾቹም ሆነ በአፍሪቃ አገሮች አለ ለማለት አይቻልም። አብዱል-ራሄም ኢትዮጵያን እንደ ምሳሌ ጠቅሰው እንደሚሉት ለነገሩ አፍሪቃ የሚባለውን ያህል ድሃ አይደለችም።

“ኢትዮጵያን የመሰለች አገር በየጊዜው ለምግብ ዋስትናና ለጤና አገልግሎት ዕርዳታ በመለመን ነው የምትታወቀው። በተመሳሳይ ጊዜ ግን ወደ ጎረቤት አገር ለመገስገስና ጦርነት ለማካሄድ ሃብት አላት”

በሌላ በኩል ለጋሽ አገሮች የልማት ዕርዳታቸውን እስከ 2010 ዓ.ም. ከ 25 ወደ 50ሚሊያርድ ዶላር ለማሳደግ የገቡትን ግዴታ መወጣታችውን ኦክስፋምን የመሳሰሉ ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች አጠያያቂ ያደርጋሉ። ለዚህም መንስዔ የሚያደርጉት የአውሮፓ ሕብረት የልማት ዕርዳታ ሚኒስትር በቅርቡ ይፋ ያደረጉት ዘገባ ነው። በዘገባው መሠረት የልማት ዕርዳታው አቅርቦት በዓለምአቀፍ ደረጃ በተገባው ቃል መሠረት ባለፈው ዓመት እንዲያውም መጠኑን አልፎ መገኘቱን አመልክቷል። ይህ ደግሞ ከተለያዩ ወገኖች በኩል በሕብረቱ ላይ ከፍተኛ ትችትን መቀስቀሱ አልቀረም። በዚህ በጀርመን ቦን ላይ ተቀማጭ የሆነው የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ዕቅድ ቅስቀሣ ቢሮ ሃላፊ ሬኔ ኤርንስት እንዲህ ይላሉ፤

“ለነገሩ ጀርመን ይፋ አሃዞችንና የአውሮፓን ሕብረት ደረጃ በደረጃ ዕቅድ ከተከተልን ግዴታዋን እየተወጣች ነው። ግን ይህ ይፋው መረጃ ነው። ከዚህ ጀርባ ከተመለከትን ግን ለናይጄሪያ ወይም ለኢራቅ የተሰረዘውን ዕዳ፤ ለውጭ ዜጎች ትምሕርት የሚወጣውን ወጪ የመሳሰሉ ነገሮች በልማት ዕርዳታው ውስጥ ታስበው ይገኛሉ። እንግዲህ በብሄራዊ ምርት መስፈርት 0,42 በመቶ ደረሰ የተባለው ዕርዳታ እንደ ዕውነቱ ከ 0,23 በመቶ በታች ይሆናል ማለት ነው”

ሬኔ ኤርንስት እንደሚሉት የልማት ዕርዳታው ገንዘብ የሚሰጣቸው አገሮች በድህነታቸው መጠን ሣይሆን በፖለቲካ ምክንያት የሚመረጡበት ጌዜም ጥቂት አይደለም። ገንዘቡ የሚሄደው እንደሚታሰበው ወደ ድሆቹ በዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ወደሚገኙት አገሮች አይደለም። የመጀመሪያዎቹ የዕርዳታው ተቀባይ አገሮች በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙ ናችው። እዚህም ቃልና ተግባር ተጣጥሞ አይገኝም። ይህ የታጁዲን-አብዱል-ራሄምም አመለካከት ነው።

“የሚያሳዝን ሆኖ ቡድን 8 ባለፉት ዓመታት ያቀረባቸው ጭብጥ ውጤቶች እጅግ ጥቂቶች ናችው። የተገባው ቃል ብዙም አልተከበረም። የዕዳ ስረዛውን ወደ ጎን ብንተው የልማት ዕርዳታው ማቆልቆሉን እንጂ አለመጨመሩን ነው የምንረዳው። ከጀርመን የምጠብቀው ሁለት ነገሮችን ነው። አንደኛ ተጨማሪ ቃል እንዳይገባ፤ ሁለተኛ ደግሞ እስካሁን የተገባው ቃል መከበሩን”

በእርግጥም በጀርመን ብቻ ሣይሆን በጠቅላላው በበለጸጉት መንግሥታት ዘንድ የሃሣብ ተሃድሶ ካልተደረገ በአፍሪቃ ድህነትን ለመቀነስ መቻሉ ዘበት ነው። ይህን ሃቅ በመሠረቱ ቡድን 8 ውስጥ የተሰባሰቡት መንግሥታት አጥተውት አይደለም። አፍሪቃን በተመለከተ በአካባቢው ያላቸውን ስልታዊ ጥቅምና ጉድኝት የልማት ዕርዳታ ፖሊሲያቸው ቀደምት ዓላማ ማድረጋችው እንጂ! ምዕራባውያኑ መንግሥታት ራሳቸው ለልማት ዕርዳታ ቅድመ-ግዴታ ያደረጓቸውን በጎ አስተዳደርን፣ ጸረ-ሙስናንና የሰብዓዊ መብት ከበሬታን ጭብጥ የተግባራችው መስፈርት ሲያደርጉ አይታዩም።

በአንጻሩ የቻይናና የአፍሪቃ ትብብር መስፋፋት ይበልጡን ከራስ ጥቅም የተነሣ ዕፎይታ ነስቷቸው ነው የሚገኘው። ቻይና የተፋጠነ ዕድገቷ የሚጠይቀውን ነዳጅ ዘይትና ሌላ የተፈጥሮ ጸጋ ለማግኘት ስትል ዕጣዋን ከአፍሪቃ አስተሳስራለች። የምትሰጠው ዕርዳታ በግልጽ እየጨመረ፤ ለአፍሪቃ መዋቅራዊ ግንባታ የምታደርገው አስተዋጽኦም በፍጥነት እያደገ ነው። በሌሎች አገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት በሚል ፖሊሲዋ እርግጥ ትብብሯን በሰብዓዊ መብት ቅድመ-ግዴታ ላይ አልመሰረተችም። ከአምባገነን ገዢዎች ጋርም ትተባበራለች። ተጽዕኖዋን ተጠቅማ ግፊት አለማድረጓ እርግጥ ያሳዝናል። በሌላ በኩል ግን ወቀሣ የሚሰነዝርባት ምዕራቡ ዓለምም ቢሆን ጥቅሙን ከመብት ማስቀደሙ ነው ችግሩ።
የቡድን 8 የፊናንስ ሚኒስትሮች ባለፈው ቅዳሜ በርሊን አጠገብ ፓትስዳም ላይ ባደረጉት ስብሰባ ቻይና በርካሽ ለአፍሪቃ የምትሰጠው ብድር ክፍለ-ዓለሚቱን መልሶ ዕዳ እንዳያሸክም አስጠንቅቀዋል። የተሻለ ጭብጥ አማራጭ ግን አላቀረቡም። ለማንኛውም የቻይና በአፍሪቃ መስፋፋት ማንም ሊገታው የማይችል ነገር ነው። ቤይጂንግ አሁን ለአፍሪቃ መዋቅራዊ ግንባታና ለንግድ መራመድ በሚቀጥሉት ሶሥት ዓመታት 24,3 ቢሊዮን ዶላር ለማቅረብ ታቅዳለች። ዓላማው የኤሌክትሪክ ሃይል፣ የመንገዶችንና የሌሎች መዋቅሮችን እጥረት ማረቅ ሲሆን ዕቅዱ ምዕራቡን ዓለም የሚያስከነዳ ነው። ምናልባት ይህ የቻይና መጠናከር በሃይሊገንዳም የሚሰበሰቡትን የቡድን 8 መንግሥታት መሪዎች ለተሻለ ዕርምጃ ይቀሰቅስ ይሆን? ቢሆን ምንኛ በበጀ!