81 ቡና ላኪዎች ለምን ታገዱ? | ኤኮኖሚ | DW | 10.04.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

81 ቡና ላኪዎች ለምን ታገዱ?

የኢትዮጵያ መንግሥት ውላቸውን አላከበሩም ያላቸውን 81 የቡና ላኪዎችን  አግዷል።  የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት የታገዱት ኩባንያዎች አድራሻቸው የማይታወቅ፤ በተከታታይ ማስታወቂያዎች ጥሪ ተደርጎላቸውም ምላሽ ያልሰጡ ናቸው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:48

ውላቸውን ያላከበሩ 81 ቡና ላኪዎች ከግብይት ታግደዋል

የኢትዮጵያ መንግሥት ውላቸውን አላከበሩም ያላቸውን 81 የቡና ላኪዎችን አግዷል ።  የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት የታገዱት ኩባንያዎች አድራሻቸው የማይታወቅ፤ በተከታታይ ማስታወቂያዎች ጥሪ ተደርጎላቸውም ምላሽ ያልሰጡ ናቸው።

ኃላፊው እንደሚሉት እግድ የተጣለባቸው ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት (ECX) በየዕለቱ ግብይት የሚፈጽሙበት መረጃ በተቋማቸው እጅ ይገኛል። ቡና ላኪዎቹ ስልክ ተደውሎላቸው እንኳ ምላሽ መጥፋቱን ዶክተር አዱኛ ደበላ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት በ81 ቡና ላኪዎች ላይ የተጣለው ዕግድ ከመጋቢት 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ሆኗል።

የኢትዮጵያ የቡና ግብይት በበርካታ ፈተናዎች የተተበተበ ሆኖ ይታያል። የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም በዓለም ገበያ ለመሸጥ የገዙትን ቡና ሰውረዋል ያላቸውን ሲያግድ ቆይቷል። በዚሁ አሰራር ኢትዮጵያ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ አሳጥተዋል የተባሉ ነጋዴዎች ክስ ተመስርቶባቸው ታስረውም ያውቃሉ።

ለኢትዮጵያ የቡና ግብይት ፈተና የሆነው ግን በአገሪቱ ገበያ የሚታየው ችግር ብቻ አይደለም። ካለፈው መስከረም ጀምሮ የግማሽ ኪሎ ቡና ዋጋ ከአንድ ዶላር በታች ወርዷል። ዓለም አቀፉ የቡና ድርጅት እንደሚለው ከጎርጎሮሳዊው 2006 ዓ.ም. ጀምሮ የቡና ግብይት እንዲህ ሲያሽቆለቁል የመጀመሪያው ነው። በዓለም የቡና ግብይት ከፍ ያለ ድርሻ ያላቸው የብራዚል እና የቪየትናም ምርት በከፍተኛ መጠን መጨመር ለዋጋው መቀነስ ዋንኛ ገፊ ምክንያት ነው። "በ13 ጊዜ ውስጥ እንደዚህ አይነት ዋጋ ታይቶ አይታወቅም" የሚሉት ዶክተር አዱኛ ደበላ ኬንያን የመሰሉ አገሮች በዋጋ መቀነስ ለተፈጠረባቸው ጫና አስተዳደራዊ መፍትሔ ለመውሰድ እርምጃ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ 

Audios and videos on the topic