80ኛው የሰማዕታት ቀን መታሰቢያ | ኢትዮጵያ | DW | 20.02.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

80ኛው የሰማዕታት ቀን መታሰቢያ

የካቲት 12 የጀግኖች ሰማዕታት ቀን ዛሬ በተለይ አዲስ አበባ ውስጥ ታስቦ ዋለ። የጸሎት ስነ ስርዓቱ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ካቴድራል የተደረገ ሲሆን፤ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የሰማዕታት ሃውልትም የአበባ ጉንጉን ተቀምጧል።

የሰማዕታቱ ቀን 80ኛ ዓመት መታሠቢያ አዲስ አበባ ውስጥ አርበኞች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተወካይ እና ታዳሚዎች በተገኙበት ዛሬ ታስቦ መዋሉን የተከበሩ አቶ ኃይለሚካኤል አባይ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ውጭ ግንኙነት እና የልማት ኃላፊ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። በተለይ ለወጣቱ ትውልድም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። 

«ማንኛው ኃይል ሲመጣ አባቶቻችን በጋራተሰባስበው እንደ አንድ ክንድ ኾነው ነው ጠላታቸውን ድል ሻደረጉት።  በጋራ፦ በቋንቋ፤ በሃይማኖት፣ በጎሣ ሳይለያዩ በጋራ እንደ አንድ ሰው ኹነው ነው፤ ኢትዮጵያ ሀገሬን በቃ ማንም አይነካትም በሚል ነው። እና ወጣቱም ትውልድ የአሁኑ ወጣት ትውልድ  የዚህ አይነት የሀገር ፍቅር ስሜት እንዲያድርበት ያስፈልጋል።»

የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. የፋሺስት ጣልያን የኢትዮጵያ አገረ ገዢ የነበረው ፊልድ ማርሻል ሮዶልፎ ግራዝያኒ ከተቃጣበት የግድያ ሙከራ በኋላ ሰላማዊ ኢትዮጵያዉያንን በፍጹም ጭካኔ እና አሰቃቂ ሁኔታ ጨፍጭፏል። በወቅቱ በተከታታይ ቀናት በተደረገው ጭፍጨፋ ከ35 ሺ በላይ ህዝብ ማለቁ በታሪክ  መዝገብ ሰፍሮ ይገኛል። 

የሮዶልፎ ግራዚያኒ የያኔዋ የፋሺስት ጣሊያን በአምስት ዓመቱ ወረራ ወቅት በዓለም የተከለከለ መርዝ ጋዝ ከአውሮፕላን መወርወርን ጨምሮ በርካታ የጭካኔ ተግባራትን በኢትዮጵያውያን ላይ ፈጽማለች። በአዲስ አበባ እና በደብረሊባኖስ ገዳም የተጨፈጨፉትን ጨምሮ በአምስት ዓመቱ የወረራ ወቅት በብዙ መቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን መስዋእት መኾናቸው ይጠቀሳል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ልደት አበበ