75 ሚሊዮን እጅ መንሻ የሚከፍሉባት አፍሪቃ | አፍሪቃ | DW | 05.12.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

75 ሚሊዮን እጅ መንሻ የሚከፍሉባት አፍሪቃ

ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ተቋም ከሰሐራ በታች በሚገኙ የአፍሪቃ አገራት በሠራው የዳሰሳ ጥናት 75 ሚሊዮን የአህጉሪቱ ሰዎች የእጅ መንሻ እንደሚከፍሉ አመለከተ። በጥናቱ መሰረት 53 በመቶ አፍሪቃውያን ሙስና በአህጉሪቱ እየተባባሰ ነው የሚል እምነት አላቸው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:50
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:50 ደቂቃ

75 ሚሊዮን እጅ መንሻ የሚከፍሉባት አፍሪቃ

በዚምባብዌ ወደ ትምህርት ቤት በመጓዝ ላይ የነበረች የዘጠኝ አመት ታዳጊ በግዳጅ ተደፈረች። ታዳጊዋ በኤች.አይ.ቪ. ተሐዋሲ ተያዘች። አስገድዶ የደፈራት ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ቢውልም ወዲያውኑ ከእስር ተለቀቀ። ምክንያቱም ጉቦ በመክፈሉ ነበር። ይህ ትራንፓረንሲ ኢንተርናሽናል ከሰሐራ በታች በሚገኙ የአፍሪቃ አገራት ካጋጠሙት ታሪኮች አንዱ ነው።

ተቋሙ ይፋ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ከሰሐራ በታች በሚገኙ የአፍሪቃ አገራት ወደ 75 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ባለፈው አንድ አመት ከፖሊስ አሊያም ፍርድ ቤት ቅጣት ለማምለጥ እጅ መንሻ ወይም ጉቦ ከፍለዋል። አፍሮባሮሜትር ከተሰኘ የማህበረሰብ ጥናት ጋር በመተባበር በ28 አገራት የተሠራው የዳሰሳ ጥናት ተሳታፊዎች ከሰሐራ በታች በሚገኙ የአፍሪቃ አገራት ሙስና በአስደንጋጭ ፍጥነት እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል። ኮራሌ ፕሪንግ የጥናቱ አስተባባሪ ናቸው።

«በደቡብ አፍሪቃ 83 በመቶ የጥናቱ ተሳታፊዎች ባለፉት አስራ ሁለት ወራት ሙስና መጨመሩን ተናግረዋል። ይህ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ነው። ይህ በደቡብ አፍሪቃ በቅርቡ ተከስቶ በነበረው የሙስና ቅሌትና በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ወጪ የሆነበት የፕሬዝዳንቱ የመኖሪያ ቤት እንዲሁም ከሃዲዱ ጋር የማይስማማ የባቡር ግንባታ ጉዳይ ላይ የህዝብ ቅሬታ መኖሩን ይጠቁማል።»

በዳሰሳ ጥናቱ መሠረት 58 በመቶ አፍሪቃውያን ባለፈው አንድ አመት ሙስና እየተባባሰ መጥቷል ብለው ያምናሉ። የአህጉሪቱ መንግስታትም ችግሩን በአግባቡ አልተቆጣጠሩትም ባዮች ናቸዉ። በጥናቱ ከተዳሰሱ 28 አገራት መካከል 18ቱ ደግሞ ጭርሱን ችላ ብለውታል። የጥናቱ ተሳታፊዎች የአፍሪቃ ፖሊስና የቢዝነስ ሥራ አስፈጻሚዎች በከፋ ሙስና የተዘፈቁ እንደሆኑ ምላሽ ሰጥተዋል። ኮራሌ ስፕሪንግ በአፍሪቃ ያለው ሙስና አስከፊ ጫና እያሳረፈ የሚገኘው የዕለት ጉርስ ባጡት መጠለያም በተቸገሩት ላይ መሆኑን በዚህ ጥናት ተረድተናል ሲሉ ይናገራሉ።

«ያገኘናቸውን መረጃዎች በጥንቃቄ ስንመረምር በሙስና እጅግ የተጎዱት ደሆች መሆናቸውን ተረድተናል። በአፍሪቃ የእጅ መንሻ የመክፈል እድላቸው ድሆች ከሃብታሞች ይልቅ ሁለት እጥፍ ላቅ ያለ ነው። ይህ በአህጉሪቱ ድሆች ላይ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ጫናነው። እነዚህ ሰዎች የዕለት ምግባቸውን እና መጠለያ ለማግኘት የሚታገሉ ሰዎች ናቸው።»

አፍሪቃውያኑ የእጅ መንሻ ለመክፈል አሻፈረኝ ለማለትም ሆነ በጸረ-ሙስና ትግሉ ውስጥ አስተዋጽዖ ለማበርከት እንደማይችሉ ያምናሉ። እንደ ፖሊስና ፍርድ ቤቶች ያሉ የመንግስት ተቋማት የችግሩ አካል መሆናቸው ደግሞ ተስፋ ከሚያስቆርጧቸው መካከል ይገኙበታል። ከአህጉሪቱ ደቡብ አፍሪቃ በ83%፤ ጋና በ76% እንዲሁም ናይጄሪያ 75% ሙስና ከፍ ማለቱ ያሳየባቸው ተብለው በጥናቱ ተዘርዝረዋል። በቡርኪና ፋሶ፣ በማሊ እና ኮትዲቯር ቃለ-መጠይቅ የተደረገላቸው ሰዎች ሙስና ተባብሷል በማለት ምላሽ የሰጡ ዜጎች ቁጥር አነስተኛ ነው። በጥናቱ መሠረት ፖሊስ፤ የቢዝነስ ሥራ አስፈጻሚዎች፤ የመንግሥት ባለስልጣናት፤ ዳኞች፤ የምክር ቤት አባላት፤ የክልል መንግስት አማካሪዎች የፕሬዝዳንት ጽ/ቤት፤ ባህላዊና ሐይማኖታዊ መሪዎች በተለያየ ደረጃ እጅ መንሻ የሚቀበሉ ተብለው የተዘረዘሩ ናቸው። ኮራሌ ፕሪንግ ደካማ የመንግሥት መዋቅር በአፍሪቃ ለተስፋፋው ሙስና ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ።

«ደካማ የመንግስት መዋቅር ያላቸው አገራት ወይም ግልጽነትና ተጠያቂነት የሌለባቸው ከፍተኛ ሙስና የሚታይባቸው አገራት ናቸው። እነዚህ አገራት ለሲቪክ ማህበረሰብ በአገራቸው እንዲኖሩና ሙስናን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት እንዲሳተፉ አይፈቅዱም።»

በዚህ ጥናት ኢትዮጵያ አልተካተተችም። የዳሰሳ ጥናቱ በምዕራብ አፍሪቃ ተከስቶ ለነበረው የኢቦላ ወረርሽኝ ዘገምተኛ ምልሽ የሰጡ ላይቤሪያና ሴራሊዮን ከፍተኛ ሙስና የሚታይባቸው መሆናቸውን ጠቁሟል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic