70 ዓመታቸውን ያከበሩት አስገራሚው የ«አስትሮ-ፊዚክስ» ነባቤ ቃል ሊቅ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 11.01.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

70 ዓመታቸውን ያከበሩት አስገራሚው የ«አስትሮ-ፊዚክስ» ነባቤ ቃል ሊቅ

ሰውየው ፤ ከአልበርት አይንሽታይን ወዲህ በአሁኑ ዘመን እጅግ ዝነኛው የፊዚክስ ሊቅ መሆናቸው ነው የሚነገርላቸው።

default

ባለፈው እሁድ፤  70 ዓመት የደፈኑ ሲሆን፣  የልደት በዓላቸውም  በዚያው ዕለት፣ በሚያስተምሩበት  በብሪታንያው ዝናኛ ዩኒቨርስቲ ፣ ኬምብሪጅ ውስጥ በተዘጋጀ ልዩ ጉባዔ ነው የተከበረው። የተሽከርካሪ ወንበር ቁራኛ የሆኑት ፕሮፌሰር ግን  ፣ ህመም ስለጠናባቸው  በአካል ተገኝተው የክብረ-በዓሉ ተሳታፊ ለመሆን አልቻሉም። የ«አስትሮ-ፊዚክስ» ነባቤ ቃል ሊቅ፣ ስቴፈን ሆውኪንግ!   
ሆውኪንግ፤  አስደናቂ ሳይንቲስት ናቸው። በ 21 ዓመታቸው ፤ ታክመው ሊድኑ የማይችሉበት Lou Gehrig’s  Disease  ወይም በሳይንሳዊ አጠራሩ  A-myo-trophic lateral sclerosis የተሰኘ የነርቭ ሞተር በሽታ አገኛቸው። የቃሉ መሠረት ግሪክኛ ሲሆን (A)አይደለም ማለት ሲሆን MYO ጡንቻ፣ TROPHIC ደግሞ መመገብ ማለት ነው፤ ስለዚህ፤ «ምግብ የማያገኝና የሚሟሽሽ ጡንቻ» የሚል ትርጓሜ ይይዛል። እስክሌሮሲስ ጠባሳ ወይም የጠጠረ የአካል ክፍል እንደማለት ነው። በሽታው፣ ሉ ገሪግ የሚል ሥያሜ  የተሰጠው፣ በፋግ (ቤዝቦል) ጎበዝ ተጫዋችነታቸው፣  «የብረት ፈረስ» የሚል ተቀጥላ ስም እስከማግኘት ደርሰው ፤ በኋላ ፣ በ 36 ዓመታቸው፣ የተጠቀሰው በሽታ ሰለባ ሆነው፣ መሰናበት ግድ በሆነባቸው  የኒውዮርክ ፤ዩናይትድ እስቴትስ ተወላጅ ሄንሪ ልዊስ ገሪግ ስም ነው። በሽታው ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ምንነቱ የታወቀው ፣ እ ጎ አ ሰኔ 19 ቀን 1903 ተወልደው ሰኔ 2 ቀን 1941 ዓ ም ባረፉት በልዊስ ወይም ሉ ገሪክ አማካኝነት ነው ። ያረፉት በታመሙ በ2ኛው ዓመት ነው።
በአጭሩ የተጠቀሰው በሽታ ፤የአንጎልንና፣  ከማጅራት እስከ ኅብለ-ሠረሠር ጫፍ፣  የነርብ ኅዋሳትን የሚያቀጭጭ ነው ።

ይህ ዓይነቱ በሽታ የሚያጋጥማቸው ሰዎች የመኖር ዕድላቸው ቢበዛ ፤ ሁለት ወይም 3 ዓመት  ነው። እስቲፈን ሆውኪንግን  ግን ፤ በሽታው፤ከሞላ ጎደል ሙሉ- በሙሉ አሽመድምዶ ፤ እ ጎ አ፤ ከ 1970 አንስቶ የተሽከርካሪ ወንበር ቁራኛ  ቢያደርጋቸውና ያ፣ ድምጽ ያሳጣቸውም በህይወት ይገኛሉ።እ ጎ አ  በ 1985 ሳንባ  ምች ከተደረበባቸው በኋላ ደግሞ ፣ ክብክቤ የሚያደርግ የህክምን  ባለሙያ ከጎናቸው አይለይም፣ ድምጻቸውን ለማሰማትም ፤ በድምፅ ማጣሪያ የኮምፒዩተር መሣሪያ መጠቀም ግድ ሆኖባቸዋል።
እስቲፈን ሆውኪንግ ፤ እ ጎ አ ጥር 8 ቀን 1942  ዓ ም ከለንደን ጥቂት ፈንጠር ብላ በስተሰሜን በምትገኘው ፣ ሌላው ዕውቅ የአንግልጣር ዩኒቨርስቲ በሚገኝባት ከተማ በኦክስፈርድ ተወለዱ።  በወጣትነታቸው የፊዚክስ ፍቅር ያደረባቸው ሆውኪንግ ፤ በአንጎልና በኅብለ ሠረሠር የነርብ ኅዋሳት በሽታ ቢጠቁም ፤ በሚወዱት የትምህርት ዘርፍ ሰፊ ምርምር ከማካሄድ የገታቸው ነገር የለም። በሙያቸው ይህን ያህል ዘመን ሲታገሉ በግል ኑሮአቸውም ፤ ሁለት ጊዜ አግብተው የ3 ልጆች አባት ለመሆን የበቁ ሰው ናቸው።  አካላቸው የዛለ ቢሆንም ፤ የአእምሮአቸው የማስተዋል ችሎታ የሚደነቅ መሆኑ ነው የሚነገረው። ሆውኪንግ፤ የሚናገሩት  ቀደም ሲል እንደጠቀስነው በኮምፒዩተር እርዳታ ብቻ ነው።
1,«በ 1980ኛዎቹ ዓመታት የሚታሰበው፤ እንደሽቦ የተጠላለፈው ነባቤ ቃል፣የተሻለ የ«ኳንተም» ስበት ኃይልና እጅግ ኃያል ስበትን የሚመለከተው ነበር ፤ እርሱም እስከዚያን ጊዜ ድረስ መሪ ተፎካካሪ ኀልዮት ነበር።»
እስቲፈን  ሆውኪንግ ፣ እ ጎ አ ፣  ከ 1979 ዓ ም አንስቶ ፤ በኬምብሪጅ፤ ከእርሳቸው በፊት  የ 17ኛው ክፍለ ዘመን እጅግ ታዋቂ የፊዚክስ ፣ሂሳብና ሥነ ፈለክ  ሊቅ የነበሩት  Sir Isaac Newton ይዘውት የነበረውን የፊዚክሱን የፕሮፌሰርነት መንበር በመያዝ ነው ፍጥረተ-ዓለምን በሚመለከተው የፊዚክስ የምርምር ዘርፍ  ላይ፣ ጥልቅ ምርምር ያካሄዱት።

2, «በአሁኑ ጊዜ፤ ቁስ አካልን ስለሚመለከተው የተፈጥሮ ህግ እናውቃለን። ይህም የተለያዩ ቅድመ-ግዴታዎችን መሠረት ያደረገ ነው።ነገር ግን ለምን እነዚህ የተፈጥሮ ህግጋት እንደጸኑና እንደተገጣጠሙ የምናውቀው ጉዳይ የለም። መጠን ባለፈ ሁኔታ ቅድመ ሁኔታ ሳቢያ፣ ፍጥረተ ዓለምን ለማስገኘት ያስቻለው  ፍንዳታ  ሊከናወን የቻለበትን ደንብ አናውቀውም።  ፍጥረተ ዓለም  ሊዘረጋ የቻለበትን ፤ የተከሠተበትን ሁኔታ አናውቅም ። ይህ ጥያቄ ደግሞ የሰውን ልጅ ምንጊዜም እንዳስደመመ የቀጠለ --ታሪክ ነው።»
የአልበርት አይንሽታይንን  አጠቃላይ የቁስ አካል፤ የብርሃን ፤ የስበት ኃይልና ፍጥነት ነክ ነባቤ ቃል  መሠረት በማድረግ፤ የፍጥረተ ዓለም መነሻ የሆነው ፍንዳታ ከ 14 ቢሊዮን ዓመት ገደማ በፊት ፣ በአንድ ነጠላ ድርጊት እንደተከናወነና አሁን ባለው መመሪያና የተፈጥሮ ህግጋት ሊታወቅ እንደማይችል፣ ሆውኪንግ ይናገራሉ። የእርሳቸው ዐቢይ ትኩረት የሆነው ሆኖ ፣ በኅዋ «ጽልመታዊ ጉድጓዶች»(BLACK HOLES)በሚሰኙት ላይ ነው። እነዚህም ጉድጓዶች፣ ሀድ በሌለው ኅዋ ፣ በተለያዩ የከዋክብትና ፕላኔቶች ቀጣና፣ ባላቸው እጅግ ኃይለኛ የስበት ኃይል ሳቢያ፣  በአጠገባቸው የሚገኝ ፤ማንኛውንም፣ ኮከብንም ሆነ ሌላ ነገር ይሠለቅጣሉ። ሆውኪንግ፤ ጽልመታዊ ጉድጓዶች መጠናቸው እየጠበበ እየተኮማተረ እንደሚሄድ ነው የሚገልጹት።  መጠናቸው ሳይጨምር ፣ ሳይቀነስ በነበረው መጠን፣ ለዘለዓለም  የሚዘልቅ አይደለም። ጉድጓዶቹም፣ በማንጸባረቅ ኃይል ያመነጫሉ ነው የሚሉት። ነጸብራቁ ፤ «የሆውኪንግ ነጸብራቅ» የሚል ስያሜ አግኝቷል።  ግን ፣ ይኸው የተባለው ነጸብራቅ መኖሩ ገና አልተረገገጠም፤ ቢረጋገጥ ኖሮ ፣ እስቲፈን ሆውኪንግ ፣ በፊዚክስ የኖቤል ተሸላሚ ለመሆን በበቁ ነበር።
3,« ከጽልመታዊ ጉድጓዶች የሚፈነጥቀውን ነጸብራቅ ተከታትሎ በመለካት ማግኘት ይቻላል። ነገር ግን ከዚህ ከእኛ አካባቢ ሆኖ፤ ይህን ማድረግ የሚቻል አይመስልም። ያሳዝናል። በምርምር ከተደረሰበት ግን በእርግጥ የኖቤል ሽልማት አገኛለሁ።»
እስቲፈን ሆውኪንግ በእርግጥ ብዙዎች እንደሚያስቧቸው እጅግ የማስተዋል ተሰጥዖ ያላቸው ናቸው ወይ? እውነት ሁለተኛው አልበርት አይንሽታይን ናቸው ወይ? በሃምበርግ የፊዚክስ ፕሮፌሰር ክላውስ ፍሬደንሀገን ግን አይደሉም ባይ ናቸው።
4,«ሆውኪንግ ያበረከቱት ድርሻ በአርግጥ አልበርት አይንሽታይን እንዳበረከቱት ላቅ ያለ ትርጉም የሚሰጠው አይደለም። አይንሽታይን ፤ ከዚያ በፊት ያልቀረበ፣ አዲስ ነባቤ ቃል ነበረ ቀምረው ያሳወቁት። ሆውኪንግ በቀረቡ ነባቤ ቃላት ላይ ነው ጠቀሚ ድርሻ  ያበረከቱት። »
አንዳንድ ሳይንሳዊ የነባቤ ቃል ቅመራዎቻቸው የሚያከራክሩ ናቸው። ይሁንና እንዲያ ዓይነት ህመም ያለባቸው ቢሆኑም ብዙ የፊዚክስ ሊቃውንት እጅግ ያደንቋቸዋል። ለምሳሌ ቤርናርድ ሹትዝ! ቀድሞ የሆኪንግ ባልደረባ ነበሩ፤ በአሁኑ ጊዜ፤ ጀርመን ውስጥ፣ በርሊን አቅራቢያ በምትገኘው ከተማ ፣  በፖትስዳም ፣ የአልበርት አይንሽታይን ተቋም ኀላፊ ናቸው።
«እስቲፈን እንደ ፊዚክስ ምሁር እጅግ በጥልቀት ነው የሚሠሩት። ዓለምን በጥሞና ለመገንዘብ ነው ዋና ጥረታቸው።  ይህን ደግሞ፤ ለብቻ በአእምሮአቸው ነው የሚያከናውኑት።»
ታዋቂው እንግሊዛዊ ሳይንቲስት ፤ ወይም የኀልዮታዊ አስትሮፊዚክስ ሊቅ እስቲፈን ሆውኪንግ፤ እንደሚባለው ትልቅ ዝና ያተረፉት በመጽሐፎቻቸው ነው። እንደ ጎርጎሪያሳዊው ዘመን አቆጣጠር በ  1988 ዓ ም ያሳተሙት አጭር የጊዜ ታሪክ  (A Brief History of Time ፣ ፍጥረተ-ዓለም በጠንካራ ክብ ቆባ ውስጥ፣ ወይም ፍጥረተ ዓለም በአጭር አገላለጽ ፤( The Universe in a Nutshell) እንዲሁም  Leonard Mlodinow ከተባሉት ሌላ  የፊዚክስ ሊቅ ጋር በኅብረት ፤ታላቁ ንድፍ፣ (The Grand Design)በተሰኙት በሰፊው ገበያ ላይ በዋሉት መጽሐፍት ሆውኪንግ  ዝናቸው ከአጽናፍ አጽናፍ ነው የተዛመተው።STAR TREK በተሰኘው የሳይንስ ልብ-ወለድ ፊልም በአንድ ምዕራፍ ተሳትፈዋል። እ ጎ አ በ 2007  ዓ ም በአሜሪካው የብሔራዊ የበረራና የኅዋ ጉዳዮች አስተዳደር መ/ቤት( NASA) ወደ ጠፈር በመዝለቅ የስበት ኃይል በሌለበት ተንሳፈው የረጅም ጊዜ ምኞታቸውን አሳክተው ነበረ የተመለሱት። ያኔም እንዲህ ማለታቸው ይታወሳል።
7, « አስደናቂ ነበር ። ኅዋ ፤ ይኸውና እዚህ ተገኝቼአለሁ»!(ጭብጨባ)
ባለፈው እሁድ 70ኛ ዓመታቸው ኬምብሪጅ ውስጥ ፣ በ«ሌዲ ሚቸል አዳራሽ » ሲከበር በመቶዎች የሚቆጠር ህዝብና ታዋቂ የምርምር ሊቃውንት ነበሩ የተገኙት። ከብሪታንያው «ሮያል የሳይንስ አካደሚ»፣  ማርቲን ሪስ፤ እንዲሁም በፊዚክስ የኖቤል ተሸላሚው፣ ሶል ፐርልሙተር ፣ የክብረ በዓሉ ታዳሚዎች ነበሩ። እስቲፈን ሆውኪንግ ፤ በተቀረጸው የምሥጋና መልእክታቸው፤ «የሰው ልጅ ከሚኖርባት ፣ ከተጎሣቆለችው ምድር  ተነስቶ በሌሎች ፕላኔቶች መሥፈር ካልጀመረ፣ መጻዔ ዕድሉ የጨፈገገ ነው፤ ለኑሮ በሌላ ፕላኔት ላይ ካላተኮርን፤ በሚመጡት ሺ ዓመታት በምድር ላይ  የሰዎች ኅልውናው አስተማማኝ አይመስለኝም ።   
ለሰፊው ህዝብ ስለ ፍጥረተ ዓለም ማስረዳት ተገቢ ነው። ርእሰ-ጉዳዩ ያሳደረው ፍላጎት ከነባቤ ቃል የላቀ ነው»ብለዋል። አያይዘውም፤
« ፍጥረተ ዓለም እንዴት እንደሚሠራ ብታውቁ፣  በሆነ ነገር ትቆጣጠሩታላችሁ» ማለታቸውም ተጠቅሷል።

ተክሌ የኋላ
ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 11.01.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/13hfS

ተዛማጅ ዘገባዎች

 • ቀን 11.01.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/13hfS