6,5 ሚሊዮን ሕዝብ የምግብ ርዳታ መሻቱ | ኢትዮጵያ | DW | 15.05.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

6,5 ሚሊዮን ሕዝብ የምግብ ርዳታ መሻቱ

የዓለም የምግብ ድርጅት በዘንድሮዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2014 ለ6,5 ሚሊዮን ኢትዮጵያዉያን የምግብ ርዳታ ለመስጠት መዘጋጀቱን የጠቀሰ ዘገባ ሰሞኑን ይፋ ሆኗል። በኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሀገሪቱ የምግብ ርዳታ የሚያስፈልገዉ ሕዝብ ከ2,7 ሚሊዮን እንደማይበልጥ ያመለክታሉ።

ሮይተር የዓለም የምግብ መርሃ ግብር በእንግሊዝኛ ምህጻሩ WFP ኢትዮጵያ በገጠማት የአንበጣ ወረርሽ፣ የዝናብ እጥረትና በጎረቤት ሀገር በሚካሄድ ጦርነት ምክንያት የምግብ አቅርቦት የሚያስፈልጋቸዉን 6,5 ሚሊዮን ወገኖች በዚህ ዓመት ለመርዳት አቅጃለሁ ሲል ጄኔቫ ላይ መግለፁን ዘግቧል። በኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ወልደ ሚካኤል ድርጅቱ በጥቅሉ በሚያካሂዳቸዉ ፕሮጀክቶች የታቀፉትን እና የዉጭ ስደተኞችን እንዲሁም ሊፈናቀሉ ይችላሉ ተብለዉ የሚገመቱ ወገኖችን ጨምሮ ጠቅሶ ሊሆን እንደሚችል ነዉ የሚያስረዱት።

ሮይተርስ የጠቀሳቸዉ የWFP ቃል አቀባይ ኤልዛቤት ባየርስ ወቅታዊዉን የደቡብ ሱዳንን ዜጎች ወደኢትዮጵያ መሰደድ ምክንያት በማድረግ ለዘጋቢዎች በሰጡት ማብራሪያ ሀገሪቱ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ስደተኞችን ጨምራ የምግብ ርዳታ ለማቅረብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት ለማሳየት መሞከራቸዉን ነዉ ያመለከቱት።

Sudanesische Flüchtlinge in Äthopien Kule Flüchtlingslager

የደቡብ ሱዳን ስደተኞች

«በ2014 WFP 6,5 ሚሊዮን ገደማ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለችግር የተጋለጡ ሰዎችን ለመደገፍ አቅዷል። ይህንንም የምናከናዉነዉ በሶስት ትላልቅ መስመሮች አማካኝነት ነዉ፤ የረዥም ጊዜዉ የምግብ ዋስትናን ማጠናከር በሚያስችለዉ ምግብ ለሥራ በተሰኘዉ ፕሮጀከት፤ በድርቅና በሌላ አደጋ ለተጎዱ ኢትዮጵያዉያን የአስቸኳይ የምግብ ርዳታ፤ እንዲሁም ለስደተኞች የህይወት ማዳኛ ርዳታ የሚሉት ናቸዉ። ምክንያቱም ደቡብ ሱዳን ዉስጥ ያለዉ ግጭት ለኢትዮጵያና ለሌሎች ጎረቤት ሃገራት ስደተኞችን በማስተናገድ ረገድ ከፍተኛ የሰብዓዊ ተግዳሮት ፈጥሯል።»

WFP ከመንግስት ጋ በመተባበር የሚያካሂዳቸዉ የእርዳታ እንቅስቃሴዎች በድርቅ የተጎዱ 2 ሚሊዮን፣ የምግብ ለሥራ ተጠቃሚዎች 1,2 ሚሊዮን፣ ተጨማሪ ምግብ የሚያስፈልጋቸዉ 1,1 ሚሊዮን፤ በትምህርት ቤት ምግብ የሚዳረሳቸዉ 670ሺ፤ መርት በተባለዉ ፕሮጀክት የታቀፉ 649 ሺ እንዲሁም 500ሺ ስደተኞች የምግብ ድጋፍ እንደሚያደርግ ነዉ የዘረዘሩት ቃል አቀባይዋል። እናም አሉ፤

«እናም 6,5 ሚሊዮን ሕዝብ ምግብ አጥቷል ማለት አይደለም፤ የተለያዩ መርሃግብሮች ናቸዉ፤ በጥቅሉ ግን ቁጥሩ ይህ ነዉ። እነዚህም የWFP የርዳታ መርሃግብር ተጠቃሚዎች ናቸዉ። ገሚሶቹ ኢትዮጵያዉያን፣ ገሚሶቹ ደግሞ ስደተኞች ናቸዉ።»

ከዚህም ሌላ WFP ማንኛዉንም ተግባር ከመንግስት ጋ በቅርበት በመተባበር እንደሚያከናዉንና ያም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገዉን ጥረት እንደሚደግፍ አመልክተዋል። እሳቸዉ ለዘጋቢዎች ያደረጉት ገለፃም ከዘገባዉ እንደሚለይ በመጠቆም በስደተኞች ብዛት ጫና የደረሰባት ኢትዮጵያ ሁኔታ በዓለም ዓቀፍ ለጋሾች ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግ መሞከራቸዉን ገልጸዋል።

አያይዘዉም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በርካታ የጎረቤት ሃገራት ስደተኞችን በማስተናገድ ተግባር መጠመዷን እና በቅርቡም ከደቡብ ሱዳን ብቻ 120 ሺ ስደተኞች ወደኢትዮጵያ መግባታቸዉን አስረድተዋል። በዚያ ላይም የሶማሊያና የኤርትራ ስደተኞች እዚያ እንደሚገኙም ገልጸዋል። በሰሜን ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ወይም አራት ዓመታት በተከታታይ ከወትሮዉ አማካይ የዝናብ መጠን ቀንሶ መታየቱ ሌላዉ በሀገሪቱ ለምግብ እጥረት የሚጋለጡ ሰዎች እንዲኖሩ ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ተገልጿል።

የሮይተስር ዘገባ WFP በምራቃዊ ኢትዮጵያ ክፍል የአንበጣ መንጋ ወረራዉ በአግባቡ ርምጃ ካልተወሰደበት አርብቶ አደሩ ኅብረተሰብ ችግር ሊገጥመዉ እንደሚችል ጠቅሷል። የተመ የስብዓዊ ርዳታ አስተባባሪ በምህጻሩ OCHA ከሁለት ሳምንት በፊት ይፋ ባደረገዉ መሠረትም መካከለኛ የበረሃ አንበጣ በሶማሌ ክልልና በምሥራቅ ሐረር ዞን መታየቱን መንግስትና ተጓዳኝ ድርጅቶችም የመከላከል ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር አመልክቷል። የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ወልደ ሚካኤል ግን ወቅቱ በመሆኑ ስጋቱ መኖሩ ካልሆነ በቀር የአንበጣ መንጋዉ ወደኢትዮጵያ ግዛት አልገባም ነዉ ያሉት። በተቃራኒዉ ትናንት የአንበጣ መንጋ አዲስ አበባ ከተማ ዉስጥ ታይቷል። ዘጋቢያችን ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር የሀገር ዉስጥ የመረጃ ምንጮችን ጠቅሶ እንዳመለከተዉም በምሥራቅ ኢትዮጵያ የአንበጣዉን መንጋ ለመከላከል መድሃኒት ለመርጨት የተሰማሩት አዉሮፕላኖች እክል ስለገጠማቸዉ አንበጦች ወደመዲና አዲስ አበባ ማቅናት መቻላቸዉ ተሰምቷል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic