60ኛ ዓመቱን ያከበረዉ ብሔራዊ ቲያትር | ባህል | DW | 03.12.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

60ኛ ዓመቱን ያከበረዉ ብሔራዊ ቲያትር

በአፍሪቃ ሕብረት መቀመጫ መዲና አዲስ አበባ ላይ ስድስት አስርተ ዓመታትን ያስቆጠረዉ የጥበብ አድባር፤ በርካታ የጥበብ ፈርጦችን አፍርቷል። በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ጉልህ ድርሻ ያበረከቱት አንጋፋ አርቲስቶች ያላቸዉን እዉቀት ለአዲሱ ትዉልድ እያሻገሩ ብሔራዊ ቲያትር ዳግም 60ዓመታት እንዲጨምር የሞያ ትግል የሚያደረጉ ባለሞያዎች ምሥጋና ይገባቸዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 17:14
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
17:14 ደቂቃ

የብሔራዊ ቲያትር 60ኛ ዓመት

በቅርቡ 60ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓልን ያከበረዉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር፤ ከምሥረታዉ ጀምሮ የኅብረተሰቡን

Äthiopien National Theater feiert 60-jähriges Jubiläum Tekle Desta

አርቲስት ደበበ እሸቱና አርቲስት ተክሌ ደስታ

እሴትና ባህል መገንባቱን በቲያትር ቤቱ ያገለገሉና በማገልገል ላይ የሚገኙ ባለሙያዎች ይናገራሉ። «ብሔራዊ ቲያትር ያደጉበት ቤቴ ነዉ» ያለችንን፤ የተውኔት ጸሐፊ፣ የቲያትር አዘጋጅ፣ ተዋናይና ገጣሚ ዓለም ፀሐይ ወዳጆ «ብሔራዊ ትያትር በእድሜ የበለፀገ፤ 60 ዓመት ማስቆጠሩ ብቻ ሳይሆን፤ ክላሲካል የሚባሉ ዛሬ በዓለም ላይ ድንቅ የሚባሉ ትያትሮች፤ እኔ አሁን ከአገር ወጥቄ ተሰድጄ ሳይና ሳወዳድር በዉጭ እንኳ ሊደፈሩ የማይችሉ፤ በዛ ደረጃ ይቀርባሉ ተብሎ የማይታመኑ፤ የነሼክፒርን ወይም ሌሎችን የዓለም ታላላቅ ደራስያን ሥራ ትርጉሞችን በትያትር መልክ ያቀረበ ቤት ነዉ፤ ብሔራዊ ትያትር። መድረኩ አመቺ ነዉ፤ አዳራሹ በዘመናዊ መልክ ተሰርቶ በጣም የተከበረና የተወደደ ቤት ነዉ። ከመሪዎች አቅም እንኳ እያንዳንዱ መሪ እየሄደ ትያትር የሚያይበት የትርኢት ማሳያ ቦታ ነዉ» ስትል ገልፃልናለች። በዕለቱ ዝግጅታችን የዛሬ ስድሳ ዓመት ሕዳር 3, 1948 ዓ,ም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተመርቆ ሥራዉን ስለጀመረዉ ስለቀድሞዉ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የአሁኑ ብሔራዊ ቲያትር የኪነ-ጥበባዊ ኤኮኖሚያዊ ብሎም ማኅበረሰባዊ ጉዞን እንቃኛለን።

ከአገር ፍቅር ቲያትር መመሥረት በኋላ አርበኞች እንዲሁም ሌሎች የቲያትር ባለሙያዎች ሆነዉ «የቲያትር ማስፋፍያ ተቋም» የሚል አቋቁመዉ የመዘጋጃ ቤት ቲያትርን መሥርተዉ ሲሰሩ ትልቅ አዳራሽ በማስፈለጉ የዛሬዉ ብሔራዊ ቲያትር ለመገንባት መብቃቱን አርቲስት ተፈሪ ዓለሙ ይናገራል። አርቲስት ተፈሪ ዓለሙ ስለብሔራዊ ቲያትርና ስለ ሎሪት ፀጋዬ ገብረመድህን የጥናት ፅሑፍ አቅርቦአል።

« ብሔራዊ ትያትር በኢትዮጵያ ትያትር ታሪክ ዉስጥ ትልቅ አስተዋጽዖ ያለዉ ቤት ነዉ። በአገራችን ትያትር መታየት በአገር ፍቅር ቢጀመርም፤ ብሔራዊ ትያትር ደግሞ ጉልህ የሆነና ትልቅ ስም ያለዉ ትያትር ቤት ነዉ። በአጠቃላይ ግን የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ባለቤት የለዉም። ኪነ-ጥበባት መጀመርያ ቀደም ሲል በትምህርት ሚኒስቴር ስር ነበር፤ ከዝያ በባህል ሚኒስቴር ስር ሆንዋል፤ ከዝያም ማስታወቅያ ሚኒስቴር ስርም ሆኖ ነበር። ብቻ ማንም ወሰደዉ ማንም ግን ሥነ-ጥበብም እራሱን የቻለ ባለሥልጣን ይፈልጋል ብዬ አስባለሁ፤ የኢትዮጵያ የሥነ- ጥበባት ባለስልጣን የሚባል መጠርያ ያለዉ ፤ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ቱሪዝም ባለስልጣን ስያሜ ማለቴ ነዉ። ይህ የኔ እምነት ነዉ።»

አዲስ አበባ እንብርት ላይ የሚገኘዉ አንጋፋዉ የኪነ-ጥበብ መድረክ ብሔራዊ ቲያትር ፤ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የኅብረሰቡን አስተሳሰብ በመገንባት የሀገሪቱን ልዩ ልዩ ባህላዊ እሴቶች አጉልቶ በማሳየት ትልቅ ሚና መጫወቱን በዚሁ የቲያትር ቤት መድረክ ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ይገልፃሉ። ከድሮዉ ማዘጋጃ ቤት ለቀዳማዊ ኃይለስላሴ የ 25 ኛ ዓመት የንግስ ክብረ በዓል ሲባል በስማቸዉ ወደ ተሰየመዉ ወደ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ቲያትር ተቀጥረዉ የመጡትና አሁን በጡረታ ላይ የሚገኙት አርቲስት ታደለ ታምራት፤ ስለቲያትር ቤቱ ሥራ አጀማመር በዝርዝር ያስታዉሳሉ። ከቀድሞwwu የመዘጋጃ ቤት ትያትር ፤ ወደ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ትያትር ቤት ተቀጥረዉ ሲመጡም ደሞዛቸዉ አድጎ 25 ብር ሆኖ በዝያን ጊዜ ተደስተዉ እንደነበር አጫዉተዉናል።

Äthiopien Nationaltheater in Addis Abeba

አርቲስት ተክሌ ደስታ

በቀድሞዉ መዘጋጃ ቤት የቲያትርና ሙዚቃ ማስፍያፍያ በ1942 ዓ,ም የተቀጠሩት አርቲስት መራዊ ስጦት ብሔራዊ ቲያትር ከተመሠረተ ጀምሮ አገልግለዋል።

በሰሜን አሜሪካ «ጣይቱ የጥበብ ማእከል»ን አቋቁማ ኢትዮጵያዊ የጥበብ ሥራዎች ከኢትዮጵያዊያን ልቦች እንዳይጠፉ ከሌሎች ኢትዮጵያዉያን የጥበብ አድናቂዎች ጋር በመሆን የምትንቀሳቀሰዉ አርቲስት ዓለም ፀሐይ ወዳጆ ፤ ብሔራዊ ቲያትር ያደኩበት ቤቴ ነዉ ስትል በዝርዝር ገልጻልናለች።

በብሔራዊ ቲያትር በተወዛዋዥነት ተቀጥረዉ በሁለገብ ሙያ በመድረክ ላይ አገልግለዉ በጡረታ የተገለሉት አርቲስት አልጋነሽ ታሪኩ፤ ቲያትር ቤቱ የስድሳኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓሉን ሲያከብር በመድረክ ዝግጅት ተካፋይ በመሆንም አገልግለዋል።

በአሁኑ ወቅት በሰሜን አሜሪካ ዋሽንተን ዲሲ ነዋሪ የሆኑት አርቲስት ተክሌ ደስታ፤ ከ26 ዓመት በላይ እንዳገለገሉ በሰፊዉ አጫዉተዉናል።

አርቲስት ተክሌ እንደገለፁት ስለቀድሞዉ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴም ሆነ ስለአሁኑ ብሔራዊ ቲያትር ቤት ሲወሳ አርቲስት ተስፋዬ ሳህሉ «አባባ ተስፋዬ» እንዲሁም ጌታቸው ደባልቄ፤ በቀዳሚነት ተጠቃሽ መሆናቸዉን በማመስገን ገልፀዋል። እንደ አርቲስት ጌታቸዉ ደባልቄ፤ ከቀድሞ ማዘጋጃ ትያትር ቤት ወደ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ቲያትር ቤት የመጣን አርቲስቶች በሙሉ የቤቱ ባለቤቶች ነበር ሲሉ ተናግረዋል።

በአፍሪቃ ኅብረት መቀመጫ መዲና አዲስ አበባ ላይ ስድስት አስርተ ዓመታትን ያስቆጠረዉ የጥበብ አድባር፤ በርካታ የጥበብ ፈርጦችን አፍርቷል። በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ጉልህ ድርሻ ያበረከቱት አንጋፋ አርቲስቶች ያላቸዉን እዉቀት ለአዲሱ ትዉልድ እያሻገሩ ብሔራዊ ቲያትርን ዳግም ስድሳ ዓመታትን ጨምሮ በባህላዊ ፤ በማኅበረሰባዊ ግንኙነት እንዲሁም በኤኮኖሚም አብቦ የአገር ቅርስ ሆኖ እንዲጠራ ምኞታችንን እንገልፃለን ያሉንን የኪነ-ጥበብ ሰዎች ለሰጡን ቃለ ምልልስ በዶቼ ቬለ ስም እያመሰገንን፤ ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic