60ኛው የጋና ነፃነት እና ክዋሜ ንክሩማህ | አፍሪቃ | DW | 04.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

60ኛው የጋና ነፃነት እና ክዋሜ ንክሩማህ

ጋና ከሁለት ቀናት በኋላ 60ኛ የነፃነት ዓመት ለማክበር ዝግጅት ይዛለች። ሀገሪቱን ለነፃነት ላበቁት የመጀመሪውያ የሀገሪቱ ፕሬዚደንት እና መስራች አባት ክዋሜ ንክሩማህ ጋናውያን የተለያየ አመለካከት ነው ያላቸው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:38

ክዋሜ ንክሩማህ

ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ጋና እጎአ መጋቢት ስድስት፣ 1957 ዓም ከብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ በመላቀቅ ነፃነቷን በተጎናፀፈችበት ጊዜ ከደጋፊዎቻቸው እና ከሰፊው የሀገሪቱ ሕዝብ ትልቅ አድናቆት የተደረገላቸው ንክሩማ የበኩላቸውን ደስታ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል።
« ከረጅም ጊዜ በኋላ ይኸው አሁን በመጨረሻ  ጦርነቱ አብቅቷል። እናም ተወዳጇ ሀገራቸው ጋና ለዘላለም ነፃ ሆናለች። »  
የጋና መስራች አባት የሚባሉትን የመጀመሪያውን የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ክዋሜ ንክሩማን በተመለከተ ዛሬ ከ60 የነፃነት ዓመታት በኋላ ያለው አስተሳሰብ ግን ከዚያን ጊዜው የተለየ ነው። ጋና የነፃነት ዓውድ ዓመት ከሁለት ቀናት በኋላ በምታከብርበት ጊዜ  የቀድሞው የሀገሪቱ  ክዋሜ ንክሩማ የሚለው ስም በ27 ሚልዮኑ የሀገሪቱ ሕዝብ ዘንድ የተለያየ ስሜት እና አስተሳሰብ መቀስቀሱ እንደማይቀር በመዲናይቱ አክራ የሚገኘው የጋና ዩኒቨርሲቲ መምህር አትሱ አይሬ ከዶይቸ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስታውቀዋል።
« ክዋሜ ንክሩማ የሚለው ስም በሚስጢር እና በአከራካሪ ጉዳዮች የተተበተበ ነው። »


ክዋሜ ንክሩማ የመሩት መንግሥት ከነፃነት በኋላ በተከተሉት የመጀመሪያዎቹ የስልጣን ዓመታት ፣ በተለይ በግብርናው ላይ ጥገኛ የሆነችውን ሀገራቸው ወደ ኢንዱስትሪያዊው ዘርፍ የሚያሸጋግራት /// የኤኮኖሚ መርሀግብር ማነቃቃቱ ይታወሳል። በዚሁ እቅዱ መሰረት፣ በቮልታ ወንዝ  የተጀመረው ፕሮዤ  ዛሬም ለጋና ዋነኛው የኤሌክትሪክ አቅራቢ መሆኑ ይነገራል። ይሁንና፣  መንግሥት ካነቃቃቸው ሌሎቹ ግዙፍ ፕሮዤዎች መካከል ብዙዎቹ ለክሽፈት ተዳርገዋል፤ በመንግሥት ስር የነበሩት ትልልቆቹ ተቋማትም በሙስና እና በተሳሳተ አስተዳደር ምክንያት በመንግሥት ላይ ግዙፍ ዕዳ አስከትለዋል። 
ሁኔታዎች አዳጋች እየሆኑ በቀጠሉበት ጊዜ  የጋና ሕዝብ  ለነፃነት ጠንክረው የታገሉለት ንክሩማ ሌላ ገፅታም እንዳላቸው ለማየት ቻለ። ንክሩማህ እጎአ በ1964 ዓም በተቀየረው የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት እጎአ በ1949 ዓም ያቋቋሙት በምህፃሩ «ሲ ፒ ፒ የተባለውን ሶሻሊስታዊውን የ« ኮንቬንሽን ፒፕልስ ፓርቲ»  ብቸኛው ሕጋዊ ፓርቲ አድርገው በጋና የአንድ ፓርቲ አስተዳደር አስተዋወቁ፤ ራሳቸውንም የዕድሜ ልክ ፕሬዚደንት ሲሉ መሰየማቸው ይታወሳል። በዚሁ ጊዜ ወደ 10,000 የሚጠጉ የጋና ዜጎች፣ ምሁራን ጭምር  ይህን ፈላጭ ቆራጭ እየሆነ የሄደውን የንክሩማህ አገዛዝ በመሸሽ ወደ ውጭ ሀገራት ተሰደዱ። የጋና ኤኮኖሚ እየወደቀ የሄደበት ሁኔታም በሕዝቡ ዘንድ ሲብላላ የቆየውን ቁጣ እንዲገነፍል ምክንያት ሆኖ፣ ንክሩማ እጎአ በ1966 ለጉብኝት ወደ ቻይና በተጓዙበት ጊዜ ወታደሮች ባካሄዱት መፈንቅለ መንግሥት ከስልጣን ተወግደዋል። የ« ኮንቬንሽን ፒፕልስ ፓርቲ»  ም በሕግ ታግዷል።
ይሁን እንጂ፣ ክዋሜ ንክሩማ የተከተሉት ፖለቲካ ጋና መረጋጋቷን ጠብቃ ለቆየችበት ድርጊት ሰፊ ድርሻ ማበርከቱን የፖለቲካ ተንታኞች አስታውቀዋል። የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር አትሱ አይሬ እንዳስረዱት፣ ምንም እንኳን የጦር ኃይሉ እጎአ በ1970 ኛዎቹ እና 1980ኛዎቹ ዓመታት ተደጋጋሚ መፈንቅለ መንግሥት ቢያካሂድም ጋና እንደ ሌሎቹ ጎረቤት ምዕራብ አፍሪቃውያት ሀገራት ቀውስ ውስጥ አልወደቀችም።  
«   ንክሩማ ስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ባስተዋወቁት የብሔረተኝነት እና የሀገር ወዳድነት አስተሳሰብ የሚታወሱ ይመስለኛል። የአንድ ሀገር ባለቤት መሆን እና ይህችም ሀገር የተረጋጋች መሆን እንደሚኖርባት ባስፋፉት ስሜትም ይታወሳሉ። »
ይህ እውነታ ግን በወቅቱ እየደበዘዘ በመሄድ ላይ ነው። እርግጥ፣ ዛሬም ብዙ ተማሪዎች በመዲናይቱ አክራ የሚገኘውን የክዋሜ ንክሩማ መካነ መቃብር ይጎበኛሉ። ይሁንና፣ ንክሩማ ማን እንደነበሩ እና ለጋና እንደ ፕሬዚደንትም ሆነ ከነፃነቱ በፊት በጠቅላይ ሚንስትርነት ስልጣናቸው የሰሩትን ወይም በዚያን ጊዜ የሆነውን በትክክል የሚያውቁት ጥቂቶች ብቻ መሆናቸውን በአክራ የሚገኘው የጀርመናውያኑ የኮንራድ አድናወር የፖለቲካ ጥናት ተቋም ኃላፊ ክርስትያን ዴሞክራቱ ቡርክሀርት ሄለማን ገልጸዋል።

Ghana Öl Sie werden profitieren: Schüler auf dem Platz der Unabhängigkeit in Accra Foto: Stefanie Duckstein / DW


« በኔ አመለካከት፣  ንክሩማ አሁንም በጋና በርግጥ የሚጫወቱት ሚና አለ። ይሁንና፣ ይህ ሚናቸው የመጀመሪያው የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ከመሆናቸው እና ሀገሪቱንም ለነፃነት ካበቁበት ታሪካዊ  ክስተት  ጋር የተያያዘ ነው። ከሀገሪቱ ሕዝብ መካከል ትልቁን ከፊል በሚሸፍነው ወጣት የጋና ትውልድ ዘንድ ግን ክዋሜ ንክሩማ፣ የህይወት ታሪካቸውም ሆነ እንደ ፕሬዚደንት የያከናወኑት ተግባር  ያን ያህል እንደማይታወቅ መናገሩ ተገቢ ነው። ክዋሜ ንክሩማ የተከተሉት ፖለቲካም  ወቅት ያለፈበት እና በአሁኑ የጋና ጊዚያዊ ሁኔታ ውስጥ አንዳችም ቦታ የለውም። »
እንደ ቡርክሀርት ሄለማን አስተሳሰብ፣ የክዋሜ ንክሩማህ የ« ኮንቬንሽን ፒፕልስ ፓርቲ» ዛሬ በጋና የፖለቲካ መድረክ ውስጥ ንዑስ ሚና ብቻ ነው የያዘው።
በዚህ አንፃር ክዋሜ ንክሩማህ ከሰሀራ በስተደቡብ በሚገኙት አፍሪቃውያት ሀገራት ውስጥ አሁንም ዝናቸው ትልቅ ነው። «ኒው አፍሪካን» የተባለው  ወርሀዊ መጽሄት እጎአ በ2004 ዓም  አንባብያን በአፍሪቃ የሚያደንቁትን ትልቅ የሚሉትን መሪ እንዲመርጡ ጥያቄ ባቀረበበት ጊዜ ከቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት እና ከፀረ አፓርታይድ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ቀጥለው ንክሩማህን በሁለተኛ ደረጃ ማስቀመጣቸው አይዘነጋም። 
አንድ የሆነች አፍሪቃ የመፍጠር፣ የአፍሪቃውያን ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ነፃነት ማጠናከርን ታሳቢ ያደረገውን ተራማጅ ባህርያት የነበሩትን የፖለቲካ አጀንዳ ወይም «ፓን አፍሪካኒዝም» ህልም የነበራቸው ንክሩማህ በጊዜአቸው በአፍሪቃ ከፍተኛ ተፅዕኖ ካሳረፉ የፖለቲካ መሪዎች መካከል አንዱ ነበሩ። በጋና የነፃነት በዓል ወቅት በአክራ ለተሰበሰበው ሕዝብ አፍሪቃውያን የራሳቸው መሪዎች ይሆናሉ የሚል  መልዕክት ነበር ያስተላለፉት።
« ዛሬ በዓለም አዲስ አፍሪቃዊ ተፈጥሯል። ይህ አፍሪቃዊ የራሱን ትግል ለመታገል እና ጉዳዮቹንም ራሱ ለማስተዳደር ዝግጁ ሆኗል። »

በዩኤስ አሜሪካ፣ የቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ ስነ አፍሪቃ ትምህርት ፕሮፌሰር የሆኑት ናይጀሪያዊው የታሪክ ምሁር ቶይን ፋሎላ ለዶይቸ ቬለ እንዳስረዱት፣ አንድ የሆነች  አፍሪቃ የምዕራባውያን ተፅዕኖን በቀላሉ ልትቋቋም ትችላለች የሚሉት ከአፍሪቃ አንድነት ድርጅት መስራች አባቶች አንዱ የነበሩት ንክሩማህ አህጉራዊ አንድነት አስተሳሰብ ዛሬም በአፍሪቃ ህብረት ሲነሳ እንደሚሰማ፣ ግን እንደቀድሞው አልገነነም። 
ባሁኑ ጊዜ፣ ማለትም፣ የቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ታቦ ምቤኪ፣ የቀድሞው የናይጀሪያ መሪ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ የስልጣን ዘመናቸውን ካበቁ ወዲህ፣ ይህን አስተሳሰብ የሚያራመዱ ጠንካራ አፍሪቃውያን መሪዎች የሉንም።  ዛሬ፣ እያንዳንዷ ሀገር የራሷን ጥቅም በማስጠበቁ እና ፖለቲካዋን በማራመዱ ላይ ትኩረቷን ከማሳረፏ ሌላ፣ እድገቱ እየቀነሰ የሄደው የኤኮኖሚ ሁኔታም አብዝቶ ያሳስባታል። በዚህም የተነሳ ትልቁ የ«ፓን አፍሪካኒዝም» ፕሮዤ ወደ ጎን ተብሏል።

ዳንየል ፔልስ/አርያም ክሌ

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች