5,500 ዶላር ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህፃናት ሕክምና ክፍል ምን ይገዛል? | ኤኮኖሚ | DW | 30.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

5,500 ዶላር ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህፃናት ሕክምና ክፍል ምን ይገዛል?

ሁለት ኢትዮጵያውያን ዶክተሮች ጎ ፈንድሚ በተባለው የገቢ ማሰባሰቢያ ድረ-ገፅ በኩል ለጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕፃናት የሕክምና ክፍል የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ለመግዛት ጥረት እያደረጉ ነው። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:05

ጥቁር አንበሳ በሕፃናት ሕክምና ከፍተኛ ጫና አለበት

ፖለቲካዊ ክርክሮች በሚበረቱባቸው ፌስቡክ እና ትዊተርን በመሳሰሉ ማኅበራዊ ድረ-ገፆች ሁለት የሕክምና ባለሙያዎች ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሕፃናት ሕክምና ክፍል ገቢ ለማሰባሰብ ብቅ ብለዋል። ጎ ፈንድ ሚ በተባለው የገቢ ማሰባሰቢያ ድረ-ገጽ ሁለቱ ዶክተሮች በጀመሩት ዘመቻ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከ20 እስከ 100 ዶላር አዋጥተዋል። ዘመቻው በአንድ ወር ውስጥ ከ2, 300 ዶላር በላይ አሰባስቧል። የሁለቱ ወጣት ዶክተሮች እቅድ 5,500 ዶላር መድረስ ነው። የሐሳቡ ጠንሳሽ ዶክተር ትንሳኤ አለማየሁ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሕፃናት ሕክምና ባለሙያ እና መምህር ናቸው። በረዳት ፕሮፌሰር ማዕረግ የቅድመ እና ድኅረ ምረቃ ተማሪዎችን ያስተምራሉ። ዶክተር ትንሳኤ እንደሚሉት ለሕፃናት በተዘጋጀው የሕክምና ክፍል የታዘቡት የአስፈላጊ ቁሳቁሶች እጥረት በግለሰባዊ ጥረት መፍትሔ እንዲያማትሩ አስገድዷቸዋል። 
ጥቁር አንበሳ የኢትዮጵያ ትልቁ የሕክምና ተቋም ብቻ ሳይሆን ስመ-ጥር ትምህርት ቤት ጭምር ነው። የእነ ዶክተር ትንሳኤ ገቢ ማሰባሰቢያ መረጃ እንደሚጠቁመው በሆስፒታሉ የሚገኘው የሕፃናት የሕክምና ክፍል በዓመት ለ11,000 ሕፃናት እና አዋቂዎች ግልጋሎት ይሰጣል። ማዕከሉ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለሚመጡለት ሕሙማን ሕፃናት ይኸንንው ግልጋሎት ያቀርባል። 
ዶክተር ፍጹም ጥላሁን በዘመቻው ከሚሳተፉ መካከል ናቸው። የሕክምና ባለሙያው በዩኤስ አሜሪካ በውስጥ ደዌ ሕክምና ሙያ ተጨማሪ ሥልጠና ወስደው ወደ ማጠናቀቁ ተቃርበዋል። ዶክተር ፍጹም የገቢ ማሰባሰቢያው ጥቁር አንበሳን በሚያክል ግዙፍ ሆስፒታል ውስጥ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚካሔድ አይደለም ሲሉ ይናገራሉ። ይልቁን በግለሰባዊ ጥረት ትንንሽ ችግሮችን ለመፍታት ያለመ እንደሆነ ያስረዳሉ።

ዶክተር ትንሳኤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ 45 ከመቶ ገደማ ዕድሜያቸው ከ15 አመት በታች መሆኑን እየጠቀሱ የሕፃናት ሆስፒታሎች ቁጥር አናሳ መሆኑን ይናገራሉ። ይኸ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ላይ ያለውን ጫና የከፋ ያደርገዋል። ለሕፃናት ሕክምና ብቻ የሚያገለግሉ ሆስፒታሎች ያስፈልጋሉ የሚሉት የሕክምና ባለሙያው እርሳቸው የሚሰሩበት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በተለይ በአዲስ አበባ ዙሪያ ነዋሪዎችን በማገልገል ረገድ ከፍተኛ ሸክም እንደተጫነበት ይገልፃሉ። 

ሁለቱም ዶክተሮች ለሕክምናው ክፍል የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች እጥረት አለ እያሉ ከማማረር ይልቅ ግለሰባዊ ጥረቶች ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያምናሉ። ፖለቲካዊ ርዕሰ-ጉዳዮች የበለጠ ቀልብ በሚስቡባቸው የማኅበራዊ ድረ-ገፆች በኩል የሚደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ ሊጠናቀቅ ጊዜያት ይቀሩታል። ዶክተር ፍጹም መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የግለሰቦች ትናንሽ ጥረቶች ከፍ ያለ ሚና እንደሚኖራቸው እምነታቸው ነው። 
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ 
እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ 

Audios and videos on the topic