1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

500 ሺሕ ለሚሆኑ ዉጤታማ ላልሆኑ ሰራተኞች ደምወዝ ይከፈላ

ማክሰኞ፣ መስከረም 29 2011

ኢትዮጵያ ለመንግሥት ሰራተኞች ከምትመድበው 18 ቢሊዮን ብር ውስጥ ስድስት ቢሊዮን የሚሆነው ውጤታማ ላልሆኑ ሰራተኞች የሚከፈል መሆኑን የኢትዮጵያ የሥራ አመራር ኢንስቲቲዩት አስታውቋል። ማዕከሉ የመንግሥት ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች በስብሰባ እና በደራሽ ሥራዎች ተጠምደው ውጤታማ መሆን እንደተሳናቸው በጥናት ማረጋገጡን ገልጿል።

https://p.dw.com/p/36Eu4
Karte Ethiopia und Eritrea ENG

አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ከሚሆነው የኢትዮጵያ የመንግሥት ተቀጣሪ መካከል አንድ ሶስተኛው ውጤታማ የሚባል ሥራ ሳይከውን ደሞዝ እንደሚከፈለው የኢትዮጵያ የሥራ አመራር ኢንስቲቲዩት አስታወቀ። የሥራ አመራር ማዕከሉ ከዚህ መደምደሚያ የደረሰው የኢትዮጵያ መንግሥት ተቋማትን የጊዜ አጠቃቀም አጥንቶ እንደሆነ አስታውቋል። 

በኢትዮጵያ የመንግሥት ተቋማት 1.5 ሚሊዮን ገደማ ሰራተኞች እንደሚገኙ የገለጹት የኢትዮጵያ የሥራ አመራር ኢንስቲቲዩት ዋና የሥራ አማካሪ አቶ አሸናፊ አበራ "ከዚህ ውስጥ አንድ ሚሊዮን ብቻ ውጤታማ የሆነ ተግባር ላይ የተሰማራ ሲሆን 500 ሺሕ ያክሉ ግን ምንም አይነት ውጤታማ የሆነ ሥራ ሳይሰራ የሚከፈለው" መሆኑን ተቋማቸው በሰራው ጥናት መረጋገጡን ተናግረዋል። በዚህም ኢትዮጵያ ለመንግሥት ሰራተኞች ደሞዝ ከምትበጅተው 18 ቢሊዮን ብር ስድስት ቢሊዮን ገደማ የሚሆነው ውጤታማ ላልሆነ ሥራ የሚከፈል ወይንም የባከነ መሆኑን አቶ አሸናፊ ጨምረው ተናግረዋል። ዋና አማካሪው በመንግሥት ላይ የሚደርሰው የስድስት ቢሊዮን ብር አመታዊ ኪሳራ "በፕሮጀክቶች መዘግየት እና በዋጋ መጋሸብ የሚመጣውን የገንዘብ ኪሳራ፤ በተገልጋዮች ላይ የሚደርሰውን መጉላላት እና የእርካታ ማጣት" እንደማይጨምር ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ተቋማትን እና የመንግሥት ሰራተኞችን ለጊዜ አጠቃቀም ብኩንነት ከዳረጓቸው አበይት ጉዳዮች መካከል አንዱ ስብሰባ መሆኑን ይኸው ጥናት ጠቁሟል። ጥናቱን ዋቢ አድርገው ማብራሪያ የሰጡት አቶ አሸናፊ እንደሚሉት "በፐብሊክ ሰርቪሱ ውስጥ የተንዛዛ ስብሰባ፣ አጀንዳ የሌለው ስብሰባ ውሳኔ የማይወሰንባቸው ስብሰባዎች" ተበራክተዋል። አቶ አሸናፊ እንደሚሉት ሰራተኞች እና ከፍተኛ አመራሮች "ስብሰባዎቻቸውን ከአቅም ማነስ የተነሳ መደበቂያ" አድርገዋቸዋል።  
የመንግሥት ሰራተኞች ከበላይ ሹማምንቶቻቸው በሚሰጧቸው ደራሽ ሥራዎች መጠመዳቸው ለጊዜ ብክነት ከዳረጓቸው ጉዳዮች መካከል እንደሚገኙበት ባለሙያው ገልጸዋል። አቶ አሸናፊ "ከበላይ አካል፤ ከበላይ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የሚመጡ ድንገተኛ የፖለቲካ እና የኮሚቴ ሥራዎች ሰራተኞች እና አመራሩ በተቋሞቻቸው ሥራ ላይ እንዳያተኩሩ አድርጓቸዋል" ሲሉ ያብራራሉ።  

የመንግሥት የማሻሻያ ውጥኖች የወረቀት ሥራ ሆነው መቅረታቸው፤ የተንዛዛ የምሳ እና የሻይ እረፍት፣ ዘግይቶ ሥራ መጀመር፣ ቀድሞ ከሥራ ገበታ መውጣት በጥናቱ ከተለዩ ችግሮች መካከል እንደሚገኙበት አቶ አሸናፊ አስረድተዋል። ፌስቡክን የመሳሰሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አጠቃቀም፣ ስልክ እና ኢ-ሜይል በሰራተኞች የሰዓት አጠቃቀም ላይ ጫና ማሳደራቸው ተጠቅሷል። 

የኢትዮጵያ መንግሥት ውጤት አልባ እና ተደጋጋሚ ስብሰባዎች በለት ተለት የተቋማት የሥራ ክንውን ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ አገር አቀፍ የስብሰባ መመሪያ ቢዘጋጅም በተግባር የፈየደው ነገር አለመኖሩን አቶ አሸናፊ አስረድተዋል። አቶ አሸናፊ በመመሪያው "እንዴት አጀንዳ ይመረጣል? እንዴት ቃለ ጉባኤ ይያዛል? ስብሰባን እንዴት አጭር ውጤታማ ማድረግ ይቻላል? የሚል ወጥቶ ለመንግሥት ተቋማት ሁሉ ተበትኖ ስልጠና ተሰጥቷቸው እየሰሩበት ነው። ግን አሁንም ውጤታማ ያልሆነ ስብሰባ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ትልቅ ችግር እያስከተለ ነው" ሲሉ የችግሩን ጥልቀት አስረድተዋል። 

ተጠያቂነት ከወዴት አለ?

የኢትዮጵያ የመንግሥት ተቋማት አመራሮች፤ ሰራተኞች እና የመፈተሽ ኃላፊነት የተጣለባቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን የመሳሰሉ ተቋማት የሥራ አፈፃጸምን በጥልቀት ሳይመረምሩ መቅረታቸውን ጥናቱ እንደደረሰበት አቶ አሸናፊ ጠቁመዋል። "ከተወካዮች ምክር ቤትም ከፐብሊክ ሰርቪስ ሚኒስቴርም ለቁጥጥር የሚወጡ ሰዎች ማሻሻያው በሥርዓት በጊዜ በወጪ ምን አመጣ የሚለውን ሳይሆን በር ላይ የተለጠፉ ነገሮችን በማየት፣ ቃለ ጉባኤዎችን በመቁጠር የመልካም አስተዳደር ችግር ለይተናል፤ ተሰብስበናል የሚሉትን ብቻ በማየት" ተቋማቱን በአግባቡ ሳይፈትሹ መቅረታቸውን ገልጸዋል።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ