50ኛዉ የአልጀሪያ የነፃነት በዓል | አፍሪቃ | DW | 05.07.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

50ኛዉ የአልጀሪያ የነፃነት በዓል

የዛሬ 50ዓመት ነዉ አልጀሪያ ከፈረንሳይ ግኝ ተገዥነት ተላቃ ነፃነቷን የተቀዳጀችዉ። መንግስት ይህን ዕለት ለመዘከር በጀት መድቦ በዋና ከተማዋ በዓል ደግሷል። ዕለቱንም በታሪክነት ለማስታወስ 50ኛዉን የነፃነት በዓል የሚገልፅ ሳንቲም ተዘጋጅቷል።

በአንፃሩ አብዛኛዉ ህዝብ የሀገሪቱ ፖለቲካ ምንም አልተሻሻለም የሚል እምነት አለዉ። ይህም የነፃነት ቀንን አስመልክቶ ህዝቡ ያን ያህል የፈንጠዝያና የበዓል ስሜት እንዳልታየበት ነዉ የተሰማዉ። ካስባህ በተባለዉ የአልጀሪያ ዋና ከተማ አልጀርስ ጥንታዊ የከተማ ክፍል በጠባቡ መተላለፊያ መንገድ ላይ ልጆች የእግር ኳስ ይጫወታሉ። ካመል ኦስማን በሃሳብ እንደተዋጠ ይመለከታቸዋል። ወቅቱ ልጆቹ ፍፁም የማያዉቁት በሀገሪቱ ለየት ያለ ታሪክ የተከናወነበት ነዉ። አልጀሪያ ወደኋላ 50ዓመት ዞራ ነፃ የወጣችበትን ቀን ትቃኛለች። ካመል ኦስማን ነገሮች እንዴት ወዳልተጠበቀ መንገድ ሊሄዱ ቻሉ ሲል ራሱን ይጠይቃል፤

«ይህች ሀገር በልፅጋ አታዉቅም ህዝቦቿም ከድህነት ተላቀዉ አያዉቁም። በየዓመቱም ሁኔታዉ ይባስ እየከፋ ነዉ የሚሄደዉ። እዚህ የሚራቡ ሰዎች አሉ፤ መድሃኒት በማጣትም የሚሞቱ ሰዎች አሉ። ይህ እኔ በፍፁም የማይገባኝ ጉድ ነዉ። የአመራር ችግር አለብን፤ አዛዉንቱ በጡረታ መሰናበት ይኖርባቸዋል፤ ያኔ ላደረጉልን ነገር ሁሉ እናመሰግናቸዋለን። አሁን ግን የአስተዳደር ችግር ስላለ ብቃት ያላቸዉ ወጣት ምሁራን ያስፈልጉናል።»

ካመል ኦስማን በሰላሳዎቹ የእድሜ አጋማሽ የሚገኝ፤ ፈረንሳይ ዉስጥ ትምህርቱን አጠናቆ ወደሀገሩ የተመለሠ ወጣት የኤኮኖሚ ባለሙያ ነዉ። ሀገሩ ላይ ባለዉ እምነትም የዉጭ ባለሃብቶችን ወደዚያ ለመሳብ ጥረት ያደርጋል። እምቅ የወጣት ሠራተኛ ኃይል በሃብትነት ያላት ሀገሩ ወደምድራዊ ገነትነት ልትለወጥ ትችላለች ብሎም ያስባል። ከአልጀሪያ ህብብ አንድ አራተኛዉ ከ15 ዓመት እድሜ በታች የሚገኝ ትዉልድ ነዉ። እንዲያም ሆኖ የእርሱ አዎንታዊ አመለካከት ገደብ አለዉ፤

«የአልጀሪያ በእድሜ ጠገብ ምሁራን መልካም አርአያ ሊሆኑ አይችሉም። ከሥራ ሲሰናበቱ ወይ ወደዉጭ ሀገር ይሄዳሉ አለያም ሙስና ዉስጥ ይዘፈቃሉ። እንዴት ነዉ እነሱ ወጣቱን ሊቀርፁ የሚችሉት? የታል የስኬት ታሪካችን? የታል የእኛ ቢል ጌትስ? ስነምግባርና ብቃት ያላቸዉ ሰዎቻችን ከፊት መታየት ይኖርባቸዋል። ስኬት መኖር አለበት፤ ያኔ ሁሉም ነገር ይስተካከላል። ይህንንም ለመሞከር ወኔዉ ሊኖር ይገባል።»

ካመል አገሬዉ ሃራጋ ስለሚላቸዉ ወጣት ወንዶች ጉዳይ ብዙ ያዉቃል። እነዚህ ወጣቶች ሥራ የላቸዉም፤ ከተስፋ መቁረጣቸዉ የተነሳ የይለፍ ሰነዳቸዉን በማቃጠል ወደአዉሮጳ ለመሻገር ጀልባዎች ላይ ይሳፈራሉ። ለምን ይህን እንደሚያደርጉ እሱ ይረዳቸዋል። አልጀሪያ ዉስጥ የሥራ አጡ ቁጥር 20 በመቶ ደርሷል፤ በተለይ ወንዶቹ በዚያች ሀገር የሚያዩት ተስፋ ሰጪ ነገር የለም። የዛሬ 50ዓመት ሀገሪቱን የመሩት ዓይነት አያት ቅድመ አያቶቻቸዉን ዛሬ ያልሟቸዉ እንጂ በገሃድ አያገኟቸዉም።

Proteste in Algerien

የአልጀሪያ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ

አሁን ስልጣን ላይ የሚገኙት ፖለቲከኞች የሀገሪቱን የነዳጅና የጋዝ ሃብት በቁጥጥራቸዉ ሥር ያደረጉ ለራሳቸዉ የበለፀጉ ናቸዉ። በሰሜን አፍሪቃና በመካከለኛዉ ምስራቅ የተቀጣጠለዉ ህዝባዊ አመጽ ያሰጋቸዉ እነዚህ የአልጀሪያ መሪዎች ተቃዉሞዉን እያረጋጉ ማኅበራዊ ሰላም ለመፍጠር ሲጥሩ ታይተዋል። እንዲያም ሆኖ ቁጣዉ ዕለት ከዕለት እያደገ መምጣቱ ነዉ የሚታየዉ። በአዉሮጳዉያኑ 1990ዎቹ የታየዉ የእርስ በርስ ጦርነት እንዳይደገም የሚሰጉ ቢኖሩም አመፁ ከዋና መዲናዋ ተነስቶ ወደሌሎች አካባቢዎችም እንዲዛመት የሚሹ ግን አልተጠፉም። አብድራህማን አንዱ ነዉ፤

«መኖሪያ ቤቶች ያስፈልጉናል፤ ሥራም እንፈልጋለን፤ እንዲሁም ላንዴና ለመጨረሻ እንደሰዉ መኖርን እንሻለን። የሚለወጥ ነገር ካልኖረ፤ ፖለቲከኞች የሚሠሩት ነገር ከሌለ፤ ከእንግዲህ ለረዥም ጊዜ መጠበቅ አንጠብቅም። በሆነ መንገድ አንድ ቀን አልጀሪያ ዉስጥ ያበጠዉ ይፈነዳል።»

የአልጀሪያ የፖለቲካ ሁኔታ ስጋት ያጥላበት ወይ ተስፋ ይኑረዉ አሁን ሊነገር የሚችል ነገር ያለ አይመስልም። አንድ ነገር ግን ሃቅ ነዉ፤ የተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ያባባሱት የታመቀ ቁጣ ጥልቀቱ የዋዛ አይመስልም። ይህን መሰሉን ስሜት በዉስጧ ይዛም ዛሬ አልጀሪያ ለ132ዓመት በፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ቀንበር ሥር ቆይታ ከአዉሮጳዉያኑ 1954 እስከ 1962ዓ,ም ድረስ ተዋግታ ነፃነቷን ያገኘችበትን 50ኛ ዓመት ዘክራለች።

አሌክሳንደር ጉብል

 ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic