490 ኢትዮጵያውያን ከየመን ወጡ | ኢትዮጵያ | DW | 31.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

490 ኢትዮጵያውያን ከየመን ወጡ

ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት 490 ኢትዮጵያውያንን በጦርነት ከምትታመሰው የመን ማስወጣቱን አስታወቀ። ከስደተኞቹ መካከል 101 ታዳጊዎች እና አንድ ህጻን ይገኙበታል። ኢትዮጵያውያኑ በየመን እስር ቤቶች እና የማቆያ ጣቢያዎች ውስጥ የነበሩ ናቸው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:21
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:21 ደቂቃ

ኢትዮጵያውያን ከየመን

የ25 አመቱ ወጣት አሊ የመን ውስጥ ከሚተዳደርበት የጫት ንግድ ሥራ ታግቶ ለማስፈታት ሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ ቤተሰቦቹ 10,000የሪያል (2,700 ዶላር) ከፍለዋል። አሊ ከታገበት ሲፈታ ራሱን እንደ እድለኛ ቆጥሯል።

«አጋቾቹ የወንዶችን አይን በቢላ ሲወጡ ተመልክተናል።ከአንዳንዶቹ ጀርባ ላይ ፕላስቲክ ያቀልጡባቸዋል፤አንድ ወጣት ክፉኛ በመደብደቡ ምክንያት የደረቱ አጥንቶች እና እጁ ተሰባብረዋል።» ሲል በእገታ በቆየበት ጊዜ የተመለከተውን ዘግናኝ ድርጊት የሚያስታውሰው አሊ በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት አማካኝነት በጦርነት ከታመሰችው የመን ከወጡ 490 ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ነው።

በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የክትትል እና ኢቫሉዌሽን ባለሙያ የሆኑት አቶ አብርሐም ታምራት በየመ የሚገኙ ስደተኞች ሲታገቱ ግርፋት፤እንግልት እንደሚፈጸምባቸው ተናግረዋል። በደረሰባቸው ስቃይ የሞቱ እንደሚገኙም ባለሙያው ተናግረዋል። ስደተኞቹ ሲታገቱ በኢትዮጵያ አሊያም በሳዑዲ አረቢያ ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እንዲልኩ ተደውሎ ይነገራቸው። አቶ አብርሐም «እስከሶስት ጊዜ የላኩ ቤተሰቦች መኖራቸውን አረጋግጠናል» ይላሉ።

በየመን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ለዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ሰራተኞች ጭምር አስጊ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አብርሐምታምራት ከየመን እና የሳዑዲ አረቢያ መንግስታት ጋር በመተባበር ስደተኞቹ መውጣታቸውን ተናግረዋል። ድርጅቱ ከየመን ሖዲዳህ የባህር ወደብ ወደ ጅቡቲ ከዛም በአውቶቡስ ወደ ኢትዮጵያ 490 ስደተኞችን ማጓጓዙን ያረጋገጡት አቶ አብርሐም «በቀጣይ ቅዳሜ እና እሁድ ደግሞ 250 ሰዎችን ለመመለስ እንቅስቃሴ ላይ እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል። ድርጅቱ በየመን ከሚገኙ ስደተኞች መካከል 1,212ስደተኞችን ለመመለስ አቅዷል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅር የስደተኞች ኮሚሽን መረጃ መሰረት በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም ብቻ ከ92,000 በላይ ስደተኞች ወደ የመን ተጉዘዋል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ 89%ኢትዮጵያውያን ሳይሆኑ እንደማይቀር ኮሚሽኑ ጨምሮ አስታውቋል። አቶ አብርሐም ታምራት ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት ስደተኞች የሚሰማሩባቸውን የስራ ዘርፎች ለማመቻቸት ተቋማቸው ጥረት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic