1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

4 ሺህ ተጨማሪ ሃይል በሶማሊያ ሊሰማራ ነው

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 15 2003

የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በሶማሊያ የተሰማራው የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሰራዊት ቁጥሩ በአራት ሺህ እንዲጨምር ወሰነ። የሰራዊቱ የቆይታ ጊዜ በ8 ወራት እንዲራዘምም ምክር ቤቱ ወስኗል።

https://p.dw.com/p/Qk3G
ምስል AP

መንግስት አልባ ከሆነች ሃያ ዓመቷን ደፈነች። እስከአሁን ማዕከላዊ መንግስት ሳይኖራት በጦር አበጋዞችና በአክራሪዎች ፍትጊያ እንደታመሰች አለች -ሶማሊያ። የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ያለው የሽግግሩ መንግስት ሀገሪቱን ማረጋጋት ይቅርና ለራሱም መቆም ሳይችል ፤ ከእስላማዊ ቡድኖች በተለይም ከአሸባብ የሚሰነዘርበትን ዱላ መመከት ያቃተው ሆኖ ቆይቷል። የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ጦር በእርግጥ የሽግግር መንግስቱ እንዳይወድቅ ጋሻ መከታ ሆኖ እየጠበቀው ነው። ከኡጋንዳና ከቡሩንዲ የተወጣጣውና 8 ሺህ አባላት ያሉበት የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሰራዊት አንዳንድ ጊዜ ከተሰጠው ስልጣን እያፈነገጠ የሽግግር መንግስቱን ለመጠበቅ የሞት ሽረት ትግል ማድረጉ የተለመደ ግን እያወዛገበ ያለ ጉዳይ ነው። የሰላም አስከባሪው ሰራዊት አቅሙ ውሱን በመሆኑ ከሞቃዲሾ አንድ ክፍል ሆኖ የሽግግር መንግስቱን ከመጠበቅ ሲልም ተዋግቶ ከማስጣል ያለፈ የስሙን ያህል ሰላም የማስከበር ሚና ሳይጫወት ነው እስከአሁን የዘለቀው። ለዚህም የሰራዊቱ ቁጥር ማነስ እንደ አንድ ሰበብ ምክንያት ይገለጻል። የአፍሪካ መሪዎች የሶማሊያን የሰላም ማስከበር ዘመቻ የመንግስታቱ ድርጅት እንዲረከብ አልያም የሰራዊቱ ቁጥር ወደ ሃያ ሺህ ከፍ እንዲል እንዲያደርግ ሲጎተጉቱ ከርመዋል። ከትላንት በስቲያ የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ታዲያ የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሃይል ቁጥሩ ወደ አስራ ሁለት ሺህ ከፍ እንዲል ነው ወስኗል።የሰላም አስከባሪው ጦር ቆይታ ለተጨማሪ 8 ወራት እንዲራዘምም ምክር ቤቱ ተስማምቷል። ሞቃዲሾ ከከተተው የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሰራዊት ብዙውን ቁጥር የያዘው የኡጋንዳ ጦር ነው። የጦሩ ቃል አቀባይ የትላንት በስቲያው የመንግስታቱ ድርጅት ውሳኔ ለአሸባብ ጥቃት አጸፋ ለመስጠት የሚረዳ ሲሉ ገልጸውታል።

«የመንግስታቱ ድርጅትን ውሳኔ አላነበብኩትም። የአፍሪካ ህብረት ጦር ቆይታ እንዲራዘም ተስማምቶ ከሆነ፤ ከታጣቂዎቹ ለሚሰነዘረው ጥቃት የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ጠንካራ አቅም እናገኛለን። ካልሆነም እስከአሁን እያደረግን እንዳለነው ተግባራችንን እንቀጥላለን።»

Flash-Galerie Somalia Soldaten
የሶማሊያ የሽግግር መንግስት ወታደሮችምስል AP

የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔ በሞቃዲሾ የሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ተጨማሪ 4 ሺህ ወታደሮች እንዲሰማሩ የሚፈቅድ ነው ይህ ተጨማሪው ሃይል ደግሞ ከኡጋንዳ የሚጠበቅ ነው።

«የኡጋንዳን ጦር በተመለከተ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም። በእርግጥ አዲስ ስለሚሰፍረው ጦር አቅምና አጠቃላይ ሁኔታን የተመለከተ ዝርዝር መረጃ ገና የምናገኘው ይሆናል።መነሻ ዕቅዳችን ግን የእኛን ጦር በመሳሪያና በቁሳቁስ አቅሙን ከፍ ማድረግ ነው።»

የምዕራባውያን የደህንነት መረጃዎች ሶማሊያን የእስላማዊ አክራሪ ቡድኖች መፈልፈያ ምድር ይሏታል። በዚህም ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ትኩረት እንዲሰጣት ሲያሳስቡ ሲያስጠነቅቁ ከርመዋል። የመንግስታቱ ድርጅት በሶማሊያ ያለውን ሰላም የማስከበር ዘመቻ ጠቅልሎ ብስሙ እንዲንቀሳቀስ ከማድረግ በአፍሪካ ህብረት በኩል እንዲካሄድ የመረጠ መስሏል። ከአፍሪካ መሪዎች የሚሰማውን ጥሪ አሁንም ሳይቀባለው የህብረቱ ጦር የሚጠናከርበትንና የቆይታ ጊዜው የሚራዘምበትን ውሳኔ አስተላልፏል።ውሳኔው የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ ባን ኪሙን ለአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሰራዊት ትጥቅና ስንቅ የሚቀርብበትን እርምጃ እንዲወስዱ ይጠይቃል። ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብም ለሰራዊቱ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ ያቀርባል። በእርግጥ የአፍሪካ ሀገራት በተለይም ኡጋንዳ በሶማሊያ 20 ሺህ ወታደሮች እንዲሰፍሩ ነው በየጊዜው የሚጎተጉቱት። አሁን ያለው ጦር በሞቃዲሾ አንድ ክፍል ተወስኖ የቀረ በመሆኑ የሰላም ዘመቻው ውጤት እንዳያመጣ አድርጓል ሲሉም ይገልጻሉ። የጸጥታው ምክር ቤት ለአፍሪካ ሀገራት ጉትጎታ ከትላንት በስቲያ መጠነኛ ምላሽ ሰጥቷል። 4 ሺህ ተጨማሪ ጦር እንዲሰማራ። በእርግጥ በአንድ የሞቃዲሾ ክፍል የተወሰነውን የአፍሪካ ህብረት ሰራዊት በተጨማሪ ቦታዎች የሚሰፍርበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል ይላሉ የኡጋንዳ ጦር ቃል አቀባይ

« በአፍሪካ ህብረት የተቀመጠልን ስልጣን ከቡሩንዲ አቻዎቻችን ጋር ሆነን በሞቃዲሾ ከተማ የሰላም ማስከበር ዘመቻ ላይ እንድንሰማራ ነው። ስለዚህ አህን የሚጨመረው ጦር ሲደርስ በሌሎች የሶማሊያ አከባቢዎች የሚሰማራበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል እንጠብቃለን።»

በሶማሊያ ከአሸባብ ጋር ተፋጦ ያለው የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሰራዊት የተውጣጣው ከቡሩንዲና ከኡጋንዳ ብቻ ነው። ደቡብ አፍሪካ ተካሂዶ በነበረው ዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ማግስት በካምፓላ የተፈጸመውን የቦምብ ጥቃት ተከትሎ እዚያው ኡጋንዳ ተደርጎ በተካሄደው የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ላይ ሌሎች ሀገራትም በሶማሊያ ጦራቸው እንዲያዘምቱ ተጠይቆ አንዳንድ ሀገራትም በቃል ደረጃ ተስማምተው እንደነበረ የሚታወስ ነው። እስከአሁን ግን በሞቃዲሾ እየተናነቁ ያሉትን ኡጋንዳንና ቡሩንዲን የተቀላቀለ ሀገር የለም። የኡጋንዳ ጦር ቃል አቀባይ

«ሌሎች ሀገራት ራሳቸውን አደራጅተው የሰራዊቱ ቁጥር እንዲጨምር አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ እንጠብቃለን። የሰላም ማስከበር ዘመቻውን የመንግስታቱ ድርጅት እንደሚረከበው ተስፋ እናደርጋለን። የአፍሪካ ህብረት መሆን የለበትም።»

በሞቃዲሾ የሰፈረው የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሰራዊት በየዓመቱ 130 ሚሊዮን ዶላር ያገኛል። የገንዘብ አቅሙን ለመጨመር የመንግስታቱ ድርጅት ጠንከር ያለ ማሳሰቢያ ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ አስተላልፏል። የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሰራዊት የቆይታው ጊዜም እስከ መጪው መስከረም ወር መጨረሻ እንዲሆን ወስኗል- ከትላንት በስቲያ።

መሳይ መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ