1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

34ተኛው የሰመርጃም የሬጌ ሙዚቃ ድግስ 

እሑድ፣ ሰኔ 30 2011

የሰመርጃም የሬጌ ፌስቲቫል ከዓርብ ዕለት አንስቶ እስከ ዛሬ እሁድ እኩለ ሌሊት ድረስ በቦን አቅራቢያ በምትገኘው የኮሎኝ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል። በየዓመቱ የሚካሄደው ይሔው ድግስ ላይ ከአለም ታዋቂ የሆኑ በተለይም የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኞች እና የሙዚቃው አፍቃሪያን ይሰበሰባሉ።

https://p.dw.com/p/3LhwA
Summerjam 2019 Köln
ምስል DW/L. Abebe

34ተኛው የሰመርጃም የሬጌ ሙዚቃ ድግስ

ፀሀይ እና ነፋሻማ በሆነው አየር የሰመርጃም ታዳሚዎች እንደእየፍላጎታቸው ተበታትነው ድግሱን ይመለከታሉ። በየዓመቱ በጎርጎሮሲያኑ የሐምሌ ወር መጀመሪያ በሚውለው አርብ፣ ቅዳሜ እና እሁድ በኮሎኝ ከተማ የሰመርጃም የሙዚቃ ድግስ ይካሄዳል። ሰመርጃም አውሮጳ ውስጥ ከሚካሄዱ ትላልቅ የሬጌ ፌስቲቫሎች አንዱ ነው። ፉህሊንገር ዜ ወይም ፉህሊንገር ሐይቅ በተባለው እና በውኃ በተከበበው ደሴት ላይ ዘንድሮም ለ 34ተኛ ጊዜ የሰመርጃም የሙዚቃ ድግስ እየተካሄደ ይገኛል። ለሦስት ቀናት በዘለቀው ድግስ 40 የሚጠጉ የሙዚቃ ባንዶች በሁለት ትላልቅ መድረኮች ይጫወታሉ። 25ሺ የሚጠጉ ታዳሚዎችም ይካፈላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ምንም እንኳን ሰመርጃም የሬጌ የሙዚቃ ስልት ላይ የሚያተኩር ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ለሂፕ ሆፕ እና አር ኤንድ ቢ ሙዚቃዎች፣ እንዲሁም ለዘመኑ የጀርመን አርቲስቶች መድረክ የሚሰጥም ሆኗል።ዘንድሮ ከአፍሪቃውያን አቀንቃኝ ተጋባዥ የነበረው ናይጄሪያዊ ዊዝኪድ ነው። ወጣቱ ዘፋኝ ወደ መድረክ ሲወጣ ታዳሚው ጋር መቆሚያ አልነበረም። የ29 ዓመቱ ዊዝኪድ ሁለት የሙዚቃ አልበሞችን ገበያ ላይ አውሏል። በተለይ ዋን ዳንስ የተሰኘው ሙዚቃው ዩናይትድ ስቴትስን እና ብሪታንያ ጨምሮ በ15 ሀገራት በሙዚቃ መዘርዝር ውስጥ 1ኛውን ስፍራ ይዞ ቆይቷል።

ሰመርጃም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲሁ የሙዚቃ ስራዎቹን ለታዳሚያን ያቀረበው ሳሞሪ -አይ ጃማይካዊ ነው። በሬጌ ሙዚቃዎቹ በአንዴ ዝናን ያተረፈ አቀንቃኝም ነው። 
ሳሞሪ -አይ እኢአ በ2015 ዓ.ም የለቀቀው ብላክ ጎልድ የተሰኘው አልበሙ በቢልቦርድ የሬጌ ቻርት የአምስተኛውን ቦታ አስገኝቶታል። በኪንግስተን የድሆች ሰፈር ኬንኮት ያደገው ሳሞሪ -አይ ዝናን ያተረፈው በአንድ የሙዚቃ ድግስ ላይ ጓደኞቹ የተወሰነች መስፈር እንዲዘፍን ከገፋፉት በኋላ ነው። 
የተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት «UNESCO» የሬጌ ሙዚቃን ባለፈው ዓመት ህዳር ቁሳዊ ያልሆነ (immaterial) የባህል ቅርስ አድርጎ መዝግቧል። ምንጩ ጃማይካ የሆነው የሬጌ ሙዚቃ በተለይ ለራስ ተፋሪያን ትልቅ ቦታ አለው። መድረኩ ለበርካታ አርቲስቶች ፍቅርን ፣ እኩልነትን እና አብሮነትን የሚሰብኩ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ እድል ሰጥቷቸዋል።
ለሰመርጃም እንግዳ ያልሆነው ፕሩቶጄ በአሁኑ ሰዓት ጃማይካ ውስጥ አሉ ከሚባሉት አቀንቃኞች አንዱ ነው። እኢአ በ2018 ዓ.ም አራተኛ አልበሙን ለገበያ አቅርቧል። የጃማይካ ባህላዊ ሙዚቃዎቹን ከሂፕ ሆፕ የሙዚቃ ስልት ጋር አጣጥሞ ማቅረቡ በዚህኛው አልበሙም ተሳክቶለታል። ቅዳሜ ምሽት በሰመርጃም መድረክ ላይ ሲወጣ ወገቡ ላይ የሚደርሱትን ድሬድ ፀጉሮቹን እያወዛወዘ ነበር።
ኑራ ከሰመርጃም ጥቂት ሴት አርቲስቶች አንዷ ናት። የኤርትራ የዘር ሐረግ ያላት ጀርመናዊት «ጥቁር ነኝ ጥቁር ነኝ ፣ የጀርመን ፓስፖርት ያለኝ» እያለች ወደ መድረክ ስትወጣ ብዙዎች ፊት ላይ ግራ የመጋባት ስሜት ይነበብ ነበር። የራፕ የሙዚቃ ስልት ላይ የምታተኩረው ኑራ  ግጥሞቿ ለጆሮ የሚከብዱም ነበሩ። በአንፃሩ ታዳሚውን ዘና እና ፈታ እንዲል ያደረገችው ሴት አቀንቃኝ የ 19 ዓመቷ ጃማይካዊት ኮፊ ናት።
ከለንደን የመጣችው ሻንታን ትውልዷ ከጃማይካ ነው። «ሰመርጃም በጣም ድንቅ ነው። ሁሉንም ሰው፣ ባህል እና ሙዚቃን አንድ ያደርጋል።» ከሰመርጃም የምትጠብቀቅ ደግሞ« በትክክል አሁን እያገኘን ያለውን ነው የምጠብቀው። አይሮፕላን ውስጥ ገብተን እስክናርፍ ድረስ ስንጠብቀው የነበረው ይሄንን ነው።»

Summerjam 2019 Köln
ፕሩቶጄምስል DW/L. Abebe

እኔም እዚህ ሰመርጃም ላይ የተገኙ ኢትዮጵያውያንን ወይም ትውልደ ኢትዮጵያውያንን አግኝቼ አነጋግሬያለሁ፤ 
«ይመስገን እባላለሁ። ከስቶኮልም ሲውዲን ነው። የመጣሁት። ቤተሰቦቼ እዚህ ይኖራሉ። እነሱን ለመጠየቅ እና ሰመርጃም ላይ ለመካፈል ብዬ ነው የመጣሁት።» ከይመስገን ጋር ከሲውዲን የመጡት ዘመጆቹ አማን እና ናዎሚም ደስ ብሏቸዋል« ሰመርጃም የተዋጣለት ነው።ቆንጆ አየር ጥሩ ሙዚቃ ሁሉ ነገር ደስ ይላል። እሁድ ሌሊት እስኪዘጉ ድረስ እዚህ እቆያለሁ። » ይላሉ አማን። ናዎሚ ደግሞ «በጣም ደስ ይላል፣ ጥሩ ዘና ያሉ ሰዎች አሉ። ከሲውዲን  በጣም ይለያል። እንደዚህ አይነት ድባብ ለማግኘት ሩቅ መሄድ ያው ግድ ይላል። ሲውዲን ውስጥ ሰዎች ራሳቸውን በሌላ መንገድ ለመግለፅ ይቆጠባሉ። እዚህ ግን ደስ ይላል ሰዎች ግልፅ ናቸው»
የሰመርጃም የሙዚቃ ድግስ ላይ በፈጣን አዘፋፈኑ የሚታወቀው ኤጀንት ሳስሶ እና ብዙም ወደ አውሮፓ መድረኮች መምጣት የማያዘወትረው ሪቺ ስፓይስ ተገኝተዋል። 
በዚህ የሙዚቃ ድግስ ላይ ለመካፈል በርካታ ከብሪታንያ፣ እና ከጀርመን ጎረቤት ሀገራት የመጡ ታዳሚዎች ገጥመውኛል። ከነዚህ አንዱ የሆነው እና ከኦስትሪያ የመጣው ማርቲን የሬጌ ሙዚቃ አፍቃሪ መሆኑ እግሮቹን ሊነካ ትንሽ የቀሩት የድሬድ ፀጉሩ ከሩቅ ያመላክታሉ። ላለፉት 10 ዓመታት ከዚህ አልጠፋሁም ይላል። ሰመርጃም ተቀይሯል የሚሉ አሉ እውነት ነው?
« አዎ በዚህ ዓመት እንደውም ትንሽ ይሻላል። ባለፉት ዓመታት እኔም በተለይ በዚህ »በአረንጓዴው» መድረክ ላይ ሂፕ ሆፕ ብቻ ነበር የሚቀርበው ማለት ይቻላል። እኔ የሬጌ አፍቃሪ ነኝ። በመጠኑ ሂፕ ሆፕ ቢኖር ምንም አይደል ብቻ የሬጌ ድግስ መሆኑን ይዞ ቢቀጥል ጥሩ ነው።»
በዘንድሮው የሰመርጃም የሙዚቃ ድግስ የቦብ ማርሊይ ልጆችም ይሁኑ እንደ አልፋ ብሎንዲ፣ ላኪ ዱበ የመሳሰሉ ዝነኛ የአፍሪቃ አርቲስቶች መድረክ ላይ አልነበሩም። ይሁንና የቅዳሜው የመጨረሻ የመድረክ እንግዳ ቡጁ ባንቶን በጉጉት ሲጠበቅ ከነበሩት አርቲስቶች አንዱ ነው። ቡጁ ባንቶን ገና የ19 ዓመት ወጣት ሳለ በአንድ ዓመት ውስጥ ከዝነኛው ቦብ ማርሊ የበለጠ በርካታ ዘፈኖቹ ቁጥር አንድ ሆነው ተጫውተዋል። የዘንድሮውን የሰመርጃም የሙዚቃ ድግስን ዛሬ ሌሊት የሚያጠናቅቁት ዝነኛው የሬጌ አቀንቃኝ ጂሚ ክሊፍ እና በሌላኛው መድረክ ላይ ደግሞ የጀርመን  257 የተባሉት ባንዶች ይሆናል።

Summerjam 2019 Köln
ከኦስትሪያ የመጣው ማርቲን ምስል DW/L. Abebe
Summerjam 2019 Köln
ምስል DW/L. Abebe

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ