30ኛ ዓመቱን የያዘዉ የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስትያን | ባህል | DW | 27.06.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

30ኛ ዓመቱን የያዘዉ የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስትያን

በጀርመን የመጀመርያዉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን የተቋቋመበትን ሰላሳኛ ዓመት እንሆ አከበረ። የዛሪ ሁለት ሳምንት ግድም በጀርመን በኮሎኝ ከተማ የሚገኘዉ የኢትዮጵያዉያን ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስትያን የተቋቋመበትን ሠላሳኛ ዓመት በደማቅ ሁኔታ አክብሮአል።

በጀርመንና በአካባቢዋ የሚገኙ ካህናት እና እጅግ በርካታ ምዕመናን እንዲሁም በጀርመን የሚገኙ የተለያዩ የአብያተ ክርስትያናት ተወካዮች በተገኙበት፤ ለሁለት ቀናት ተከብሮአል። የክብረ በዓሉ ታዳሚ ሆነን፤ ምዕመናኑ አነጋግረን፤ በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያንን ጉዞዉ በጥቂቱ ልናስቃኝ ቅንብር ይዘናል፤በኮሎኝ የሚገኘዉ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያን ከተቋቋመ፤ እነሆ 30 ኛ ዓመቱን ደፈነ። የኮሎኙ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስትያን በአዉሮጳ ከተቋቋሙት ቤተክርስትያናት ሁሉ፤ የመጀመርያና እና ፋና ወጊም ሆና ቆይቷል። ቤተክርስትያኒቱ መቋቋሟን ተከትሎ «ሐዋርያዊ ጉዞ በምዕራብ አዉሮጳ »

በሚል ርዕስ ለአንባቢዎች እና ጥናት ለሚያደርጉ ግለሰቦች እትም ታዘጋጃለች። በስነ መለኮት ትምህርት የ PHD ዲግሪ ጥናትለመቀጠል በጎርጎሳዊዉ 1979 ዓ,ም ወደ ጀርመን የመጡት የአሁኑ በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ኃላፊ ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀ፤ ያኔ ገና ትምህርታቸዉን እንደጀመሩ ነበር የኢትዮጵያዉያን መሰባሰብያ ቤተ ክርስትያንን ለሟቋቋም ትግል የጀመሩት። በዚህም የፈጣሪ ሃይል ተጨምሮበት ሊሳካ መጫሉን ነዉ የተናገሩት። ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀ፤ በመቀጠል ለቤተክርስትያኒቱ መቋቋም ትልቅ ሥራን እና ትግል ካደረጉት መካከል ባለቤታቸዉ ወ/ሮ ንጋት ከተማ አንዷ መሆናቸዉንም ሳይገልጹ አላለፉም። ከኮሎኙ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያን በኋላ በመካከለኛዉ አዉሮጳ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያናት በሙሉ የተቋቋሙ ከዚች ቤተ ክርስትያን ጋር ተያያዥነት እንዳላቸዉም ገልጸዋል። ከቤተክርስቲያኒቱ ምስረታ ጋር ስማቸዉ የሚነሳዉና በማህበረሰብ ጉዳይ ሠራተኛ የሆኑት የሃንቡርግ ከተማ ነዋሪ አቶ ታደሰ ደሳለኝ፤ ይህ ቤተ ክርስትያን ለመሰራት እቅድ ሲጀመር ጀምሮ አስታዉሳለሁ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከፍተኛ ጥረት ተጨምሮበት እዚህ ደርሶአል። አሁን እንደሚታየዉ መሰባሰብያችን፤ መጠያየቂያችን ቤታችን ሆንዋል።

በጀርመን በኮለኝ ከተማ የዛሩ ሠላሳ ዓመት የኢትዮጵያዉያኑ ቤተ ክርስትያን ከተቋቋመ በኋላ በቀጣይ በሙኒክ፣ በፍራንክፈርት፣ በበርሊን፤ በሽቱትጋርድ፣ በኑረንበርግ፣ በቪስባድን፣ በካስል፤ በሃምቡርግ እና በዳርምሽታት ከተሞች ባጠቃላይ በምድረ ጀርመን 10 አጥብያ ቤተክርስትያናት ተቋቁመዋል። በሰዉ ሀገር ሳለን ቤተክርስትያናችን ሃይማኖታችንን የምንጠብቅባት ብቻ ሳትሆን፤ ስለሀገር ጉዳይ የምንወያይባት፣ ለልጆቻችንም ሆነ ለባእዳን ባህላችንን፣ ቋንቋችንን የምናሳይበት መሰባሰብያችን ነዉ ያሉን በጀርመን ኮሎኝ ከተማ አካባቢ የግላቸዉ የአዛዉንት መጦርያ ድርጅት ያላቸዉ ሲስተር መሠረት አለፈለገ ሰላም እንደሚሉት የዛሪ ሰላሳ አመት የወለዷቸዉ ልጃቸዉ እንኳ ክርስትና የተነሱት እዚህ ነዉ። አሁን እንዲህ ቀሎን ብናይ ግን ይህን ቤተ ክርስትያን ለማቆም የነበረ ትግል እና ስራ በቃላት የሚገለጽ አይደለም ብለዋል። የሰዉ ልጅ ለመኖር እና ለስጋዉ የሚያስፈልገዉ ምግብ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ምግብም ያስፈልገዋልና፤ እዚህ ያለነዉ ኢትዮጵያዉያን በባህላችን እግዝያብሄርን የምናመሰግንበት ቤት በማግኘታችን ትልቅ ደስታ ነዉ ቀላልም አይደለም ብለዋል።

በኢትዮጵያዉያኑ አንድነት እና ባህል፤ በዘማሪያኑ ሽብሸባ እና የጸሎት ስነ-ስርዓት እጅግ የተማረኩትና ከሃያ ዓመታት ጀምሮ ከኢትዮጵያዉያኑ ምዕመናን ጋር አብሬ ነኝ ያሉን ጀርመናዊዉ ቀሲስ ዶክተር ሃንስ ጎዮርግ ሊንክ፤ ኢትዮጵያን ጎብኝተዉ የጥምቀትን በዓል አከባበርን ማየታቸዉን ነግረዉናል፤ የዛሬዉ ክብረ በዓል ደግሞ አሉ ምንም እንኳ ለረጅም ግዜ ከኢትዮጵያዉያን ጋር እንዲህ አይነት በዓላትን አክብሬ ባዉቅም፤ እንደዛሬዉ አስደሳች እና ደማቅ የሆነ በዓል አላየሁም። በመንፈስም ሆነ በሥጋ እጅግ ተደስቻለሁ። በጣም እድለኛም ነኝ የኢትዮጵያዉያንን ባህል አይቼ ፤ በዓሉንም እዚሁ ሀገሬ አብሬ በማክበሬ በጣም እድለኛ ነኝ።» ከቤተክርስትያኒትዋ ጋር አብረዉ የተጓዙ ኢትዮጵያዉያኑ ቤተ ክርስትያን እንዲያገኙ ጥረት ያደረጉ እንዲሁም የኮለኝ ከንቲባ ለሁለት ቀን በተካሄደዉ ክብረ በዓል ላይ ተገኝተዉ፤ ለኢትዮጵያዉያን ያላቸዉን ክብር ገልጸዋል፤ አመስግነዋል። ከተለያዩ የጀርመን ከተሞች እና የአዉሮጳ አገራት የተሰባሰቡት ምዕመናን አገራችን በጥምቀት እንደተለመደዉ ጎዳናዉ ተዘግቶ እያሸበሸቡና እያዜሙ አስፋልቱን ሞልተዉት ሲጓዙ ማየቱ ከ 2000 ዓመት በላይ ታሪክ ያላት እናት ቤተ ክርስትያን ባህል፤ አገር፤ ህዝብ ማስተዋወቁ በባዕድ አገር በነጻነት ሆኖ ማየቱ በስደት ላይ ላለ ሁሉ የደስታ ሲቃ ይተናነቃል። ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀ ከአባትነት ምክራቸዉ ባሻገር በድግሱ ላይ «ዋልድባ ይከበር የህዳሴ ግድብም ይገደብ»

ከዚህ ባሻገር አሉ ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ በንግግራቸዉ ለጀርመኑ ርዕሰ ብሄር ዮአሂም ጋዉክ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት እቄስ ጉዲና ቱምሳ መካነ መቃብር ላይ ብቻ የአበባ ጉንጉን ማስቀመጣቸዉን ነገር በአንድ ላይ ለነበሩት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ፓትሪያርክ ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ግን አለማንሳታቸዉን በሚመለከት ደብዳቤ ልኬ ይቅርታ ጠይቀዉናል ሲሉ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ገልጸዋል። በሃንቡርግ ነዋሪ የሆኑት የቆዳ ሃኪሙ ዶ/ር መክብብ ግዛዉ ክብረ በዓሉላይ ተገኝተዉ ሃገሪ ያለሁ ያህል ተሰማኝ ብለዉናል

ልጃቸዉ ለመጠየቅ ዘወትር ወደ ጀርመን ብቅ የሚሉት በኢትዮጵያ በራሳቸዉ አነሳሽነትና ወጭ የመጀመርያዉን የስነ-ጥበብ ትምህርት ቤት የከፈቱት አቶ አለፈለገ ሰላም ህሩይ ለዚህ በዓል በመብቃታቸዉ ደስ መሰኘታቸዉን ነግረዉናል።

ቡና በመሸጥ ቤተ ክርስትያንዋን በመርዳታቸዉ የሚታወቁት ወ/ሮ ላቀች በበኩላችን ቤተክስያን መግቢያችን መቀበርያችንን በማገልገሌ ደስተኛ ነኝ ብለዉናል። ከፈረንሳይ ፓሪስ የመጡት አባ ወልደተንሳኤ ጫኔም፤ በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አባቶች በጀርመን የሚገኙ የሌሎች የክርስትና ሃይማኖት አባቶች ጋር በጋራ በመስራታቸዉ አዲስ ነገርን ተምሪአለሁ፤ ወደ ምኖርበት ወደፈረንሳይ ስሄድ ይህንኑ ተሞክሪ ይዤ እሄዳለሁ ብለዉናል። የበርሊን ቅዱስ አማኑኤል ቤተክርስትያን አስተዳዳሪ አባ ብርሃነ መስቀል ተድላ ምዕመናኑ የራሳቸዉ ቤተክርስትያን ለመግዛት ጥረት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በጀርመን የመጀመርያዉ የኢትዮጵያ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያን የተቋቋመበትን 30 ዓመት ለማክበር ፤ የከአንድ ሽ በላይ ምዕመናን እንደተገኙ ይገመታል። በስደት ኑሮ በስደት ሀገር እግዚአብሄር አምላክ የብዙዎቹን አባት አብርሃምን እባርከዋለሁ ለበረከት ሁን የሚባርኩህንም እባርካለሁ ብሎ በረከቱ እንደ ሰማይ ኮከብ እንደ ምድር አሸዋ እንዳደለዉ እኛ ኢትዮጵያዉያንንም ከበረከት ወደ በረከት ያሸጋግረን ዘንድ በጸሎት እንለምነዉ ያሉንንን ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀን እናመሰግናለን። ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማድመጫዉን ቁልፍ ተጭነዉ ያድምጡ!

አዜብ ታደሰ

ሸዋዪ ለገሰ

Audios and videos on the topic