284 ኢትዮጵያውያን በጀልባ ከየመን ሊጓዙ ነው | ዓለም | DW | 22.07.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

284 ኢትዮጵያውያን በጀልባ ከየመን ሊጓዙ ነው

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት በርስ በርስ ጦርነት በምትታመሰው የመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን እየመለሰ መሆኑን አስታወቀ። እስካሁን ድረስ 1,429 በዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት 4,442 በኢትዮጵያ መንግስት ስደተኞች መመለሳቸውን ድርጅቱ አስታውቋል። በተጨማሪም በሚቀጥለው ሳምንት 284 ኢትዮጵያውያን በጀልባ ወደ ጅቡቲ ለማጓዝ አቅዷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:45
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:45 ደቂቃ

284 ኢትዮጵያውያን በጀልባ ከየመን ሊጓዙ ነው

« የመን ሰላም ነች።» ከትውልድ ቀያቸው ተነስተው በጅቡቲ ኦቦክ አሊያም በሶማሊያ ቦሳሶና ሞቅዲሹ-የኤደን ባህረ-ሰላጤ

በማቋረጥ የመን ከተሳካላቸው ደግሞ ሳዑዲ አረቢያ ለመግባት ለሚሹ ኢትዮጵያውያን በህገ-ወጥ-የሰዎች አዘዋዋሪዎች የሚነገር ተረት ነው። የየመንን ውጥንቅጥ፤ የሳዑዲ አረቢያንና አጋሮቿን የአየር ጥቃት፤ የእስላማዊ ታጣቂ ቡድኖችን ድርጊት ደብቀው «የመን ሰላም ነች»ይሏቸዋል። ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ያመኗቸውን ከመኖሪያ ቀያቸው አፈናቅለው ከመከራ ይከቷቸዋል። የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ባለሙያ አቶ ቴዎድሮስ ጌታቸው «በጅቡቲ ወደ የመን ለመግባት ሲሞክሩ በባህር ላይ የመስመጥ፤በአጋቾች የመያዝና ከቤተሰቦቻቸው ገንዘብ ለማስላክ ብቻ የሚገረፉበት ሁኔታ አለ። »ሲሉ የስደተኞቹን ፈተና ይናገራሉ። እንደ ባለሙያው ገለጻ በህገ-ወጦች በሚመራው ጉዞ ሴቶች የመደፈር አደጋም ይገጥማቸዋል።

በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን መረጃ መሰረት አሁን በየመን 257,645 ስደተኞችና 8,674 ተገን ጠያቂዎች ይገኛሉ።ከእነዚህ መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት የኢትዮጵያ፤ሶማሊያ እና ኤርትራን የመሳሰሉ የምስራቅ አፍሪቃ አገራት ዜጎች ናቸው።

የመን የተሻለ የስራ እድል እና የኑሮ ሁኔታ ፍለጋ ወደ ሳኡዲ አረቢያ እና ወደ ሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ለመጓዝ የኢትዮጵያውያን ስደተኞች መሸጋገሪያ ነች። በህገ ወጥ የሰዎች አሸጋጋሪዎች አማካኝነት ከጅቡቲ ተነስተው የቀይ ባህርን በጀልባ በማቋረጥ የመን የሚገቡት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ብዙ ጊዜ ሃሳባቸው አይሳካም። አቶ ቴዎድሮስ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ከ3478 በላይ ስደተኞችን ወደ ኢትዮጵያ መመለሱን ይናገራሉ።

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት በየመን ዋና ከተማ ሰንዓ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የስደተኞችን ማንነት የማጣራት ስራ ካከናወነ በኋላ ተመላሾችን ያጉዛል። ድርጅቱ በዋንኛነት በየመን ባለው አለመረጋጋት ምክንያት በነፍስ አድን ስራ ላይ ትኩረት ማድረጉን አቶ ቴዎድሮስ ጌታቸው ተናግረዋል። ስደተኞቹ ወደ ኢትዮጵያ ከተመሰሱ በኋላ የትራንስፖርት እና አስፈላጊ ጉዳዮችን በማሟላት ወደ ትውልድ ቀያቸው እንዲመለሱ ያግዛል።

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅትም ይሁን የኢትዮጵያ መንግስት በየመን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ስደተኞችን የመታደግ ስራ ቢያከናውኑም በተቃራኒው ወደ የመን የሚጓዙ ደግሞ በርካታ ናቸው። ባለፈው ሳምንት የተባበሩት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የርስ በርስ ጦርነት ከተጀመረበት ከወርሃ መጋቢት ጀምሮ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች ወደ የመን መግባታቸውን አስታውቆ ነበር።ከእነዚህ መካከል የኢትዮጵያ፤ሶማሊያ እና ኤርትራ ዜጎች ይገኙበታል። አሁንም ግን በአየርም ይሁን ወደ አገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ስደተኞች አሉ። «ሆዴዳ በሚባለው ስፍራ ላይ በአሁኑ ሰዓት 284 ኢትዮጵያውያን አሉ። በቀጣይ ሳምንት ውስጥ በጀልባ ወደ ጁቡቲ ከጅቡቲ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ይደረጋል።» ሲሉ አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ሒሩት መለሰ

Audios and videos on the topic