276 ዜጎች የተገደሉባት ሶማሊያ የሐዘን ቀን አውጃለች | አፍሪቃ | DW | 16.10.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

276 ዜጎች የተገደሉባት ሶማሊያ የሐዘን ቀን አውጃለች

በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቅዲሹ በደረቅ ጭነት ማጓጓዣ የተጫነ ቦምብ ባለፈው ቅዳሜ ፈንድቶ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 276 ደርሷል። የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ ይችላል የሚል ሥጋት አይሏል። ጥቃቱን የፈጸመው አል-ሸባብ ነው የሚሉ አስተያየቶች ቢደመጡም ተመሳሳይ ድርጊት በመፈጸም የሚታወቀው ታጣቂ ቡድን ግን እስካሁን ትንፍሽ አላለም። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:00
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:00 ደቂቃ

ሞቅዲሹ ሐዘን ላይ ነች

በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቅዲሹ በዕለተ-ቅዳሜ በደረቅ ጭነት ማጓጓዣ ተሽከርካሪ የተጠመደ ቦምብ በማፈንዳት በተፈጸመው ጥቃት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 276 አሻቅቧል። ቁስለኞች በማመላለስ ሥራ ላይ የተጠመደው አሚን አምቡላስ ኃላፊ ዶ/ር አብዱልቃድር አዳም እንዳሉት አብዛኞቹ በአደጋው በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት ባለፉት ሰዓታት ሕይወታቸውን አጥተዋል።  

ሶማሊያ በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎቿ የቀብር ሥነ-ሥርዓት እያካሔደች ሲሆን የሟቾቹ ቁጥር ከዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችል መንግሥት አስታውቋል። ጋዜጠኛ ሐሳን ኢስቲላ እንደሚለው ሞቅዲሹ ዛሬ ሐዘን ተጭኗታል።

"ዛሬ የሞቅዲሹ ከተማ በጥልቅ ሐዘን ውስጥ ትገኛለች። ብዙ ሰዎች በፍንዳታው የቆሰሉት ተጎጂዎች ከተኙባቸው ሆስፒታሎች ደጃፍ ተቀምጠዋል። የሶማሊያ መንግሥት ባለስልጣናት እና የተለያዩ ወገኖች ሆስፒታሎቹን እያገዙ ነው። ደም የሚሰጡም አሉ። 276 ሰዎች የገደለው የቦምብ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ትናንትና ከሰዓት በኋላ የተቆጡ ሰዎች ወደ ሞቅዲሹ አደባባይ ወጥተው ነበር። ጥቃቱ ከተፈጸመበት ቦታ ሰልፍ የወጡት ሰዎች አደጋውን ሲያወግዙ ነበር። የሶማሊያ መንግሥት የከተማዋን ጸጥታ ለማስጠበቅ ብዙ መስራት እንዳለበትም ጠይቀዋል።"  

ኢትዮጵያ፤ ቱርክ እና ኬንያ የሶማሊያ መንግሥት "ብሔራዊ አደጋ" ሲል ለጠራው ጥቃት የሕክምና ባለሙያዎች ለመላክ ፈቃደኝነታቸውን አሳይተዋል። ከ70 በላይ ቁስለኞች ለተጨማሪ ህክምና ወደ ቱርክ ተወስደዋል። የሶማሊያ ሆስፒታሎች እና የሕክምና ተቋማት የከፋ ጉዳት የደረሰባቸውን ለማከም በመታገል ላይ ይገኛሉ። ሶማሌያውያን ደግሞ ሐዘን እና ጸሎት ይዘዋል። 
የሞቅዲሹ ነዋሪዋ ረሒማ አብዲአሊ እንደሚሉት የዕለተ-ቅዳሜውን ያክል የከፋ ጥቃት አይተው አያውቁም።

"ቅዳሜ ዕለት የታዘብንው ጭፍጨፋ ነው። እንዲህ ያለ ነገር ባለፉት 27 ዓመታት አልተመለከትኩም። የአንድ ትንሽ ልጅ ጭንቅላት መሬት ወድቆ አይቻለሁ። በፍንዳታው እናቱ እና ሌሎች ልጆች በፍንዳታው ጭንቅላታቸው ተቆርጦ ከአጠገቡ ወድቀው ነበር። ሰዎች የተበጣጠሱ አካላትን ለየብቻቸው ለመቅበር ተገደዋል። እጅግ አሰቃቂ ሁኔታ ነበር።"

ለጥቃቱ እስካሁን በይፋ ኃላፊነት የወሰደ ወገን ባይኖርም ሶማሊያውያን አደባባይ ወጥተው እጁ አለበት ያሉትን የአል-ሸባብ ታጣቂ ቡድን አውግዘዋል። በሆስፒታሎች ተዘዋውረው ቁስለኞችን የጎበኙት ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሒ ሞሐመድም ቢሆኑ በሶማሊያ ታሪክ የከፋው የተባለውን ጥቃት ያደረሰው መንግሥታቸውን ሊጥል ያደፈጠው አል-ሸባብ ለመሆኑ ጥርጣሬ አልገባቸውም። 

"ይህ አሰቃቂ እና አል-ሸባብ ንጹኃን ዜጎችን ዒላማ ማድረጉን እንደቀጠለ የሚያሳይ ጥቃት ነው። የሶማሊያ ኅብረተሰብ ከሌላ ጊዜ በላይ የቡድኑን ሰይጣናዊ እቅድ ማወቅ አለበት። ዛሬ እንደገና ሰው ከሚበዛበት ቦታ ንጹኃንን አጠቃ"

ከሞቅዲሹ ነዋሪዎች መካከል አሁንም ወዳጅ ዘመዶቻቸው የገቡበት የጠፋቸው፤ፍለጋ የገቡም በርካቶች ናቸው። የሶማሊያ መንግሥት የማፈላለጉን ዘመቻ የሚያግዝ ኮሚቴ ማቋቋሙን አስታውቋል። ከተቀበሩ ሰዎች መካከል 100 ያክሉ ማንነታቸውን ቀርቶ ጾታቸውን እንኳ መለየት አለመቻሉን መንግሥት ጨምሮ አስታውቋል። 

የግብይት ማዕከላት፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ሆቴሎች እና ምግብ ቤቶች በሚበዙበት እና ሁሌም ሞቅ ደመቅ በሚለው የሆዳን አደባባይ የነጎደው የጭነት ተሽከርካሪ ወደ 500 ኪ.ግ. የሚመዝን ተቀጣጣይ ቁስ ሳይጨን እንዳልቀረ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። የጸጥታ መሥሪያ ቤቶቹ በበኩላቸው የጥቃቱን ፈጻሚ ማንነት ፈትሾ ለማግኘት ምርመራ መጀመራቸውን ገልጠዋል። በጄምስ ፋውንዴሽን የምሥራቅ አፍሪቃ ፖለቲካ ተንታኙ እና ጋዜጠኛው ሞሕያዲን ሮብሌ እንደሚለው ግን የጥቃቱ ፈፃሚ አል-ሸባብ ነው የሚለው ድምዳሜ ሚዛን ይደፋል። 

"አል-ሸባብ ይኸን ጥቃት ለመፈጸሙ ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ አልሰጠም። ታጣቂ ቡድኑ ይኸን ያክል ጉዳት ያደረሱም ባይሆኑ ተመሳሳይ ጥቃቶችን ግን ሲፈፅም ቆይቷል። የመንግሥት ባለሥልጣናት ጥቃቱን የፈጸመው አል-ሸባብ ነው እያሉ ነው። ሌላ የሚጠረጠር ወገን ባለመኖሩም ብዙ ሰው ተመሳሳይ ሐሳብ አለው። አል-ሸባብ መንግሥቱን ሲዋጋ፤ በሰላማዊ ሰዎች ላይም እንዲህ መሰል ጥቃቶች ሲፈፅም ቆይቷል። ሁሉም ምልክቶች ከዚህ ጥቃት ጀርባ የአል-ሸባብ እጅ መኖሩን የሚጠቁሙ ናቸው።"

ፎርማጆ በሚለው ቅጽል ሥማቸው የሚታወቁት ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሒ ሞሐመድ የሶስት ቀናት ብሔራዊ ሐዘን አውጀዋል። በሳዑዲ-አረቢያ እና ኳታር መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ ባህር አቋርጦ የተጫናቸው ፕሬዝዳንቱ የሞቅዲሾው ጥቃት መንበረ ስልጣናቸውን የሚነቀንቅ ሌላ ሆና ፈተና ሊሆንባቸው ይችላል።

 
እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic