1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

223 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው ተመለሱ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 18 2008

ህገ ወጥ የተባሉ 223 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ዓርብ ዕለት ከማላዊ እስር ቤት ተለቀው ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን አንድ የስደተኞች ቡድን ገለፀ። ኢትዮጵያውያኑ ማላዊ ውስጥ የታሰሩትም በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ተሻግረው ወደ ሀገሪቱ በመግባታቸው እንደሆነ ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/1HE3i
Logo Internationale Organisation für Migration IOM
ምስል IOM/Alemayehu Seifeselassie

ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች በቁጥጥር ስር የዋሉት በማላዊ በኩል አድርገው ወደ ደቡብ አፍሪቃ ስራ ፍለጋ በጉዞ ላይ ሳሉ ነበር ተብሏል። ሁሉም ስደተኞች ወንዶች ናቸው። እስረኞቹ ምንም እንኳን የተፈረደባቸውን የስድስት ወር እስር እና የገንዘብ ቅጣት ያጠናቀቁ ቢሆንም እነሱን ወደ ሀገራቸው መመለሻ ገንዘብ ስላልተገኘ በጠባብ እስር ቤት ውስጥ ታስረው ቆይተዋል። የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት በምህፃሩ (IOM) የማላዊ ኃላፊ ስቴፈኔ ትሮኸር ለፈረንሳይ ዜና ወኪል እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያውያንን መመለስ የተቻለው ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል በተደረገ ትብብር ነው። አብዛኞቹ ስደተኞች ከአንድ ዓመት በላይ በማውላ ወህኒ ቤት የቆዩ ሲሆን አሁንም ከ 50-70 ኢትዮጵያውያን ማስረጃዎቻቸው እስኪያሟሉ ድረስ ማላዊ ውስጥ እንደሚቆዩ ተገልጿል። ማላዊ በርካታ ቁጥር ያላቸው፤ ኢትዮጵያውያን፣ ሶማሊያውያን እና ሌሎች የአፍሪቃ አገራት ዜጎች ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለመግባት ሀገሪቱን እንደማቋረጫ እንደሚጠቀሙ ገልጻለች።

ልደት አበበ

እሸቴ በቀለ