2017ዓ.ም. ሲቃኝ | ጤና እና አካባቢ | DW | 26.12.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

2017ዓ.ም. ሲቃኝ

ጎርጎሪዮሳዊዉ 2017ዓ,ም በጤናም ሆነ በአካባቢ ተፈጥሮ ረገድ በርካታ ክንዉኖችና ኩነቶችን አስተናግዶነዉ ሊሰናበት አምሥት ቀናት የቀሩት። እንደ ቀደምቱ ዓመታት ሁሉ ዓመቱ አዎንታዊ እና አሉታዊ አጋጣሚዎችን ሲያስተናግድ ሰንብቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:39

በዓመቱ በጤና እና በአካባቢ ተፈጥሮ ረገድ ከነበሩ ኩነቶች ጥቂቱ፤

በ2017 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት መጀመሪያ ቀናት ገደማ ነበር በጤናዉ ረገድ በተለይ ድሀ ሃገራት ዉስጥ ተንሰራፍቶ የኖረዉ ጊኒ ዎርም ጨርሶ ለመጥፋት መቃረቡ የተገረዉ። በቀድሞዉ የአሜሪካን ፕሬዝደንት ጂሚ ካርተር ማዕከል ይፋ የተደረገዉ ይኸዉ ዜና በሽታዉ አሁን በመላዉ ዓለም በ25 ሰዎች ላይ ብቻ መገኘቱን አመልክቷል። የካርተር ማዕከል በዚህ ትል ላይ በተጀመረዉ ዘመቻ መሳተፍ ሲጀምር በጎርጎሪሳዊዉ 1980ዎቹ ዓለም ዉስጥ ማለት ነዉ በ21 ሃገራት ዉስጥ 3,5 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች በዚህ ትል ተጠቅተዉ ነበር። አሁን ጊኒ ትል ይገኝባቸዋል ከተባሉት 25 ሰዎች ሦስቱ ኢትዮጵያ ዉስጥ፣ 16ቱ ቻድ እንዲሁም ቀሪ ስድስቶቹ ደቡብ ሱዳን ዉስጥ ነዉ የሚገኙት።

ጊኒ ዎርምን ለማጥፋት ዘመቻዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሲጀመር ችግሩ የታየዉ በደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች እንደነበር የካርተር ማዕከል ድረ ገጽ መረጃ ይዘረዝራል። ይህን ያረጋገጡት በወቅቱ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ በኢትዮጵያ የካርተር ማዕከል ተጠሪ ዶክተር ዘሪሁን ታደሰ ፤ ስለበሽታዉ ባህሪ ዘርዝረዉ ነበር።

የታማሚዎቹ ቁጥር መቀነሱ እዉነት ቢሆንም ከበሽታዉ ባህሪ በመነሳት ሙሉ ለሙሉ ጠፋ ብሎ መናገር አዳጋች እንደሚሆን አስገንዝበዋል። ከአዎንታዊዉ ዜና በተቃራኒዉ በጦርነት እና በእርስበርስ ግጭት በተንኮታኮተችዉ የመን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በኮሌራ መጠቃታቸዉ የተሰማዉም በዚሁ ዓመት አጋማሽ ነበር። የተመድ ባለፈዉ ሰኔ ወር እኩሌታ ላይ ባወጣዉ መረጃ 200 ሺህ የመናዉያን በኮሌራ መያዛቸዉን ገልጿል። እስከ አሁን ባለዉ ጊዜም በጥቅሉ ኮሌራ የመን ዉስጥ አንድ ሚሊየን ሕዝብን አዳርሷል። ከ2 ሺህ የሚበልጡትንም ገድሏል። ኮሌራ በዚሁ ዓመት ዛምቢያን እና ናይጀሪያንም ሲያጨንቅ የሰነበተ ወረርሽኝ ነበር።

የናይጀሪያ ሰባት ከተሞች በበሽታው የተጠቁ ሲሆን 80 ሰዎች በዚህ ሰበብ መሞታቸዉ ተነግሯል። ሌላዋ በኮሌራ ወረርሽኝ የተጎዳችው አፍሪቃዊት ሀገር ዛምቢያ ናት። የሀገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በዋና ከተማ ሉሳካ ከመስከረም አጋማሽ እስከ ታኅሳስ መጀመሪያዎቹ ቀናት ድረስ በኮሌራ 547 ሰዎች መያዛቸዉን እና 15ቱ ሕይወታቸዉ በዚሁ ምክንያት ማለፉን ይፋ አድርጓል። ሌላዉ አፍሪቃ ዉስጥ ከፍተኛ ሞት የሚያስከትለዉን የወባ በሽታ ለመከላከል የሚደረገዉ ጥረት ዉጤት እያስገኘ መሆኑ ባይካድም ለምርምር የሚፈለገዉ ተገቢዉ የገንዘብ ድጋፍ እየቀነሰ በመምጣቱ አንዲስ ፈተና እንዳይሆን ስጋት መኖሩ የተሰማዉም በዚሁ በተሰናባቹ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2017 የመጨረሻዎቹ ወራት ሲቃረቡ ነዉ።  ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት በ91 ሃገራት 216 ሚሊየን የወባ ታማሚዎች መኖራቸዉን ይፋ ያደረገዉ የዓለም የጤና ድርጅት ከዚያ ቀድሞ በነበረዉ 2015ዓ,ም ቁጥሩ 5 ሚሊየን ብቻ እንደነበር ያስታዉሳል። መሻሻል ሲገባዉ እየጨመረ የሄደዉ የታማሚዎች ቁጥርም በሽታዉን ለመከላከል የሚዉለዉ በጀት ያስከተለዉ ተፅዕኖ መሆኑን በድርጅቱ የወባ ጉዳዮች አስተባባሪ አመልክተዋል። ሌላዉ በዚህ ዓመት የተሰማዉ ጤና ነክ ጉዳይ በካንሰር የሚጠቁ ሰዎች ዉጥር በፍጥነት እየጨመረ የመሄዱ ጉዳይ ነዉ። በኬንያ የሰዎችን ሕይወት ከሚቀጥፉ በሽታዎች ሦስተኛ ደረጃን ይዟል ካንሰር።

ተሰናባቹ 2017ዓ,ም ብክለትን በተመለከተ የደረሱ ጉዳቶች እየተጠቀሱ ብዙ የተነገረበት ዓመት ነበርም ማለት ይቻላል። በየዓመቱ 300 ሚሊየን ቶን ፕላስቲክ ሥራ ላይ እንደሚዉል ያዉቁ ይሆን? ተፈላጊነቱ ከጨመረ መመረቱ መልካም ነዉ ሊባል ይችላል። ጥናቶች የሚያሳዩት ግን ከዚህ ሁሉ ሥራ ላይ ከዋለዉ የፕላስቲክ መጠን 14 በመቶዉ ብቻ ነዉ ዳግም በሌላ መልኩ ተሠርቶ ጥቅም መስጠት የቻለዉ። ከብቶች ሲታረዱ ከሆዳቸዉ የሚገኘዉ የፕላስቲክ ዕቃ መያዣ እየበረከተ መምጣቱ ያሳሰባት ኬንያ በዚህ ዓመት ነዉ ይህን የዕቃ መያዣ ላስቲክ ከሥራ ዉጪ ያደረገችዉ።

ሕንዶችን ደግሞ የአየር ብክለት ሲያጨንቃቸዉ ነዉ የከረመዉ። ዘገባዎች እንዳመለከቱት ከጦርነት እና ጥቃት ይልቅ በተበከለ አየር እና ዉኃ ምክንያት የሚሞተዉ ህዝብ ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ መሄዱን አመልክተዋል። ባለፈዉ ጥቅምት ወር አንድ የኒዉ ዴሊህ ከተማ ነዋሪ ከቤታቸው ወጥተው እንደልባቸዉ መዘዋወር እንዳልቻሉ እንዲህ ነበር የገለጹት፤

«በእርግጠኝነት ኒዉ ዴሊህ በጣም ተበክላለች። ብክለቱ ሕይወቱን አዳጋች አድርጎታል፤ እናም እንደ እኔ ከ50 ዕድሜ በላይ ላሉት አዝናለሁ። ትንፋሽ ሳያጥረን አንዲት ኪሎ ሜትር እንኳ መጓዝ አንችልም። ብዙ ጊዜ እንደውም ሊያፍነን ይደርሳል።»

የአየር ብክለቱ በድሀ ሃገራት ብቻ ሳይሆን በበለፀጉትም ለሰዎች ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት እየሆነ መሄዱ የተነገረዉም በዚሁ ዓመት ነዉ። ለምሳሌ ለንደን ዉስጥ ብቻ በየዓመቱ በዚሁ ሰበብ 9 ሺህ ሰው እንደሚያልቅ የከተማዋ ከንቲባ ይፋ አድርገዋል።

የፕሬዝደንትነት መንበራቸዉን ከተረከቡ ዓመት ያልደፈኑት የዩናይትድ ስቴትስ አወዛጋቢ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በዚሁ በ2017ዓ,ም ሰኔ መቻ ላይ ነበር ሀገራቸዉ ከፈረመችዉ የፓሪሱ የአየር ንብረት ለዉጥ መከላከል ስምምነት መዉጣቷን የሚገልፅ ዉሳኔያቸዉን ለዓለም ይፋ ያደረጉት። ስምምነቱን የፈረሙት ሌሎች ሃገራት በየበኩላቸዉ በቃላቸዉ ከመፅናት በተጨማሪ የታለመዉን ማሳካት የሚያስችሉ ዕቅዶቻቸዉን በየበኩላቸዉ ለማሳወቅ ሲሞክሩ ታይቷል። ይህ በአንድ ወገን የዓለማችን ግንባር ቀደም ከባቢ አየር በካይ አሜሪካ ዉሳኔ ያመጣው የመደናገር ስሜት ሳይበርድ ነው እዚህ ጀርመን ቦን ከተማ ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ የተካሄደዉ። በተቃራኒዉ የትራምፕ አስተዳደር የወሰደዉን አቋም የሚቃወሙ የማኅበረሰብ ወኪሎች በጉባኤዉ ላይ ተገኝነተዉ ድምጻቸዉን ሲያሰሙ ሰንብተዋል። ስብሰባውን በሊቀመንበርነት የመራችው በባህር ከፍታ መጨመር ምክንያት አደጋ የከበባት ፊጂ ደሴት ስትሆን ከመጥፋታችን በፊት ድረሱልን የሚል ጥሪዋን በፕሬዝደንቷ አማካኝነት ለዓለም አቅርባለች።

የተለየ ውጤት እንደማይታይበት ከመነሻዉ የተገመተዉ ይኸዉ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ሲጠናቀቅ ታዲያ የፊጂ ፕሬዝደንት ፍራንክ ባይኒማራማ የፓሪሱ ስምምነት ተግባራዊ የሚሆንበትን መመሪያ የማዘጋጀቱ ተግባር በወጉ ሊከናወን መቻሉን በመግለጽ በመጪው ዓመት ፖላንድ ታላኖአ ላይ ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘዉ ነበር ተሰብሳቢዎቹን በመዝጊያ ንግግራቸዉ የተሰናበቱት። በዚህ ጉባኤ ቦን ከተማ ከ20 ሺህ የሚበልጡ የጉባኤውን ተሳታፊዎች ለሁለት ሳምንታት አስተናግዳለች።

በዚሁ ዓመት የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የበጋ ወራት አጋማሽ ወጀብ የቀላቀለ አዉሎ ነፋስ በተለይ ሰሜን አሜሪካ እና እስያ በሚገኙ ሃገራት ቀላል የማይባል ጉዳት አድርሷል። ሃርቪ የሚል ስያሜ የተሰጠዉ ኃያል ወጀብ ሂዉስተን እና አካባቢዉ ላይ ያደረሰዉጥፋት የ90 ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል። 198,6 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ንብረትም አዉድሟል። ይህም በሀገሪቱ ታሪክ ሃሪኬይን ሃርቪ ከፍተኛ ወጪ ያስከተለ የተፈጥሮ አደጋ እንዲመዘገብ አድርጎታል። ሌላዉ በኃያል ወጀብ እና አዉሎ ነፋስ የተጎዳ  ደግሞ የካሪቢያን ደሴቶች አካባቢ ነዉ። ኢርማ እና ማሪያ የሚል ስያሜ የተሰጣቸዉ ተከታታይ ከባድ ወጀብ የቀላቀሉ አዉሎ ንፋሶች በዶሜኒካን እና ፖርቶ ሪኮ ለሰዎች ሕልፈት ምክንያት ሆነዋል። ኢርማ 134፣ ማሪያ ደግሞ 94 ገድለዋል። በንብረት ላይ ያደረሱት ጉዳትም 166 ቢሊየን ዶላር ተገምቷል። ይኸዉ ኢርማ የተሰኘ ወጀብ የቀላቀለ ኃያል ነፋስ ዩናይትድ ስቴትስን እና የሜክሲኮ ባህረ ገብ አካባቢንም ጠራርጓል።

 

ከተፈጥሮ አደጋዎች መካከል ሜክሲኮን በዚሁ ተሰናባች ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት መስከረም ወር አጋማሽ ላይ የመታዉ የመሬት መንቀጥቀጥ ከ350 የሚበልጡ ሰዎችን ገድሎ፤ 6ሺዎቹን ለጉዳት መዳረጉ ተመዝግቦለታል። በወቅቱ ሜክሲኮ የዛሬ 32 ዓመት የደረሰባትን እና በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን የፈጀዉን የመሬት መንቀጥቀጥ የምታስብበት እንደነበር ነዉ የተነገረዉ። ከዋና ከተማ ሜክሲኮ 125 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘዉን ፒዩቤላ ግዛትን ሕንጻዎች ያፈራረሰዉ በሬክተር ስኬል 7,1 የተመዘገበ የመሬት ነዉጥ ነዉ። ዓመቱ ሊያልቅ ሲቃረብ ባለፈዉ ኅዳር ወር የኢራቅ እና ኢራን ድንበር አካባቢ የመታዉ 7,3 የተመዘገበዉ የመሬት መንቀጥቀጥ ቢያንስ 530 ሰዎችን ገድሎ 70 ሺዎቹን ደግሞ ቤት አልባ አድርጓቸዋል። ድርቅ የሚያጠቃዉ የአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት ደግሞ እንደተለመደዉ በሰደድ እሳት ስትጠበስ ነዉ ዓመቱን ያሳለፈችዉ። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በመላዋ ዩናይትድ ስቴትስ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት በሰደዱ እሳት ጋይቷል።

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic