1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

2010 የማይሆን የሚመስለዉ የሆነበት

ሰኞ፣ ጳጉሜን 5 2010

በኢትዮጵያ የቅርብ ዘመናት ታሪክ ልዩ ሥፍራ የሚሰጣቸዉ ፖለቲካዊ ሁነቶች የተከናወኑበት 2010 በዘመን ሲሻር ፈጣን ፖለቲካዊ ለዉጥን ከአዝጋሚ ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት፤ የሠላም በጎ ተስፋን ከግጭት-ግድያ ሥጋት፤ የስደተኞች መመለስን፤ ከሚሊዮኖች መፈናቀል፤ዕርቅን ከጠብ፤ስክነትን፤ ከግንፍልነት፤ ዕቅድን-ከዘፈቀደ ተቃርኖ ጋር ለሻሪዉ ዘመን አዉርሶ ነዉ

https://p.dw.com/p/34del
Äthiopien Vereidigung Premierminister Abiy Ahmed
ምስል picture-alliance/AA/M. W. Hailu

2010 የማይሆን የሚመስለዉ የሆነበት

ቃል ተገብቶ ቃል የታጠፈበት፤ የሕዝብ ጩኸት የመትረየስ ሔሊኮብተርን ስግምግምታ የዋጠበት፤ ፅናት ሞትን ድል ያደረገበት፤ የማይሆን የሚመስለዉ የሆነበት 2010 ሔደ።ያዉ መቼም የዐመት ዑደት፤ የባሕል ወግ ደግሞ ተስፋ ላጣዉ ሕዝብ ተስፋ ተስፋ ያለ ለማስመሰል የኢትዮጵያ መንግሥት የፕሮፓጋንዳ ማሽን ዘመነ-ከፍታ ብሎት ነበር ዓመቱ ሲጀመር።
ከዓመት በፊት ደብረዘይት ቢሾፍቱ ላይ ለዓመት ግብር ፌስታ ደስታ የታደመዉን ሕዝብ እንደወጣ ያስቀሩት ሔሊኮብተሮች የሆነዉ ያልሆነ ይመስል በ2010 አስር ዋዜማ የአዲስ አበባን ሰማይ በበራሪ ወረቀት አደመቁት።የከፍታ ዘመን ብስራት መሆኑ ነዉ።የሰወስተኛዉ ዓመአት የመጀመሪያ አስርኛ ዓመት።ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያምም ደሳለኝም ፍቅር አንድነትን ሰበኩ።

ስርዓቱ ያደለዉ አዲስ አበባ ዉስጥ ሚሊኒየም በሚባለዉ አዳራሽ፤ ለሚሊኒየሙ አስርኛ ዓመት ፌስታ፤ሲጨፍር፤ሲቦርቅ ከኢንጪኒ እስከ ጨለንቆ፤ከጠገዴ እስከ ኮንሶ የሶስት ዓመት ሐዘን እራሮታቸዉ እንደተቆራመዱ ነበር።

Ethiopian Airlines neuer Linienflug von Addis Abeba nach Asmara
ምስል Fana Broadcasting Corporate

አዲሱ ዓመት ሳምንት ሳይሆነዉ እነ አወዳይ፤ጪናቅሰን፤ጂጂጋ እንደብዙ የኦሮሚያ፤ የአማራ እና ጥቂት የደቡብ አካባቢዎች ሁሉ በግፍ በተገደሉ ሰዎች ደም ራሱ። በገፍ በተፈናቀሉ ሰዎች ዋይታ ታወኩ።«የከፍታ ዘመን» መርገምት
ከሕዳር 2008 ጀምሮ ከኢንጪኒ እስከ ጎንደር፤ ከቢሾፍቱ እስከ ሚኤይሶ ሰዉ በተገደለ ቁጥር ከመንግስት ባለሥልጣናት የምንሰማዉ ዉግዘት፤ የማጣራት፤ ለፍርድ የማቅረብ ቃል እንደገና ተንቆረቆረ።
የፍቅር-አንድነት ዘመን እንደሚሆን የተሰበከለት ዓመት የመጀመሪያ ወር በግድያ ማግስት፤ ተቃዉሞ፤ ግጭት እና ግድያ እንደነገሰበት ተሰናበተ። ጥቅምት የተለየ አልነበረም።«በጥቅምት አንድ አጥንት» የሚለዉ የሩቁ ኢትዮጵያዊ ዴጋ፤ጮራ፤መኮ የሚባሉ የኢሉባቦር አካባቢዎችን በግድያ፤ዝርፊያ መፈናቀል ታሪካቸዉ አወቃቸዉ።

ሕዝብ ገዢዎቹን ይቃወማል፤ የሕዝብን ደሕንነት ፀጥታ ማስከበር የሚገባዉ ፀጥታ አስከባሪ ይገድላል።የመብት ተሟጋቾች፤ የፖለቲካ አንቃኞች፤ ጋዜጠኞች ይጮኻሉ፤ ሟች ቁስለኛ ይቆጥራሉ።የመገደል፤ መፈናቀል፤ መታሰር ስጋት፤ፍርሐት፤ያደረበት ሕዝብ የጭንቀት ቀን አሰናብቶ የጭንቅ ቀን ይቀበላል።ጥቅምትን ሸኘ።ሕዳር።ተከታታዩ ሕዝባዊ ተቃዉሞ፤ግጭት ግድያዉ የተጀመረበት ሰወስተኛ ዓመት።የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ኢሕአዴግ ስራ ሰራፈፃሚ ጉባኤ መቀመጡን አወጀ ።
 

EPRDF Logo

የኢአሐዴግ መግለጫ ለአብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ 26 ዓመት የሰማዉ ግን ባዶ ቃል ነበር።ገዢዉ ፓርቲ  «አርጅታችኋል» ወይም «ደክማችኋል» ብሎ በጡረታ ያሰናበታቸዉን ሽማግሌ ገዢዎች እንደገና ጉባኤ መጥራቱ ግን ለፖለቲካ ተንታኞች የፈገግታ የጥልቅ ትንታኔም መሠረት ነዉ የሆነዉ።
አንጋፋዎቹ መሪዎች ከያሉበት የተጠሩት ለሕዝቡ ጥያቄ ተገቢዉን መልስ መስጠት አለብን በሚሉ እና ህዝብ አንቅሮ የተፋዉ ያገዛዝ ስልት መቀጠል አለበት በሚሉት የገዢዉ ፓርቲ ገዢዎች መካከል የተፈጠረዉን ልዩነት ለመጠበብ እንደነበር ለብዙዉ የፖለቲካ ተንታኝ ምሥጢር አልነበረም። 
«ቲም ለማ» ፤ «ቲም ገዱ» የሚባሉት ቃላት በየመገናኛ ዘዴዉ ደመቅ፤በየተንታኙ አፍ ደገምገም ማለት የጀመሩትም ያኔ ነዉ።አስራ-ሰባት ቀን በዝግ የመከረዉ የኢሕአዴግ ሥራ-አስፈፃሚ እና የቀድሞዉ ታጋዮች ጉባኤ መግለጫም በለዉጥ አራማጆች እና የሕዝብ ጥያቄ በኃይል መደፍለቅ አለብን በሚሉት መካከል ልዩነት መኖሩን በካድሬያዊ ቋንቋ ለመሸፋፋን ቢሞክርም አልተሳካለትም። ታኅሳስ 20።
                
የኢሕአዴግ መሪዎች የመከፋፈላቸዉ ሐቅ ጎላ፤ደመቅ እያለ ይነገር፤ ይዘገብ ገባ።በ2009 ወልዲያ ላይ ብልጭ ብሎ የነበረዉ ግጭት ዉስጥ ዉስጡን ሲንተከተክ ቆይቶ ጥር ላይ የብቅላ ለበቅ ይወርዳል ብሎ ያሰበ ከነበረ እሱ ለብቀላ ያደባ የነበረ ነበር።
ዕለቱ ጥምቀት ነበር።የፀሎት-ምስጋና፤ የደስታ-ጭፈራ፤ የግብዣ መዘነጪያ ዕለት።ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ እንዲባል።የወልዲያ ወጣቶች ግን ጥይት ይዘንብባቸዉ ገባ።ዘንድሮ ጥምቀት ወልዲያ ላይ የተጫረዉ ዕሳት ቆቦ፤ መርሳ እና ሲሪንቃንም በሰዉ ደም በከለ።የዓይን ምስክሩ እንዳሉት የሰዎች እንቅስቃሴም ታገደ።
               
ጊንጪ፤  አርሲ፤ ኮፈሌ ባሌ፤ አምቦ ፤ጉደር ጎንደር፤ ባሕርዳር፤ ቢሾፍቱ፤ ኮንሶ  ዳሮለቡ፤አወዳይ፤ ዴጋ፤ መኮ፤ ከተማ-መንደሮች ስንጠራ፤ ሟች ቁስለኛ ሥንቆጥር፤ የጠፋ ሐብት ንብረት፤የተሰደደ  ሥናሰላ፤ ሕዝባዊ ቁጣዉ ፈናፈኛ ያሳጣቸዉ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሥልጣን በቃኝ አሉ።
                         
ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ስድት ዓመት በሚጠጋ ዘመነ ሥልጣናቸዉ የሰሩት ሥራ ካለ ትልቁን የዚያን ቀን ከወኑት።የካቲት ስምንት።የካቲት በኢትዮጵያ ታሪክ ጉደኛ ወር ነዉ።ጠቅላይ ሚንስትሩ ሥልጣን በለቀቁ ማግስት የሚመሩት መንግሥት ሕዝባዊ ቁጣዉን ለመደፍለቅ የመጨረሻ ለበቁን መዘዘ።አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ።
                                       
የካቲት ማብቂያ የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሬክስ ቲለርሰን አዲስ አበባ ገቡ።ቲለርሰን የኢትዮጵያ አቻቸዉን ወርቅነሕ ገበየሁን ከጎናቸዉ አቁመዉ የኢትዮጵያ መንግስት ለሁለተኛ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉን ተቃወሙት።መልዕክቱ ኢሕአዲግን ለሥልጣን ያበቃችዉ፤ ለኢሕዴግ መንግስት ዙሪያ መለስ ድጋፍ የምትሰጠዉ ልዕለ ኃያል ሐገር ለኢትዮጵያ ገዢዎች ጀርባዋን መስጠትዋን በግልፅ ጠቃቋሚ ነበር።
               
«የኢትዮጵያ መንግስት ሥለየተቀሰቀሰዉ አመፅ እና ስለሚጠፋዉ የሰዉ ሕይወት ሐሳብ የገባዉ መሆኑን እኛም እንጋራለን።ይሁንና እኛ አጥበቀን የምናምነዉ (መፍትሔዉ) ለሕዝቡ የላቀ ነጻነት መስጠት እንጂ መቀነስ አይደለም።»
ተቃዉሞ፤ ግጭት፤ግድያዉ አምቦ፤ሚኤይሶ፤መቱ እያለ ሞያሌ ላይ የአስሮችን ሕይወት ቀጠፈ።በትንሽ ግምት ሐምሳ ሺዎችን አሰደደ።
                          
ግድያ፤አፈሳ፤ እስራት፤ ሰዎችን ማፈናቀል እና ማሰደዱ በተደጋጋመ ቁጥር የገዢዉ ፓርቲ አንድነት እየተፈረቀቀ፤ለዉጥ አራማጅ የሚባሉት ኃይሎች አቅም እየፈረጠመ፤የነበረዉ እንዲቀጥል የሚንገታገቱት ኃይላት በተለይ የሕወሐት መሪዎች ከዉስጥም፤ከዉጪም የሚያገኙት ድጋፍ እየመነመነ መጥቶ መጋቢት ላይ የማይቀረዉ ሆነ።
የኢሕአዲግ ምክር ቤት የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ኦሕዴድ ሊቀመንበር ዐብይ አሕመድ ሐይለማርያም ደሳለኝን እንዲተኩ መረጠ።መጋቢት 24 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዶክተር ዐብይን ጠቅላይ ሚንስትርነት አፀደቀ።
                           
ዘመነ ዐብይ አንድ አለ።የአርባ ሁለት ዓመቱ የቀድሞ ኮሎኔል ቃለ መሐላ ሲፈፅሙ ያደረጉት ንግግር አንድነት፤ ሰላም፤ተስፋ፤ለናፈቀዉ ሕዝብ ማራኪ፤ አስደሳች ተስፋ ሰጪም ነዉ።
ይሁንና ገዢዎቹ ሰላም ለማስፈን ቃል እየገቡ ሠላሙን ሲቀሙት፤ ፍትሕ ዴሞክራሲን ለማስረፅ እየማሉ ሲገድሉ፤ ሲያስሩት የኖረዉ ህዝብ በአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ንግግር እየተመራከም ከጥርጣሬ አልወጣም ነበር።
የ42 ዓመቱ ጎልማሳ ይሕን ያጡት አይመስልም።ሕብረተሰቡን ይወክላሉ የሚባሉ ወገኖችን ተራበተራ አነጋገሩ።በግጭት የታበጡ አካባቢዎችን ጎበኙ።ከሁሉም በላይ ከመመረጣቸዉ በፊት መንግሥት ገርበብ ያደረገዉን የወሕኒ ቤቶች በር ጨርሶ በረገዱት። ከደራሲ አሕመዲን ጀበል እስከ ፖለቲከኛ አንዳርጋቸዉ ፅጌ ያሉ እስረኞች ከየእስር ቤቱ ወደ ዉጪ ይጎርፉ ያዙ።በብዙ ሺሕ ለሚቆጠር ሕዝብ መገደል፤መታሰር፤ መሰቃየት ተጠያቂ የሚባሉትን አንጋፋ ፖለቲከኞች፤ የስለላ መስሪያ ቤት አዛዦች፤የጦር ጄኔራሎች፤ በብዙ ቢቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አባክነዋል የሚባሉት የሜቴክ፤የስኳር ድርጅት እና የሌሎችንም መስሪያ ቤቶችን ኃላፊዎችን እየጠረጉ ጡረታ ዶሏቸው።
የአዲስ አበባ እና የአካባቢዉ ሕዝብ ለአዲሱ ጥቅላይ ሚንስትር ምስጋና ለማቅረብ የትልቂቱን ከተማ ትልቅ አደባባይ አጥለቀለቀዉ።ሰኔ 16።
                             
«መደመር» የምትለዋ የአዲሱ ጠቅላይ ሚንስር አዲስ ቃል ወይም የመርሕ ስያሜ የዘመኑ ፋሽን ሆነች።ሰልፉ የሕይወት ደም አካል ዋጋም አስከፍሏል።ጠቅላይ ሚንስትሩን ለማጥፋት እንደታለመ በሚነገረዉ በሰልፈኛዉ መሐል በተጣለ ቦምብ ሁለት ሰዉ ተገድሏል።አስሮች ቆስለዋል።

Äthiopien Kundgebung Premierminister Abiy Ahmed in Addis Ababa | Explosion
ምስል Getty Images/AFP/Y. Tadese
Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed
ምስል picture-alliance/AA/M.W. Hailu
USA Aßenminister Rex Tillerson
ምስል Reuters/J. Duggan

በዉጪ መርሕ ኬንያ፤ሱዳን፤ ሶማሊያ ጅቡቲ፤ግብፅን፤ ሳዑዲ አረቢያ፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ጎብኝተዉ ኢትዮጵያ ከየሐገራቱ ጋር ያላትን ግንኙነት በአዲስ አቀራረብ ለማጠናከር ጥረዋል።ልዩዉ ግን የአስመራዉ ጉብኝት ነበር።ኃምሌ አንድ 2010።ሁለቱ ሐገራት የ20 ዓመት ጠብ ጦርነታቸዉን በሰላም ዉል ዘጉ።በሳምንቱ አዲስ አበባ።
ክረምቱኑ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተጉዞዉi የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሁለት ሲኖዶሶችን አስታርቀዉ።አዲስ አበባ ላይ የጀመሩትን የተቀናቃኝ ሙስሊም ተቋማት መሪዎችን ማስታረቁን ዋሽግተንም ቀጥለዉ በጠብ የሚፈላለጉ የሙስሊም ተቋማት መሪዎችን አስታርቀዋል። ዋሽግተን፤ሎሳንጀለስ እና ሚኒያ ፖሊስ ላይ በየአካባቢዉ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዉን አሜሪካዉያን ጋር ተወያይተዋል።መደመር የምትል አዲስ ርዕያቸዉን አስተዋዉቀዋል።

ዐዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ዋሽግተን ላይ የኢትዮጵያን አባዜ ሲተርኩ አዲስ አበባ ላይ የሕዳሴ ግድብ ኃላፊ መሐንዲስ ስመኘዉ በቀለ ሞተዉ ተገኙ።ኃምሌ 19።በሰዉ እጅ ተገድለዋል የሚለዉ መላምት አይሎ ነበር።የኋላ ኋላ ግን እራሳቸዉን ማጥፋታቸዉ ፖሊስ አስታወቀ።ጵዋጉሜ 2።
                  
የዐብይ አሕመድ መንግስት በመገናኛ ዘዴዎች፤ እና በተቃዋሚ ፖለቲከኞች ላይ የጣለዉን እገዳ አንስቷል።በዚሕም ምክንያት ለበርካታ አመታት ተሰደዉ የነበሩ ኢትዮጵያዉን ፖለቲከኞች ወደ ሐገር ቤት ተግተልትለው ገብተዋል። መንግሥት ተለያዩ አማፂ ቡድናት ጋር ተደራድሮ ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲመለሱ አድርጓል።
በዚሕ ዓመት አዲስ አበባ ከገቡት የቀድሞዉ አማፂ ቡድን መሪዎች የመጨረሻዎቹ ትናንት የገቡት የአርበኞች ግንቦት ሰባት የአንድነት እና የዴሞክራሲ መሪዎች ናቸዉ።ዶክተር ብርሐኑ ነጋ።
                                   
ፈጣኑ ለዉጥ፤ በጎዉ እርምጃ፤ ጅምሩ ፍትሕ በየአካባቢዉ እንቅፋት አላጣዉም።ዶክተር ዓብይ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን ከያዙም በኋላ መልኩን እየቀያየረ የቀጠለዉ ግጭት  ቤኒ ሻንጉል፤ ሶማሌ፤ ኦሮሚያ፤ ደቡብ ኢትዮጵያ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት አጥፍቷል።በተለይ ሶማሌ ክልል ለጠፋዉ ሕይወት እና ንብረት ተጠያቂ ናቸዉ የተባሉ የክልሉ ርዕሠ መስተዳድር አብዲ መሐመድ ዑመር እና ተባባሪዎቻቸዉ ታስረዋል።ይሁንና አብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ እንደሚያዉቀዉ አብዲና ደካሞቹ ተከታዮቻቸዉ ለግጭት-ግድያዉ  ብቸኛ ተጠያቂ አይደሉም።የሾሙ፤የሸለሙ፤ ገደብ የለሽ ሥልጣን የቸሩ፤ከሁሉም በላይ ሰዉ እንዲገድሉ-እንዲያስገድሉ ያዟቸዉ የቀድሞ እና ያሁን ከፍተኛ ሹማምንታት ዓለመጠየቃቸዉ የአዲስ አበባ ፍትሕ አሁንም በንጡቻ ላይ ነዉ ያለችዉ እያሰኘ ነዉ።እንዳሰኘ-2010 አዲዮስ።

Asmara - Premierminister Abiy Ahmed mit somalischem Präsidenten Formajo und Präsident Isaias
ምስል Prime Minister's Office/F. Arega

 

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ