2009 ዓ.ም እንዴት ይታወሳል? | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 11.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

2009 ዓ.ም እንዴት ይታወሳል?

2009 ዓ.ም በተለያዩ ቦታዎች ተቃውሞዎች የቀጠሉበት፣ በተወሰኑ ቦታዎች ግጭቶች የነበሩበት፣ ብዙዎች ከታቃውሞ ጋር በተያያዘ የታሰሩበት በስተመጨረሻ ደግሞ መንግስት በከፈተው የጸረ-ሙስና ዘመቻ የተወሰኑ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር የዋሉበት ነበር፡፡  

አውዲዮውን ያዳምጡ። 18:19
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
18:19 ደቂቃ

የአመቱ አበይት ጉዳዩች ዳሰሳ

2009 ዓ.ም ከባተ ከሶስት ሳምንት በኋላ የምስጋና በዓል በሆነው ኢሬቻ አደጋ ተከስቶ ነበር፡፡ ከኢሬቻ አደጋ ብዙም ሳይቆይ የኢትዮጵያ መንግስት ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል፡፡ አዋጁ በ26 ዓመት የኢህዴግ የስልጣን ዘመን ከዚያ ቀደም ያልታየ ነበር፡፡ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ መቶ በመቶ ካሸነፈበት ምርጫ በኋላ በ2008 ዓ.ም ካቢኔ መስርቶ ነበር፡፡ አንድ ዓመት ገደማ የቆየውን ካቢኔ መልሶ ያዋቀረው በጥቅምት መጨረሻ ነበር፡፡ 

ባለፈው ዓመት ሌላው ጉልህ ነገር የነበረው የአፈሳ እና እስር ጉዳይ ነበር፡፡ በተቃውሞ ተሳትፋችኋል የተባሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ታስረዋል፡፡ በወታደራዊ ማሰልጠኛ ሳይቀር የታሰሩት እነዚህ እስረኞች የተሃድሶ ስልጠና ተሰጥቷቸው እንደተለቀቁም ተነግሯል፡፡ የተወሰኑት ደግሞ ለህግ እንደሚቀርቡ ተገልጿል፡፡ አመቱ በኢህአዴግ እና ተቃዋሚዎች መካከል  ውይይት ወይም ድርድር የተካሄደበት ነበር፡፡

2009 ዓ.ም አደጋዎችን ያስተናገደም ነበር፡፡ ሚሊዮኖችን ለምግብ ርዳታ ካጋለጣቸው ድርቅ አንስቶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸውን እስከጠፋበት የአዲስ አበባው በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር እስከደረሰው አደጋ ድረስ በዚሁ አመት ተከስቷል፡፡ 

ወደአመቱ ማገባደጃ የተሰቀሰው በገቢ ግብር ትመና የተነሳው ውዝግብ እና እርሱን ተከትሎ የተነሳው ተቃውሞ እና አድማ ሌላው የ2009 ዓ.ም ጉልህ ክስተት ነበር፡፡ በአመቱ መጨረሻ መንግስት የከፈተው የሙስና ዘመቻ ወደ 2010 ዓ.ም የተሻገረ ይመስላል፡፡ ይህ ዘመቻ በመካከለኛ ደረጃ ያሉ በርከት ያሉ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን ለእስር የዳረገ ነው፡፡ የአንዳንዶቹ ጉዳይ በፍርድ ቤት ቤት መታየት የጀመረ ሲሆን የብዙዎቹ ግን ገና በፖሊስ ምርመራ ደረጃ ላይ ነው፡፡ መስፈንጠሪያውን በመጫን ሙሉ ዳሰሳውን ማዳመጥ ይቻላል፡፡

 

ነጋሽ መሐመድ/ ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ

 

Audios and videos on the topic