2009-ከአፍሪቃና ካዉሮጳ ዉጪ ያለዉ ዓለም አበይት ክንዉኖች-I | ዓለም | DW | 21.12.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

2009-ከአፍሪቃና ካዉሮጳ ዉጪ ያለዉ ዓለም አበይት ክንዉኖች-I

አሜሪካ የመጀመሪያዉን ክልስ መሪ መርጣ አዲስ ታሪክ አስመዝግባ-እዉቅ ድምፃዊ ዳንከረኛዋን ቀበረች።አለም ሥለ ሠላም፥ ሥለምጣኔ ሐብት፥ ሥለተፈጥሮ ጥበቃ እየመከረ-እንደተለያየ ሁለት ሺሕ ዘጠኝን-ሊሰናበት-አንድ ሁለት ይል ያዘ።

default

21 12 09


የጎርጎሮሳን የቀን ቀመር-የሚከተለዉ ዓለም 2009ኝን ሸኝቶ-ሁለት ሺሕ አስርን ሊቀበል አስር ቀን ቀረዉ-ዛሬ።ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።ከአስር ቀን በሕዋላ አምና በሚሆነዉ ዘንድሮ በመጀመሪያዉ መንፈቅ ከአፍሪቃና አዉሮጳ ክፍለ-አለማት ዉጪ በሚገኘዉ አለም የተከናወኑ አበይት ክንዉኖችን ባጭሩ እንቃኛለን አብራችሁን ቆዩ።
--------------------------------------------------------------------

የፍልስጤም እስራኤሎች ጦርነት፥ ግጭት፥ ዉዝግብ፥ ሁለቱን ወገኖች ለመሸምገል የሚደረገዉ ሙከራ እንደ ለሥልሳ አንደኛ አመቱ ሁሉ እንደቀጠለ፥ ኢራቅ የቦምብ ጥይት፥ የሽብር-ፀረ-ሽብር ሙቷን እንደቆጠረች፥ አፍቃኒስታን፥ በሚሳዬል፥ ታንክ፥ ቦምብ አረር እንዳረረች-አለም አዲስ አመት ሊል ዕለታት ያሰላ ገባ።

አሜሪካ የመጀመሪያዉን ክልስ መሪ መርጣ አዲስ ታሪክ አስመዝግባ-እዉቅ ድምፃዊ ዳንከረኛዋን ቀበረች።አለም ሥለ ሠላም፥ ሥለምጣኔ ሐብት፥ ሥለተፈጥሮ ጥበቃ እየመከረ-እንደተለያየ ሁለት ሺሕ ዘጠኝን-ሊሰናበት-አንድ ሁለት ይል ያዘ።

ያረጀዉን አመት-አዲስ ሆኖ አንድ ሲል ጥር-ጃፓን፥ ሜክሲኮና ዩጋንዳ በየሁለት አመቱ የሚፈራረቀዉን የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት መቀመጫን ያዙ።

የፍልስጤሟ ግዛት-ጋዛ በጧፍ-ምትክ-የአዉሮፕላን ቦምብ እሳት እንደተንቀለቀለባት፥ በርችት ፋንታ የሚሳዬል እንተምዘገዘገባት-በእልቅት ፍጅት ጢስ-ጠለሷ አድሩስ እንደታጠነች-የተቀበለችዉ ሁለት ሺሕ ዘጠኝ ሰወስተኛ ቀኑን ሲይዝ-የእስራኤል ምድር ጦር ታንክ-መድፍ ይርመሰመስባት ያዘ።
የእስራኤል ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ፓልሞር ያኔ እንዳሉት ጋዛን ያወደመዉ የሐገራቸዉ ጦር ጥቃት-ያለመዉ በሐማስ እንጂ በግዛቲቱ ሕዝብ ላይ አይደለም።

«የምንዋጋዉ ከሐማስ ጋር እንጂ ከጋዛ ሕዝብ ጋር አይደለም።ከፍልስጤም ሕዝብ ጋር አይደለም። ከእሁድ ጀምሮ አስር ሺሕ ቶን ሠብአዊ ሸቀጥ ወደ ጋዛ ተጉዟል።በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ዉስጥ ደግሞ ተጨማሪ ቁሳቁሶች ይላካሉ።»

Lage in Gaza - Flash-Galerie

ጋዛ

የፍልስጤሙ የምክር ቤት እንደራሴ ሙስጠፋ ባርጉዋቲ ግን-የእስራኤልን ጥቃት የጦር ወንጀል ብለዉታል።

«በመላዉ ምዕራባዊ ዳርቻ፥ በመላዉ የፍልስጤም ክፍል የሚኖረዉ መላዉ የፍልስጤም ሕዝብ በጋዛ ላይ የሚፈፀመዉን ወረራ በመቃወም ለመታገል ዛሬ አደባባይ ወጥቷል።(አለማዉ፣) -ባስቸኳይ ተኩስ እንዲቆም ለመጠየቅ፥ ወረራዉ እንዲቆም ለማሳሰብ፥ ከጋዛ ሕዝብ ጎን ሙሉ በሙሉ መቆሙን እና የትግል አጋርነቱን ለመግለጥ-ነዉ።የጋዛ ጦርነት መቆም አለበት።ጋዛ ላይ የተፈፀመዉ ከበባ ባስቸኳይ መነሳት አለበት።ጋዛ ዉስጥ የሚደርሰዉ ሌላ አይደለም-የጦር ወንጀለኝነት እንጂ።በእስራኤል የሚፈፀም የጦር ወንጀለኝነት።»

የሁለት ሺሕ ዘጠኙ ጥር ሃያኛዉን ቀን ሲረግጥ -ከአንድ ሺሕ አራት መቶ በላይ ሰዉ-በአብዛኛዉ ሰላማዊ ሰዎች ያለቁበት ዉጊያ ቆመ።የድፍን አለም-አይን ጆሮ ግን ዋሽንግተን ነበር።የመጀመሪያዉ አፍሪቃ-አሜሪካዊ ፕሬዝዳንት ቃለ መሐላ ፈፀሙ።

«እኔ ባራክ ሁሴይን ኦባማ፣-በፅኑ መንፈስ እምላለሁ፥-የዩናይትድ ስቴትስን ፕሬዝዳት ፅሕፈት ቤት ምግባር በታማኝነት፥ለማከናወን፥የዩናይትድ ስቴትስን ሕገ-መንግሥት ለማስከበር፥ ለመጠበቅና ለመከላከል የምችለዉን ሁሉ ለማድረግ (ቃል እገባለሁ) ለዚሕ ፈጣሪ ይርዳኝ።»
-----------------------------------------------------------------------
«ክቡር ፕሬዝዳት

BdT Obama Inauguration Tanz mit First Lady Michelle Obama

የቃለ ማሐላዉ ምሽት

እንኳን ደስ አለዎት»

ከሁለት ሺሕ ሰባት ጀምሮ አለምን የናጠዉ ምጣኔ ሐብታዊ ድቀት አይስላንድ ላይ ጠንቶ-የሐገሪቱን ጠቅላይ ሚንስትር ጊያር ሐርደን ከሥልጣን አስወገዳቸዉ።ጥርም-አዲዮስ።የካቲት-አንድ።የአይስላንዷ ፖለቲከኛ ጆና ሲጉሮርዶቲ-የሐገሪቱ የጠቅላይ ሚንስትር ሆነዉ ተመረጡ።ሲጉሮርዶቲ ግብረ ሰዶማዊነታቸዉን በይፋ የተናገሩ የመጀመሪያዋ የሐገር መሪ ናቸዉ።

የአለም ትልቂቱ ደሴት-አዉስትሬሊያ በዉብ አራዊት እንስሳት፥ በዱር-ደን ዉሐ የምትታወቅ-የምትደነቀዉን ያክል-ለጎርፍ፥ለቃጠሎም እንግዳ አይደለችም።የዘንድሮዉ የካቲት ቃጠሎ ግን በርግጥ መዝገብ በሚያዉቀዉ ታሪኳ ልዩ ነበር።አንድ መቶ ሰባ-ሰወስት ሰዉ ገደለ።አምስት መቶ አቆሰለ።ሰባት ሺሕ አምስት መቶ-ሰዉ እንበለ ቤት አስቀረ።

ICC-በሚል የእንግሊዘኛ ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የአለም የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት በሥልጣን ላይ ያለ የሐገር መሪ እንዲታሰር ለመጀመሪያ ጊዜ ዋራንት የቆረጠዉም ዘንድሮ ነዉ።ፍርድ ቤቱ የሱዳኑ ፕሬዝዳት ኡመር ሐሰን አል-በሽር በተገኙበት እንዲያዙ ማዘዙ በርግጥ አሁንም ብዙ እንዳወዛገበ ነዉ።ግን-በየነ።መጋቢት-4።ምክንያት፣-የፍርድ ቤቱ ቃል አቀባይ፣-
«ኡመር-አልበሽር ባብዛኛዉ የዳርፉር-ሱዳን ሕዝብ ላይ ሆን ተብሎ ለተፈፀመዉ ጥቃት፥ በተዘዋዋሪ በመተባበር ወይም ጥላቱ እንዲፈፀም በተዘዋዋሪ መንገድ ሆን ብለዉ መመሪያ በመስጠት ወንጀል በተጠያቂነት ተጠርጣሪ ናቸዉ።»

ሱዳን-ዉሳኔዉን «የተፃፈበትን ቀለም ያክል ዋጋ እንኳን የማያወጣ« በማለት አጣጥላዋለች።በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሐገሪቱ አምባሳደር ደግሞ እንዳሉት ደግሞ ዘ-ሔግ ኔዘርላንድስ የሚያስችለዉ አለም አቀፍ ፍርድ ቤት ለሐገራቸዉ የለም።
«ይሕንን ብይን አጥብቀን እንቃወመዋለን።ለኛ አይ ሲ ሲ ሕልዉና የለዉም።ለዉሳኔዉ አንገዛም።በየትኛዉም መንገድ አንተባበርምም።»
-----------------------------------------------------------------------
የብሪታንያዋ ርዕሠ-ከተማ ለንደን ሚያዚያን የተቀበለችዉ በትላልቅ፥ሐብታም ሐገራት መሪዎች፥ በምጣኔ ሐብት አዋቂዎች-ተጨናንቃ፥ በተቃዋሚ ሰልፈኞች-ተጣብባ ነበር።የቡድን ሃያ-አባል ሐገራት የመሪዎች ሁለተኛ ጉባኤ።ሚያዚያ ሁለት።

የሃያዎቹ ሐገራት መሪዎች የአለምን ምጣኔ ሐብት ከዉድቀት ለማንሳት የሚሉ የሚያደርጉት የሚቀይሱት ብልሐት በቅጡ ከመታወቁ በፊት ግን የአለምን የቴሌቪዥን መስኮት የሞላዉ የተቃዉሚዎቹ ሰልፍ-መፈክር-አመፅ ነበር።

አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ እንደ ኮኮብ የደመቁበት፥ ጎርደን ብራዉን ብዙ የባተሉበት፥ንግሥት ኤልሳቤት የጋበዙበት ጉባኤ-የምጣኔ ሐብት ድቀትን ለማስወገድ አግባቢ እና ሁነኛ ርምጃ ወስዷል ነዉ-የጉባኤተኞቹ መልዕክት።የጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ያኔ እንዳሉት ግን ጉባኤዉ አለምን ካለፈዉ ስሕተት ለማስተማር ብዙ ጠቅሟል።

(ሁላችንም ከዚሕ ቀዉስ መማር ያለብን መሆኑ አያጠያይቅም።እኛ ሁላችንም ከምሬ ነዉ-የምለዉ ሁላችንም ይሕን መሠሉ ቀዉስ እንዳይደገም መከላከል አለብን።»

የለንደኑ ጉባኤ ባበቃ በማግስቱ ፈረንሳይና-ጀርመን የድንበር ከተሞች የተደረገዉ የሰሜን አትላንቲ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የመሪዎች ጉባኤ የደፊቱን ዋና ፀሐፊ መረጠ።ይሁንና መሪዎቹ የዴንማርኩን ጠቅላይ ሚንስትር አንድረስ ፎግሕ ራስሙስን ከመምረጣቸዉ በፊት ከድርጅቱ ነባር አባል ቱርክ የተሰነዘረዉን ተቃዉሞ ለማርገብ ብዙ መደራደር፥ መሸማገል፥ ለቱርክ ማካካሻ መፍቀደም ነበረባቸዉ።

የኔቶ ጉባኤተኞች-ዉሳኔ-ስምምነት እንዴትነት አስገምግሞ ሳያበቃ-ሰሜን ኮሪያ ክዋንግ-ምዮግ-ሶንግ ፪ ያለችዉን ሚሳዬል መተኮሷ ተሰማ።እርምጃዉ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤትን ለአስቸኳይ ጉባኤ አስቀምጦ ነበር-በይፋ የወጣ መግለጫ ግን የለም።

በማግስቱ የጣሊያንዋ ከተማ ላ አኩላ በመሬት መንቀጠቀጥ-ተርገፈገች።በሬክተር ስኬል-፮.፫ የተለካዉ የመሬት መንቀጥቀጥ ሰወስት መቶ ሰዉ ገደለ።ከአንድ ሺሕ አምስት መቶ በላይ አቆሰለ።የታይላንድን መንግሥት በመቃወም በተከታታይ የተደረገዉ የአደባባይ ሠልፍ-ንሮ ከሮ ባንኮ ሊደረግ የነበረዉን የምሥራቅ እስያ ሐገራትን ጉባኤ አስ-ሠረዘ።ሚያዚያ-አስራ አንድ።

ግንቦት ለሺሪላንካ ታሪክ እንደየተመልካቹ ብይን-አስደሳች፥ ወይም አሳዛኝ ወር ነዉ።ታሚሎች የሚኖሩበትን ግዛት ከሐገሪቱ ማዕከላዊ መንግሥት አስተዳደር ነፃ ለማዉጣት ለሃያ-አምስት አመት በነፍጥ የሚዋጋዉ የታሚል ነብሮች-አማፂ ቡድን መስራችና መሪ-በመንግሥት ጦር ተገደሉ።ግንቦት አስራ-ስምንት።ለፕሬዝዳት ማሕንደ ራኣፓክስ ታላቅ-ድል ነበር።የታሚሎቹ የነብሮች ነብር-በርግጥ ወደቁ።-ቬሉፒላይ ፕራባሕ-ካራን።አብሮም- የታሚሎች የሃያ-አምስት አመት የነፍጥ ዉጊያ ተደመደመ።

ሙዚቃ (ማይክል)

Michael Jackson Beerdigung Flash-Galerie

«መልካም ዕረፍት-ማይክል»

ይሕ ልሳን፥ ይሕ አምባራቂ፥ ተስረቅራቂ ድምፅ-ተዘጋ።የአለምን የሙዚቃ-የዳንኪራ ሥልት ባዲስ መልክ ያሾረዉ ማይክል ጃክሰን ሞቱ።-ሰኔ-ሃያ አምስት።ከፓሪስ በሰነዓ አድርገዉ ወደ ኮሞሮስ ደሴቶች ይጓዙ የነበሩ አንድ መቶ ሃምሳ ሰወስት መንገደኞች ያሰፈረዉ የየመኒያ አዉሮፕላን ዉቂያኖስ ዉስጥ ገባ።ለወሬ ነጋሪት አንዲት ልጅ ብቻ ተረፈች።-ሰኔ አበቃ።ለቀሪዉ መንፈቅ ሳምንት ጠብቁኝ-ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ፣

ተክሌ የኋላ፣

Audios and videos on the topic