2ኛው የጀርመን እና አፍሪቃ ኤኮኖሚ ጉባዔ በናይሮቢ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 08.02.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

2ኛው የጀርመን እና አፍሪቃ ኤኮኖሚ ጉባዔ በናይሮቢ

የጀርመን ተቋማት በአፍሪቃ ለማሰራት ያሳዩት ፍላጎት እስካሁን ንዑስ ነው። ይህንን ሁኔታ ነገ በናይሮቢ፣ ኬንያ በሚጀመረው 2ኛው የጀርመን እና የአፍሪቃውያን ኤኮኖሚ ጉባዔ ይቀይራል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።  በዚሁ ጉባዔ ላይ ከ400 የሚበልጡ የጀርመን ተቋማት እና ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትም ተሳታፊዎች ናቸው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 06:03

የጀርመን እና የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ትብብር

የጀርመን የኤኮኖሚ ትብብር ሚንስትር ጌርድ ሚውለር እና የኤኮኖሚ ሚንስትር ብሪጊተ ሲፕሪስ፣ እንዲሁም፣ በፌዴራዊ ምክር ቤት የገንዘብ ሚንስቴር ዋና ጸሐፊ  ዛሬ በኬንያ መዲና ናይሮቢ በሚጀመረው የሶስት ቀናት የጀርመን እና የአፍሪቃውያን ኤኮኖሚ ጉባዔ ተሳታፊዎች ይሆናሉ። የኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ በሚያስተናግዱት ሶስት ቀን በሚቆየው ጉባዔ ላይ የዛምቢያ፣ ርዋንዳ፣ ዩጋንዳ እና ሌሎች አፍሪቃውያት ሃገራት ሚንስትሮች ይገኙበታል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለሃገራቸው የቴሌቪዥን ጣቢያ ጀርመን በአፍሪቃ ያለውን የገበያ እድል ሳትጠቀምበት እንደቆየች ያስታወቁት የኤኮኖሚ ትብብሩ ሚንስትር ጌርድ ሚውለር  ጀርመን ከአፍሪቃ ጋር ያላትን ኤኮኖሚ ትብብር ልታጠናክር እንደሚገባ ገልጸዋል፣ ለዚህም፣ ይላሉ ሚንስትሩ፣ ብዙ ምክንያቶች አሉ። ከአፍሪቃ የሚታየው ግዙፉ ስደት አንዱ ምክንያት ነው። የስደተኞቹ ቁጥር እንዲቀንስ ከተፈለገ በአፍሪቃ የኑሮው ሁኔታ መሻሻል እንዳለበት የጀርመን መንግሥት ተረድቶታል። የአፍሪቃን ችግር መፍትሔ ካልተገኘለት ስደተኞች ወደ አውሮጳ መምጣታቸው እንዳማይቀር ሚውለር አስጠንቅቀዋል።

ሌላው በጀርመን የስራ ቦታ ፈጠራን የሚመለከት ነው።  ብዙ ጀርመናውያን ፖለቲከኞች አፍሪቃን ለጀርመናውያን  ባለሀብቶች በወቅቱ  ምቹ ሆና አግኝተዋታል። «ፖሊቲክ ኡንድ ቪስንሻፍት» በሚል መጠሪያ የሚታወቀው በበርሊን የሚገኘው የፖለቲካ ጥናት ተቋም ባልደረባ ኤልቪራ ሽሚግ እንደሚሉት፣ በገበያው ዘርፍ አፍሪቃ የያዘችው ትርጓሜ ከፍ እያለ መጥቷል። አፍሪቃውያን ወደ አገሮቻቸው በንግድ የሚያስገቡትን ምርት ለብዙ ዓመታት ይገዙ የነበሩት ከአውሮጳ ነበር። ይህ ዛሬ ተቀይሮ፣ ሰፊ የገበያ እድል መያዟ ከሚነገርላት አፍሪቃ ጋር የንግዱ ግንኙነት የሚያካሂዱት ቻይና እና ህንድን የመሳሰሉ ሃገራት ናቸው። ለምሳሌ፣ ቻይና ተቋማት በኤኮኖሚ ጉባዔ አስተናጋጅ ሃገር ኬንያ ውስጥ መዲናይቱን ናይሮቢ ከሞምባሳ ወደብ ጋር የሚያገናኝ 14 ቢልዮን ዩሮ የሚፈጀውን የባቡር መስመር እየሰሩ ነው። ውሎ አድሮ ወደ ዩጋንዳ የሚያደርሰውን ዝርጋታ ጀምረዋል።  ምክንያቱም፣ የመንግሥት ተወካዮች ደጋግመው እንደሚናገሩት፣ የአፍሪቃ ጠቅላላ ብሔራዊ ገቢ እጎአ ከ1990 ዓም ወዲህ በአምስት እጥፍ ጨምሯል፣ የተፈጥሮ ሀብቱም እንደበፊቱ ግዙፍ ነው፣ የሕዝቡ ቁጥርም እያደገ ነው።   
ያም ቢሆን ግን ጀርመናውያን ተቋማት በአህጉሩ ያን ያህል ውክልና የላቸውም። በኤኮኖሚ ትብብር ሚንስቴር ዘገባ መሰረት፣  ወደ 1,000 የሚጠጉ ብቻ ናቸው በዚያ የሚሰሩት።

ከነዚህም ሁለት ሶስተኛው ገንዘባቸውን የሚያሰሩት በደቡብ አፍሪቃ ነው። በጀርመን የውጭ ንግድ ውስጥ ከሁለት እስከ ሶስት ከመቶ የሚሆነው የአፍሪቃ ድርሻ የሚጫወተው ሚና እጅግ ንዑስ ነው። የጀርመናውያን ኤኮኖሚ  አፍሪቃ የያዘችው ኤኮኖሚያዊ ትርጓሜ ከፍ ያለ መሆኑን በየጊዜው ከተናገረ በዚሁ ረገድ እስካሁን የተከተለውን አሰራር መቀየር እንደሚኖርበት  የጀርመን አፍሪቃ ጉባዔን ያዘጋጁት በጀርመን ኤኮኖሚ ከሰሃራ በስተደቡብ የሚገኙ አፍሪቃውያት ሃገራትን ጉዳይ ተመልካች ክፍል ሊቀ መንበር ሀይንስ ቫልተር ግሮሰ ገልጸዋል።
« አፍሪቃ ባለፉት 12 ወራት ለውጥ ያሳየ እና በዚህም ሰበብ የጀርመናውያን ተቋማትን ትኩረት እንደሳበ አምናለሁ። እርግጥ፣ ከያንዳንዱ አካባቢ እና ከያንዳንዷ ሃገር ጋር ያለው ደረጃ የተለያየ ነው፣ ግን፣ አጠቃላዩ የንግድ ግንኙነት እየቸመረ ሄዷል። ይህን የልማት መዘርዝሮች ያሳያሉ። እጎአ በ2015 ዓም ለምሳሌ ጀርመን ከአፍሪቃ ጋር ያደረገችው የንግድ ግንኙነት ወደ 26 ቢልዮን ዩሮ ከፍ ብሏል። »

ገሀዱ ይህን ቢመስልም፣ ብዙ የጀርመን ተቋማት ገንዘባቸውን አፍሪቃ ውስጥ ከማሰራት ተቆጥበዋል። ባንዳንድ ሃገራት የሚታየው የፖለቲካ አለመረጋጋት የተቋማቱን ኃላፊዎች ማሳሰቡ አልቀረም። ሙስናም ኢንቬስትመንትን  ያደናቀፈ ሌላው ምክንያት ነው።

 በዚህም የተነሳ የኤኮኖሚ ማህበራት ከመንግሥት ዋስትና ሲጠይቁ ይታያል። የኤኮኖሚ ትብብር ሚንስትር ጌርድ ሚውለርም ይህን ዓይነቱን ዋስትና ለአፍሪቃ ይበጃል በሚል ባዘጋጁት  የማርሻል እቅዳቸው በሀሳብ ደረጃ አቅርበዋል። ይሁንና፣ ይህ ብቻውን በአፍሪቃ የጀርመን ኢንቬስትመንትን ለማሳደግ እንደማይበቃ ኤልቪራ ሽሚግ አስታውቀው፣ለመካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ከዚህ በተጨማሪ የፖለቲካ መረጋጋት እና አፍሪቃውያኑ አጋሮቻቸው የመክፈል ኃላፊነታቸውን በትክክል የሚወጡበት አሰራር ሊዳብር እንደሚገባ አስረድተዋል። 

« በማርሻል እቅዱ ስለግብር ማቃለል ወይም ስለ ብድር ማግኘት ዋስትና ውይይት ቢደረግ ይህ በመጠኑም ቢሆን ሊረዳቸው ይችል ይሆናል። በረጅም ጊዜ ሲታሰብ ግን፣ በአፍሪቃ ለኢንቬስትመንት አመቺ ሁኔታ የሚፈጠርበት ድርጊት ነው ወሳኝ የሚሆነው። እና እኛ የምጣኔ ሀብታችንን ለማነቃቃት ብለን የምናቀርባቸው ዘዴዎች ፣ በዚያ የተወሰነ ውጤት ብቻ ነው ልናስገኝ የምንችለው። »

ዳንየል ፔልስ/አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic