1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

17ኛው የብሄረሰቦች ቀን በብዝኃነት ባህል

ሐሙስ፣ ኅዳር 29 2015

ዛሬ በሀዋሳ ከተማ የተከበረው 17ኛው የብሄሃር ብሄረሰቦች በዓል እንደወትሮው ሁሉ ከፖለቲካዊ ይዘቱ ይልቅ ባህላዊ ትዕይንቱ ጎልቶ የተስተዋለበት ሆኗል፡፡ በሀዋሳ አለምአቀፉ ስታዲየም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ታዳሚዎች በተገኙበት የተከበረው ይኼው በዓል ከአራቱም የአገሪቱ አቅጣጫዎች የመጡ የባህል ተወካዮች ባህላዊ አለባበስና ጭፈራዎችን አቅርበውበታል፡፡

https://p.dw.com/p/4Kgac
Äthiopien Hawassa City | 17. Ethiopian Nationalities Day
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በሐዋሳ ከተማ ተከብሯል

17ኛው የብሄረሰቦች ቀን

ዛሬ በሀዋሳ ከተማ የተከበረው 17ኛው የብሄሃር ብሄረሰቦች በዓል እንደወትሮው ሁሉ ከፖለቲካዊ ይዘቱ ይልቅ ባህላዊ ትዕይንቱ ጎልቶ የተስተዋለበት ሆኗል፡፡ በሀዋሳ አለምአቀፉ ስታዲየም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ታዳሚዎች በተገኙበት የተከበረው ይኼው በዓል ከአራቱም የአገሪቱ አቅጣጫዎች የመጡ የባህል ተወካዮች ባህላዊ አለባበስና ጭፈራዎችን አቅርበውበታል፡፡ በበዓሉ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድም በስታዲየሙ ለተሰበሰበው ታዳሚ ንግግር አሰምተዋል፡፡

Äthiopien Hawassa City | 17. Ethiopian Nationalities Day
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በብሄር ብሄረሰቦች ቀን አከባበር ላይ በሐዋሳ ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

አብይ በዚሁ ንግግራቸው ከሰሞኑ በምዕራብ ኦሮሚያ እየተባበሰ ሥለመጣው ሞትና መፈናቀል በገደምዳሜም ቢሆን በንግግራቸው አንስተዋል፡፡ በራሳቸው ሳይሆን በሌሎች አጀንዳ የተገዙ ያሏቸው ሀይሎች በንፁሃን ደም ፖለቲካ እየሠሩ ይገኛሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን አይደለም ሊያፈርሱ ሊነቀንቁ አይችሉም ›› ብለዋል፡፡ አሁን ባለው ሀኔታ ለኢትዮጵያ ደንግዝግዝና ጭለማ ቢመስልም የአዲስ ድል ባለቤት መሆናችን አይቀርም ሲሉም ለታዳሚው ተናግረዋል፡፡

የበዓሉ ተሳታፊዎች ሥሜት

በሀዋሳ  የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ላይ የተለያዩ የባህል ቡድኖች ባህላዊ ትርኢቶቻቸውን አቅርበዋል፡፡ ወይዘሮ ዳሳሽ ቢፍቱ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ከመጡት የበዓል ቡድን አባላት መካከል አንዷ ናቸው፡፡ በበዓሉ ላይ ሲገኙ የዛሬው ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ ዳሳሽ ‹‹ ሁሉንም የብሄር ብሄረሰቦች የሚወክል የባህል ቡድኖች እዚህ ተገኝተው የባህል ልውውጥ ማድረጋቸው መልካም ነገር ነው ፡፡ ይህም በሕዝቦች መካከል የጠለቀ ትውውቅና መግባባትን ይፈጥራል ›› ብለዋል፡፡

Äthiopien Hawassa City | 17. Ethiopian Nationalities Day
የብሄር ብሄረሰቦች ቀን አከባበር በሐዋሳ ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW
Äthiopien Hawassa City | 17. Ethiopian Nationalities Day
ወይዘሮ ዳሳሽ ቢፍቱ በብሔር ብሔረሰቦች ቀን አከባበር ላይ ፤ ሐዋሳምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ከጎፋ ዞን የመጣው አቶ ድንበሩ ደርቤ ከወይዘሮ ሳላይሽ ጋር ተመሳሳይ ሀሳብ እንዳላው ይናገራል፡፡ ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰብ አገር ናት የሚለው ድንበሩ ‹‹ ሁሉም ባህል ወጉን ማስተዋወቅና ሌሎች እንዲያደንቁለት ይፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓልን የመሰለ ምቹ አጋጣሚ አይገኝም ›› ብሏል፡፡

ፖለቲካና ባህል

በየዓመቱ ህዳር 29 ቀን የሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው  የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሪፖብሊክ ህገ መንግሥት የጸደቀበት ቀንን ምክንያት በማድረግ እንደሆነ ይታወቃል ፡፡ ይሁንእንጂ በዓሉ ከፖለቲካዊ ዳራው ይልቅ ባህላዊ እድምታው ጎልቶ እንደሚታይ ከበዓል ዝግጅቱ መረዳት ይቻላል፡፡ አቶ ዳያሞ ዳሌ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካና የዓለምአቀፍ ህዝብ ግንኙነት ሙሩቅ ሲሆኑ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆንም አገልግለዋል፡፡ አቶ ዳያሞ በየዓመቱ የሚከበረው ህዳር 29 ባህላዊም ፖለቲካዊም አውድ የተላበሰ ነው ይላሉ ፡፡ በኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 8 በኢትዮጵያ ሉዐላዊ የፖለቲካ ሥልጣን  ባለቤቶች ብሄር ብሄረሰቦች ናቸው በማለት እንደሚደነግግ የሚጠቅሱት አቶ ዳያሞ ‹‹ ፖለቲካዊው የአገሪቱን ህብረ ብሄራዊነትንና ብዝሃነትን ለማሳየት የተቀረጸ ነው ፡፡ በዚሁ አንቀጽ ላይ ፖለቲካዊ ዓላማ በሚል ያስቀመጠው በህዝቦች መካከል አኩልነትና  ወንድማማችነትን እንዲሰፈን ማድረግ በሚል ተጠቅሶ ይገኛል ፡፡ ይህም በባህላዊ ትዕይንቶች ጭምር የሚገለጽ ነው ፡፡ በዓሉም ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ የብሄረሰብ ውክልና ባለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስፈጻሚነት እየተካሄደ ይገኛል ›› ብለዋል ፡፡

Äthiopien Hawassa City | 17. Ethiopian Nationalities Day
የብሄር ብሄረሰቦች ቀን አከባበር በሐዋሳ ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የህዳር 29 የብሄር ብሄረሰቦች በዓልን በመልካም ገጽታው የሚመለከቱት ያሉትን ያህል የዘውግ ፖለቲካ ቅጥያ አድርገው የሚመለከቱትም ብዙዎች ናቸው ፡፡ አቶ ዳያሞ ግን በዚህ ሀሳብ አይስማሙም ፡፡ በዓሉ ብሄር ብሄረሰቦች የአላባበስና የአጨፋፈር ቱባ ባህላቸውን ለማስተዋወቅ ዕድል እንደሚፈጥር የሚናገሩት አቶ ዳያሞ ‹‹ ትዕይንቱ በህዝቦች መካከል ባህላዊ መገባባትን / Caltural understanding  / ለመፍጠር ያስችላል ፡፡ በተለይ በሙዚቃና በዳንስ ዘርፍ ወደ ኪነ ጥበባዊ የእንዱስትሪ ገበያ ለመግባት መነሻ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል ፡፡ በርካታ ባህላዊ ድምጻዊያን እና ዳንኪረኞች ከዚህ በመንደርደር የሙያውን ዘርፍ እንዲቀላቀሉ አስችሏቸዋል ›› ብለዋል፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

አዜብ ታደሰ