1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

16ኛው የብሪክስ ጉባኤ በሩሲያ - ካዛን

ገበያው ንጉሤ
ሐሙስ፣ ጥቅምት 14 2017

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የግብጽ ፕሬዝደንት አብዱል ፋታኅ አል ሲሲን ጨምሮ የ9 ሀገራት መሪዎች የተሳተፉበት የብሪክስ ጉባኤ መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል። በመግለጫው "ማዕቀብን ጨምሮ በተናጠል የሚወሰዱ ሕጋዊ ያልሆኑ አስገዳጅ እርምጃዎች" እንደሚያሰጓቸው ገልጸዋል። በብሪክስ መካከል የፋይናንስ ትብብር ለማሳደግ ቁርጠኝነታቸውን አሳውቀዋል

https://p.dw.com/p/4mC8V
የሩሲያ እና የቻይና ፕሬዝደንቶች በብሪክስ ጉባኤ
ሩሲያ በካዛን የብሪክስን የመሪዎች ጉባኤ ያስተናገደችው ከዩክሬን ወረራ ምክንያት ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ከዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት በተቆረጠባቸው የእስር ማዘዣ ምክንያት የውጭ ጉዟቸው በተገታበት ወቅት ነው። ምስል Sergey Bobylev/Brics-Russ/Planet Pix/ZUMA/dpa/picture alliance

16ኛው የብሪክስ ጉባኤ በሩሲያ - ካዛን

16ኛው የብሪክስ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ጉባኤ ካለፈው ማክሰኞ ጀመሮ በሩሲያ ካዛን ከተማ  ሲካሄድ ቆይቶ ዛሬ የጋራ መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል። በጎርጎሮሳዊው 2009 የበለጸጉ የምዕራብ አገሮች የኢኮኖሚን ጫና እና አሰራር ለመቋቋም ታስቦ የተመሰረተው ብሪክስ፤ ስሙን የወሰደው ከመጀመሪያዎቹ መስራች አገሮች ብራዚል፣ ሩስያ፣ ህንድ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ የእንግሊዝኛ ስሞቻቸው (BRICS) የመጀመሪያ አልፋቤቶችን በመውሰድ ነው።

የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት አንድምታ

ቡድኑ ባለፈው ጥር ወር በጆሀንስበርግ ባካሄደው 15ኛው ጉባኤው፤ ግብጽን፤ ሳኡዲ አረቢያን፤ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችን፤ ኢራን እና ኢትዮጵያን በአባልነት የጨመረ ሲሆን፤ ሌሎች የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል የሆነቸውን ቱርክን ጨምሮ 30 አገሮች አባል ለመሆን እንደጠይቁ ወይም ፍላጎት እንዳሳዩ ተገልጿል።

የጉባኤው ዋና አጀንዳ እና የጋራ መግለጫ

“በዓለም ቀፍ ንግድ እና የክፍያ ስርዓት ከዶላር ጥገኝነት መላቀቅ የሚያስችል አሰራርን መዘርጋት በሚቻልበት ሁኔታ መምከር” ዋናው የ16ኛው ጉባኤው አጀንዳ የነበር ሲሆን፤ በቡድኑ አባል አገራት መካከል ሊኖሩ ስለሚገባቸው የኢኮኖሚ ትብብሮችና አለማቀፍ ጉዳዮችም በጉባኤው ውይይት የተደረገ መሆኑ ታውቋል። 

የሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በካዛን በተካሔደው የብሪክስ ጉባኤ
የሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በካዛን የተካሔደው ጉባኤ የብሪክስ አባል ሀገራትን የፋይናንስ ትብብር በማጠናከር ላይ እንደተወያየ ተናግረዋል። ምስል Valery Sharifulin/Sputnik/AP Photo/picture alliance

ኢትዮጵያ በይፋ ብሪክስን ስትቀላቀል ባለሙያዎች ስለ ፋይዳው ጥርጣሬ ገብቷቸዋል

ከጉባኤው ጎን ለጎን በርካታ የሁለትዮሽ ውይይቶች እንደተካሄዱና ስምምነቶችም እንደተፈረሙም  ተገልጿል። የጉባኤው ተሳታፊዎች በመጨርሻም “የካዛን መግለጫ” የተሰኘ የጋራ ሰነድ አውተዋል። በመግለጫው፤ የመንግስታቱ ድርጅትና የዓለማቀፍ የፋይናንስ ተቋማት አሰራርን መሻሻል አስፈላጊነትና፤ የብሪክስ አገራት  የጋራ የእህል ግብይት ስርዓት መቋቋምን የመሳሰሉ በርካታ የቡድኑና አለማቀፍ ጉዳዮች የተገለጹ ሲሆን፤ የዩክሬንና የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነትቶችም በመንግስታቱ ድርጅት ቻርተር መሰረት መቆም ያለባቸው ስለመሆኑ ተጠቅሷል።

ጉባኤው ለሩሲያና ፕሬዝዳንት ፑቲን ያስገኘው ጠቀሜታ

 ሩሲያ በጎርጎሮሳዊው 2022 በዩክሬን ላይ ጦርነት ከከፈተች ወዲህ በርካታ የኢኮኖሚ ማዕቀቦች የተጣሉባትና ፕሬዝዳንት ፑቲንም ከአለማቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት በተቆረጠባቸው የዕስር ማዘዣ ምክኒያት የውጭ ጉዟቸው ተገቶ በቆየበት ወቅት ይህን የመሰለ አለማቀፍ ጉባኤ በሩሲያ መካሄዱ ፑቲን የተገለሉት ከጥቂት የምራባውያን መንግስታት እንጂ ከአለም አለመሆኑን የሚያሳይ ሁኗል እየተባለ ነው።  የዶቼ ቬለ የሩያ ተንታኝ ኮንስታንቲን ኤገርት ያረጋገጠውም ይህንኑ ነው፤ “ሩሲያ ቢዲፕሎማሲው  መገልል ቢድረስርባትም፤ ጉባኤው ግን እውነታው ይህ እንዳልሆነ ለማሳየት የረዳ ሁኗል”  በማለት መልዕክቱም ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ ብቻ ሳይሆን ላገር ውስጥም መሆኑን ገልጿል።

የሕንድ እና የቻይና መሪዎች
በካዛን የተካሔደው ጉባኤ የብሪክስ መሥራቾች የሆኑት የሕንድ እና የቻይና መሪዎች ጭምር የተገኙበት ነበርምስል China Daily/REUTERS

የብሪክስ ዋና አጀንዳ መሳካት ላይ የተጋረጡ ተግዳሮቶች

በሌላ በኩል ግን ጉባኤው ባጠቃላይ፤ ብሪክስ በኢኮኖሚው አንጻር ሊያመጣ የሚችለውን ለውጥ በተለይም ሩሲያን ከማዕቀብ ጫና ሊያላቅቅ ይችል ይሆናል ተብሎ በታሰበው ከዶላር ጥገኘት የመላቀቅ አጀንዳ ላይ  ብዙም ተጨብጭ ውጤት እንዳላሳየ ነው የሚነገረው። ለዚህም በዋናነት የሚጠቀሰው በቡድኑ አባል አገራት መካከል ያለው ልዩነት ነው።

ኢትዮጵያ ብሪክስን ብትቀላቀል ምን ጥቅም ታገኛለች?

የዶቼ ቬለ የሩሲያ ተንታኝ ኮንስታንቲን እንደሚለው ቡድኑ የተለያዩ አንዳንዴም የሚቃረኑ ፍላጎቶች ያሏቸው አገሮች ስብስብ ነው። “ከሀያ አመታት በፊት ቡድኑ ሲመሰረት በዓለማቀፉ የኢኮኖሚ ስራት ላይ የራሱን የሆነ የኢኮኖሚ ሚና እንዲኖረው ታስቦ ቢሆንም፤ ባሁኑ ወቅት ግን ቢያንስ በኢራን፣ ቻይና እና ሩሲያ ቡድኑ ጸረ ምራባውያን ሀይል ሆኖ የተወሰደ ሲሆን፤ ሌሎች አባሎች ለምሳሌ ህንድ ግን ፍላጎቷ በዓለማቀፉ ኢኮኖሚ ላይ  ጫና ለማሳደር እንጂ ከአሜሪካ  ወይም ከምዕራባውያኑ ጋር ተጻሮ ለመቆም አይደለም” በማለት በቡድኑ ውስጥ ያለውን ልዩነት ግልጽ አድርጓል።

በተጨማሪም በቡድኑ አባል አገራት መካከል ለምሳሌ በህንድና ቻይና፤ በሳኡዲ አረቢያና ኢራን፤ በግብጽና ኢትዮጵያ መካከል ያሉ  አለመግባባቶች እና ግጭቶችም የቡድኑን አንድነት እና ስኬት ሊገዳደሩ እንደሚችሉ ነው ታዛቢዎች የሚናገሩት።

አውሮፓ እና አሜሪካ ጉባኤውን በንቃት ሲከታትሉት ነው የቆዩት። የአውሮፓ ህብረት የጉባኤው ተሳታፊዎች ፕሬዝዳንት ፑቲን ጦርነቱን እንዲያቆሙ ይነግሯቸው ዘንድ ፍላጎቱ መሆኑን የህብረቱ የውጭ ግንኙነት  ቃል አቀባይ ፒተር ስታኖ  አስታውቋል። የዋና ጸህፊ ጉቴረዥ በስብሰባው መገኘት ያስከፋቸው የህብረቱ አገሮች መኖራቸውም ተገልጿል። ቱርክ የብሪክስ አባል ለመሆን መጠየቋና ፕሬዝዳንት ኢርዶጋንም በጉባኤው መሳተፋቸውም የህብረቱና የኔቶ አባል አገራትን ያስገረመና ያነጋገርም ሆኗል።  

ገበያው ንጉሴ

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ