1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

125ኛው የአድዋ ድል አከባበርና የኦፌኮ ከምርጫ ራስን ማግለል

ዓርብ፣ የካቲት 26 2013

የ125ኛው የዓድዋ ድል በዓል አከባበር እንዲሁም የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ፓርቲ በመጭው ሀገራዊ ምርጫ እንደማይሳተፍ ማስታወቁ።በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ዘንድ ብዙ አነጋግሯል።

https://p.dw.com/p/3qGBd
Symbolbild I BigTech I Social Media
ምስል Ozan Kose/AFP/Getty Images

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

በየዓመቱ የካቲት 23 ቀን የሚከበረው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዘንድሮም በሳምንቱ መጀመሪያ ለ125ኛ ጊዜ ተከብሯል።በዓሉ በተለያዩ አካባቢዎች በጎዳና ላይ ትርኢቶች ደምቆ የተከበረ ቢሆንም፤ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የበዓሉን ኢትዮጵያዊነት የዘከሩ የመኖራቸውን ያህል፤ በዘመቻው የተሳተፉ አርበኞችን በዬጎራው ከፍለው የተከራከሩም አልጠፉም። በሌላ በኩል የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል  በአዲስ አበባ ከተማ በሚኒሊክና በመስቀል አደባባይ ሁለት ቦታ መከበሩ እንዲሁም፤በመሰቀል አደባባዩ አከባበር ላይ የጠቅላይ ሚንስትር  ዓብይ አህመድ  ፎቶ ከአርበኛ ባልቻ አባነብሶ ፎቶ ጋር ተሰቅሎ መታየቱም የበዓሉን መከበር ተከትሎ  ሌላው ያነጋገረ ጉዳይ ነበር።
ደምስ እሸቴ የተባሉ አስተያየት ሰጪ «እኔ ለኦሮሞ ጀግኖች ትልቅ ክብር አለኝ።ለምሳሌ ለነጃጋማ ኬሎ ለነባልቻ አባነብሶ ለነ ሀብተገወርጊስ ዲነግዴ አባመላ ወዘተ ። ነገርግን የጠቅላይ  ሚንስትሩ ፎቶ  በአደዋ ድል አከባበር ሥነ-ሥርዓት ላይ ለምን እንደሰቀለ አልገባኝም ።»ሲሉ፤ፀባዬ ሰናይ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ«የማንም ፎቶ ተሰቀለ ድሉን ማንም ያምጣው የአድዋ ድል ለሀገራችን ብሎም ለአፍሪቃ ኩራት ነው።የአሁኑ ትውልድም ከመናቆር ወጥቶ የራሱን የቤት ስራ ይስራ።»ብለዋል። ጎዶሊያስ ጎዶሊያስ በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ«አድዋ አንድነትን ነው ያስተማረን አዲስ አበባ ላይ ለምን ለየብቻ ሁለት ቦታ ማክበር እንደተፈለገ አልገባኝም።»ብለዋል
ሲሳይ ነኝ በሚል ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ«የአድዋ ድልን ተቀብሎ  መሪዎቹን ሚኒሊክንና ጣይቱን ማሳነስ ሰርጉን ወዶ ሙሽራውን የመጥላት ያህል ነው።የሚሻለው የታሪክን ለታሪክ ትቶ በሚያስማማን ነገር እየተስማማን ብንሄድ መልካም ነበር።የተያዘው የፅንፍ መንገድ የትም አያደርስም።»ይላል።
ሀና ፍቅር የተባሉ አስተያየት ሰጪ«እኔ ከመሪው ይልቅ ለሀገሩ ህይወቱን ለሰጠው ተራ ህዝብና ተራ ወታደር ክብር አለኝ።»ሲሉ፤
ወርቁ ሽፈራው በበኩላቸው«አንድ ነገር ታወሰኝ ። አርጀንቲና የዓለምን ዋንጫ ስታሸንፍ ኮከብ ተጫዋቹ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ነበር ። ያኔ " አርጀንቲና ማራዶና ፤ ማራዶና አርጀንቲና ።" ተብሎ በዓለም ተወድሷል ። እንዲህ ነው ብሐራዊ ጀግና የሚፈጠረው ። እኛ ግን ተረግመናል መሰለኝ።ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ነጻነት የተረፈውን ታሪክ የአድዋ ድልን ሰናከብር የመሪ ተዋናያኑን ፎቶ ሳንይዝ ፣ ሰሙንም ሳናወሳ መሆኑ በእርግጥም ተረግመናል ። እግዚአብሔር እርግማናችንን ይሰርዝልን ።»የሚል አስተያየት አስፍረዋል።
ፋክት ቡክ በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ«በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ይህ ጀግና የጉራጌ ነው፣ይህኛው  የኦሮሞ ነው ያኛው ደግሞ የትግራይ ነው የአማራ ነው። እያለ በታሪክና ለሀገራቸው በሞቱ ጀግኖች የሚጣላ ትውልድ ከማየት የበለጠ ምን የሚያሳፍር ነገር አለ።»ይላል።
ትግስት ሀይሉ በበኩላቸው «አድዋንስ በእንግሊዘኛ የፃፉት ለምንድነው ?እኛ  የራሳችን ፊደል አለን አይደለም።»ሲሉ ተችተዋል።
«ባሻይ አዋሎም፣አሉላ አባነጋ፣ባልቻ አባነብሶ፣ሀብተጊርጊስ ዲነግዴ በሚኒሊክና በጣይቱ የተመሩ  ቆጥሬ የማልጨርሳቸው ከመላው ኢትዮጵያ የተመሙ የአድዋ ጀግኖች እነዚህ ሁሉ የሞቱት ለሀገር ነው።በየ ጎጡ የምትከቷቸው ሰዎች አታሳንሷቸው።እነዚህ ጀግኖች አሁን ያለውን ትውልድ ቢያዩ የሚያፍሩ ይመስለኛል።»ያሉት ደግሞ ናቲ ደረጄ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው። 
አሌክስ ጋዙ በበኩላቸው፤«በአድዋ ጦርነት ግን ጣሊያን እንጂ ዘረኝነት አልተሸነፈም።ለምን ይዋሻል።»ብለዋል።
መሀመድ አወል ደግሞ«አፄ ሚኒሊክ የሰሩት ጥሩ ስራ እንዳለ ሆኖ፤ መጥፎ ስራቸዉም መፃፍ መቻል አለበት። እንደ መላዕክት  ምንም መጥፎ ነገር አልሰሩም ብሎ የሚከራከር የታሪክ ፀሀፊ የሞላባት ሀገር፤ ትዉልዱም ጠያቂ ያልሆነ መንጋ የሆነ ትዉልድ ፤ተነጋግሮ ነገሮችን ለመፍታት እየቻለ ሀሳብ ስለሌለዉ ብቻ የሚሳደብ፤ ጩኸት ለመቀማት ሌላ አጀንዳ ሚፈጥር ትዉልድ ነዉ ያለዉ።ሩቅ ሳንሄድ በዚሁ በፌስቡክ በሚፃፈዉ አስተያየት ብቻ መመልከት በቂ ነዉ።»የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
ሚኪ ጀንበሬ የተባሉ አስተያየት ሰጪ «የአድዋ ድል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው።ከዛም አልፎ የመላው ጥቁር ህዝቦች ነው።ከዚህ ከወረደ ግን ባይከበርና ሳናስበው ብንውል ይሻላል።ብቻ ፈጣሪ ማስተዋል ይስጠን።»ሲሉ፤ «ምን ዋጋ አለው ።አድዋ በአሁኑ ወቅት ሰላም ርቋት ችግር ላይ ነች።»ያሉት ደግሞ ሀረግ ሀይለ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው።
ሌላው በዚህ ሳምንት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎችን ያነጋገረው ጉዳይ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግሬንስ ፓርቲ ኦፌኮ  በመጭው ሀገራዊ ምርጫ እንደማይሳተፍ ማስታወቁ ነው።ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ምርጫው ላይ  የማይሳተፈው በየአካባቢው ያሉ አባላቱ በመታሰራቸው እና ጽህፈት ቤቶቹም በመዘጋታቸው ፓርቲውን የሚወክሉ እጩ ተወዳዳሪዎችን ለማቅረብ በመቸገሩ ፣በአጠቃላይ የፖለቲካ ምህዳሩ ለምርጫ አመቺ ባለመሆኑ በማለት  አስታውቋል፡፡ ፓርቲው አያይዞም ከምርጫው በፊት  ለኢትዮጵያ ሠላምና መረጋጋት፣ ለነፃና ፍትሓዊ ምርጫ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለተሳካ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ ብሔራዊ መግባባትን የሚፈጥር ንግግር ይጀመር ብሏል።ይህንን የኦፌኮ መግለጫ ተከትሎ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች በአወንታዊም ይሁን በአሉታዊ መልኩ በርካታ አስተያየቶችን ሰጥተዋል።
ጃኒት ጃራ የተባሉ አስተያየት ሰጪ«የኦፌኮ አቋም ትክክል ነው።ሰው እየታሰረና  እየሞተ  ምርጫ ከማድረግ ይልቅ ለምርጫ የሚሆን ሰላማዊ ሁኔታ መፈጠር አለበት።»በማለት የፓርቲውን አቋም ደግፈዋል።
መሲ ወርቁ በበኩላቸው «ነገሩ ሁሉ አልጋ በአልጋ እንዲሆን ነው የሚጠብቁት።ፖለቲካ እኮ ትግል ነው።ታገሉና ለኦሮሞ ህዝብ ድምፅ ሁኑ አለዚያማ ምኑን የፖለቲካ ፓርቲ ሆናችሁ?»ብለዋል።
ሰው ለሰው የተባሉ አስተያየት ሰጪ «ሲጀመር ፓርቲው ራሱ ማንፌስቶ ያለው አይመስለኝም።» ሲሉ፤ዳባ በቀለበ በኩላቸው «ስለፓርቲው ለማውራት መጀመሪያ ማወቅ ይጠይቃል። በመሰለኝ ማውራት ነው ሀገሪቱን የጎዳት።»ሲሉ መልሰዋል።
«ድሮም የተዘጋጁ አይመስለኝም ።ምክንያት ፍለጋ ነው።ምርጫ ለምን ተራዘመ ስትሉ ቆይታችሁ አሁን ደግሞ አንሳተፍም ማለታችሁ ያሳዝናል።»ያሉት ደግሞ ምስጋናው ዋለ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው።
አየለ ታፋ ደግሞ«ህዝቡ አዝሎ ወደ ቤተ-መንግሥ እንዲስገባችሁ ነው የምትፈልጉት እንጅ፤ ጥያቄያቹ ሲታዩ  የምርጫ ፍላጎት ያላችሁ አይመልም።»የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
ሳሚያ በክሪ በበኩላቸው «እኩል የመጫወቻ ሜዳ በሌለበት በምርጫ ተሳትፎ አሯሯጭ ከመሆን በምርጫው አለመሳተፍ ትክክለኛ ውሳኔ ነው።»ብለዋል።
 ሀይማኖት ተፈራ የተባሉ አስተያየት ሰጪ«የኛ ፖለቲከኞች ይገርሙኛል ።ብሄራዊ መግባባት ተብሎ ሲሰባሰቡ፤ ስለ ብሄራዊ መፈራረስ ነው ሚያወራው። ግን ሁሌም ብሄራዊ መግባባት መፈጠር አለበት ይላሉ። እዴትና መቸ በምን በሉልኝ እስኪ ።»በማለት ፅፈዋል።
ግርማ ገመቹ ደግሞ «መግባባት ያቃታቸው ራሳቸዉ ፓርቲዎቹ ሆነው ሳላ ስለ ብሄራዊ መግባባት ያወራሉ።»ብለዋል።ኪያ ኪያ የተባሉ አስተያየት ሰጪ«ሀገሪቱ በአራቱም አቅጣጫ ተወጥራ በተያዘችበት ወቅት ኦፌኮ ከምርጫ ይልቅ ስለብሄራዊ መግባባት ማውራቱ ተገቢ ይመስለኛል።የሚሻለን እሱ ነው።»ሲሉ
ደጀኔ አድማሱ በበኩላቸው «አንዲት ሀገር ብሄራዊ መግባባት ስታደርግ ምንን አስመልክቶ ነው? ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ አገዛዝ ስትላቀቅ ብሄራዊ መግባባትን አድርጋለች። በበዳዮች እና በተበዳዮች መካከል የተደረገ ህርቀ ሰላም ወይም መግባባት ነበር።እኔን ያልገባኝ ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት መግባባት ነው የሚጠበቅባት ወይስ በአይነቱ ለየት ያለ ነው? ከደቡብ አፍሪካው ጋር የሚመሳሰል ከሆነ ደግሞ በዳይ እና ተበዳይ ህብረተሰብ ሊኖር ግድ ይላል!በኛ ሀገር ደግሞ ስርዓት እንጅ ህዝብ በድሎ አያውቅም።»በማለት አስተያየታቸውን ቋጭተዋል።
በሌላ በኩል በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ኦነግም በዚህ ምርጫ እንደማይሳተፍ ነገር ግን፤ ሰላማዊ ትግሉን እንደሚቀጥል  ገልጿል። በዚህ የኦነግ  ውሳኔ ላይም  በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ዘንድ  በርካታ አስተያየቶች ሲንሸራሸሩ ተመልክተናል።

Deutschland Äthiopiens Oromo federalist congress |  Merera Gudina
ምስል Eshete Bekele Tekele/DW
Äthiopien Büro des Oromo-Föderalistenkongresses
ምስል DW/S. Muchie
Äthiopien Adwa  125. Unabhängigkeitstag
ምስል Solomon Muchie/DW
Äthiopien Adwa  125. Unabhängigkeitstag
ምስል Alemnew Mekonnen/DW
Äthiopien Adwa  125. Unabhängigkeitstag
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ፀሀይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ