125 ዓመት ሜድ ኢን ጀርመኒይ | ኤኮኖሚ | DW | 24.08.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

125 ዓመት ሜድ ኢን ጀርመኒይ

የጀርመን ምርት መለያ «ሜድ ኢን ጀርመኒይ» ገሃድ ከሆነ እነሆ ነገ 125 ዓመት ይሆነዋል። ወደ አገር የሚገቡ የውጭ ምርቶችን ፉክክር ለመቋቋምና የራሷን አምራቾች ጥቅም ለማስጠበቅ ስትል ይህን መለያ የፈጠረችው ብሪታኒያ ነበረች።

የጀርመን ምርት መለያ «ሜድ ኢን ጀርመኒይ» ገሃድ ከሆነ እነሆ ነገ 125 ዓመት ይሆነዋል። ወደ አገር የሚገቡ የውጭ ምርቶችን ፉክክር ለመቋቋምና የራሷን አምራቾች ጥቅም ለማስጠበቅ ስትል ይህን መለያ የፈጠረችው ብሪታኒያ ነበረች። ይሁንና ዕርምጃው ብሪታኒያ እንዳሰበችው ሣይሆን ለጀርመን አምራቾች እንዲያውም ዘግይቶ የስኬት ምዕራፍ ከፋች ነው የሆነው። እንግዲህ በ19ኛው ክፍለ-ዘመን አጋማሽ የኢንዱስትሪው ዓብዮት ስር ከሰደደ በኋላ በቅድሚያ ብሪታኒያ የውጭ ፉክክርን ለመቋቋም ስትነሣ ነበር የምርት ዓይነቶችን መለያ ስያሜ የመስጠቱ ታሪክ ሀ ብሎ የጀመረው።

እርግጥ ብሪታኒያ የውጭ ምርቶች ከግዛቷ እንዳይገቡ ጨርሶ ማገዱን በሌሎች ሃገራት ሊወሰድ የሚችል ተመሳሳይ ዕርምጃን በመፍራት አለደፈረችም። ለማንኛውም በአገሪቱ የኤኮኖሚ ዘርፍ ግፊት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ነሐሴ 23 ቀን 1887 «ሜርቻንዳይዝ ማርክስ አክት» የተሰኘው የብሪታኒያ የንግድ መለያ ሕግ እንዲጸና ይደረጋል። በዚሁ መሠረት ከብሪታኒያ ጋር ለመነገድ የሚሻ ማንኛውም አገር ምርቱ ላይ የምንጩን መለያ ማስፈር ነበረበት።

«ይህ ደምብ ደግሞ በተለይም በጀርመን ላይ ያለመ ነበር። ምክንያቱም ጀርመኖች የብሪታኒያን ምርቶች ገልብጦ ወይም ኮርጆ በመስራት በመጠረጠራቸው ነው። ይህ መቀስና ቢላዋን የመሳሰሉ የዞሊንገን የስፌት ዕቃዎችን፤ እንዲሁም የሳክሶኒያን ማምረቻ መኪናዎች ይጠቀልል ነበር»

ይህን የሚሉት በቢለፌልድ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ-ሃብት ታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ቬርነር አበልስሃውዘር ናቸው። ተመራማሪው እንደሚያስረዱት በተለይ ሁለት ምክንያቶች ደምቡ እንዲሰፍን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። በአንድ በኩል የብሪታኒያን ፍጆተኛ ጥራት ያለው የሼፊልድ የስፌት ምርቶች ግልባጭ ከሆኑት ርካሽ ዕቃዎች ለማትረፍ ይታሰባል። በሌላ በኩል ደግሞ በጊዜው ልዕልና የነበረውን የጀርመን የምርት መኪና ስራ ለማቃለል መፈለጉ አልቀረም።

ግን ይህ የታሰበውን ውጤት አያስከትልም። «ሜድ ኢን ጀርመኒይ» መለያ ይልቁንም የኋላ ኋላ የተለየ የጥራት ምልክት እየሆነ ይሄዳል። እርግጥ እስከዚያው የተወሰነ ጊዜ ማለፉ አልቀረም። በ 1891 ዓመተ-ምሕረት የማድሪድ ውል አብዛኞቹ የንግድ ተካፋይ ሃገራት በምርቶች ላይ የተሳሰተ ምንጭ መስፈሩን ለመከላከል ከስምምነት ይደርሳሉ። ይህም እያንዳንዱ አገር የራሱን «ሜድ ኢን» መለያ በተግባር ላይ እንዲያውል የሚያደርግ ነበር።

በነገራችን ላይ የምርት ኩረጃው እንደዛሬው ሁሉ ቀደም ብሎም በሩቅ ምሥራቅ እሢያ አካባቢ የተለመደ እንደነበር ይነገራል። በዚሁ የተነሣም ለምሳሌ ጃፓን ከታላቋ ጎረቤቷ ከቻይና የሚገቡ ምርቶች ሁሉ «ሜድ ኢን ቻይና» የሚል መለያ እንዲሰፍርባቸው ግድ አድርጋ ነበር።

«እዚህም ምክንያቱ አንድ ዓይነት ነበር። ምርት ኮራጆችንና የባለቤትነት ፈቃድ ዝርፊን መፍራት! ነገር ግን ኩረጃው ሣይሆን የተፎካካሪው ወገን ተሽሎ መገኘት አመዛኝ እንደነበር ግልጽ ይሆናል»

ይህ ከጊዜው ሂደት ጋር ቢቀር በአውሮፓ ሃቁ ነበር። በ 1914 አንደኛው የዓለም ጦርነት ሲነሣ «ሜድ ኢን ጀርመኒይ» መለያም ይበልጥ ማተኮሪያ ይሆናል። የጀርመን ምርቶች በሪታኒያና አጋሮቿ በሚቆጣጠሯቸው ገበዮች ላይ እንዳይቀርቡ ይከለከላል። እናም የጀርመን ምርት መለያ በይበልጥ የድል ጎህ የቀደደው ቆይቶ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ነበር። ጀርመን ለምሳሌ ቬርነር አበልስሃውዘር እንደሚሉት እንደ አሜሪካ በገፍ ምርት ላይ ሣይሆን በልክ በተቀደደ ጥራት ባለው ምርት ላይ ነው ያተኮረችው።

«በልክ ቅድ» ሲባል የጀርመን ኤኮኖሚ በገፍ ምርት ሣይሆን በደምበኞች ፍላጎት ላይ የተመሠረተ የአሠራር ዘይቤን እንደሚከተል ለማመልከት ነው። መላ መሣሪያዎቹ፣ መዋቅራዊ ፕሮዤዎቹ፣ ጥበብና መኪናዎቹ በቀጥታ የደምበኞቹን ፍላጎት የሚከተሉ ናቸው። እንዲያው ዝም ብሎ በገፍ ማምረት አይደለም»

ታዲያ በዚህ ሁኔታ የሚቀርቡ ምርቶች ተወዳጅ እየሆኑ ሲሄዱ «ሜድ ኢን ጀርመኒይ» የሚለውን መለያ ለንግድ ማስታወቂያና ለገበያ ማስፋፊያ መሣሪያ አድርጎ የመጠቀሙ ዘመቻም ስኬታማ እየሆነ ይሄዳል። ይሄው የጀርመን ምርት መለያ እስካዛሬ ድረስ የተለየ ትርጉሙን ጠብቆና የሽያጭ ማግባቢያ ሆኖ ነው የሚገኘው። ይህ ደግሞ በተለይ ተሽከርካሪዎችን፣ የምርት መኪናዎችን፣ ኤሌክትሮ ቴክኒክንና የንጥረ-ነገር ኢንዱስትሪ ውጤቶችን የመሳሰሉትን በዓለምአቀፍ ደረጃ ቀደምት የሆኑ የጀርመን ምርቶችን የሚመለከት ነው።

የታሪክ ተመራማሪው እንደሚሉት በመሠረቱ የንግድ አበሮቹ ምርቱን በመገልበጣቸው ጉዳት የደረሰበት መስሎ የሚሰማው አገር የተሳሳተ ነው። እዚህ ጀርመን ውስጥ በቻይና ላይ ያለው አቋምም ይህን የመሰለ ሲሆን ሁኔታው ሊጤን ይገባዋል።

«የጀርመን የውጭ ንግድ ትርፍ የሚገኘው ምንጊዜም በዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ከሚገኙ ሃገራት ጋር በሚደረግ ንግድ ሆኖ አያውቅም። ይልቁንም 90 በመቶው ንግድ የሚካሄደው በተመሳሳይ የዕድገት ደረጃ ላይ ካሉ አቻ ሃገራት ጋር ነው። እና በዚሁ የተነሣም ቻይናውያን ወደኛ ደረጃ ከፍ እንዲሉ መሻት ይኖርብናል። እንዲህ ሲሆን ነው ከነርሱ ጋር በሚገባ መነገድ የምንችለው»

በአጠቃላይ የጀርመን ምርት መለያ «ሜድ ኢን ጀርመኒይ» ለአገሪቱ የኤኮኖሚ ዕድገት ወሣኝ አስተዋጸኦ አድርጓል። ግሎባል-ማርኬት የተሰኘው የገበያ ጥናት ኢንስቲቲዩት ባለፈው 2006 ባወጣው መረጃ ላይ የያንዳንዱን አገር መለያ ዋጋ አስፍሮ ነበር። በዚሁ መሠረት ያኔ የመለያው ዋጋ በ 4,582 ሚሊያርድ ዶላር ተተምኖ ነበር። ይህም በጊዜው ከጀርመን አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት 167 በመቶው መሆኑ ነው።

የምርት መለያዎች የአስተማማኝነት መመዘኛዎች ሲሆኑ ለበለጠ ቴክኒካዊ ዕርምጃ፣ ለኤኮኖሚ እርጋታና ለዕድገት አንቀሳቃሽም ናቸው። የጀርመን መለያ የሰፈረባቸው ምርቶች ዛሬ በዓለም ላይ ከፍተኛ ዋጋ ካላቸው ቀደምቶቹ ናቸው። ከፍተኛ ታዋቂነትና ተመራጭነት አላቸው። ለጀርመን ኢንዱስትሪዎች ስኬትና ለአገሪቱ ዓለምአቀፍ ዝናም ድርሻቸው ታላቅ ነው። «ሜድ ኢን ጀርመኒይ» በአሁኑ 21ኛ ክፍለ-ዘመንም የጀርመን ምርት ጥራት መለያና የተሃድሶ ሞተር እንደሆነ ይቀጥላል።

የምርት መለያ የኤኮኖሚ አጠቃቀም ደግሞ ወደፊትም መጠበቅ የሚኖርበት ጉዳይ ነው። በተለይም በዛሬው የኢንተርኔት ዘመን የአይምሮ ንብረትን መጠበቁ ፈታኝ ሆኖ ነው የሚገኘው። የሃሣብ ስርጭትንና የአዕምሮ ንብረትን ሚዛን ለመጠበቅ የሚያስችል ሕግ መረጋገጥ አለበት። ፍትሃዊና የተረጋጋ የንግድ ፉክክርን የሚያረጋግጥ ሁኔታን ማስፈኑ ወደፊትም የመንግሥት ተግባር ሆኖ ይቀጥላል።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 24.08.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15uI4
 • ቀን 24.08.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15uI4