1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

120ኛ ዓመት የያዘዉ የኢትዮጵያና ሩስያ ይፋዊ ወዳጅነት

ሐሙስ፣ የካቲት 15 2010

የኢትዮጵያና የሩስያ ይፋዊ ግንንኙነት የጀመረዉ ከአፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ነዉ። ከቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ጀምሮ በሩስያ ከ 20 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዉያን ትምህርታቸዉን ተከታትለዋል። በአሁኑ ሰዓት ወደ 130 የሚሆኑ ተማሪዎች አሉ። አዲስ አበባ ቡና ቤት ሞስኮ የሚገኝ አንዱ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብ ቤት ነዉ።

https://p.dw.com/p/2tB3r
Rußland, Addis Abeba Kaffee in Moskau
ምስል Ethiopian Embassy

«ወደ 275 ኢትዮጵያዉያን ሩስያ ዉስጥ ይኖራሉ»

ሩስያና ኢትዮጵያ ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመሩበትን 120ኛ ዓመትን ማክበር ጀምረዋል። የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ይፋዊ ባልሆነ መልኩ በ 16ኛዉ ክፍለ ዘመን መጀመሩን የታሪክ መዝገባት ያሳያሉ። ቢነገርም ይፋዊ ያልሆነዉ የዲፕሎማሲ ግንኙነት በአፄ ሚኒሊክ ዘመነ መንግሥት እና በሩስያዉ ንጉስ ኒኮላ ዘመን መሆኑን የታሪክ መዝገባት ያሳያሉ። የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ተጠናክሮ በቀጠለበት በቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ዘመን ከ 20 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዉያን የከፍተኛ ትምህርት እድልን አግኝተዋል። በዚh ዝግጅታችን ለረጅም ዘመናት ስለዘለቀዉ የኢትዮጵያ ሩስያ ግንኙነት እና በወቅታዊ የንግድ የፖለቲካ ብሎም ባህላዊ ግንኙነትን በተመለከተ በሩስያ ፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን ከአምባሳደር ግሩም አባይ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገን ቅንብር አሰናድተናል።

Äthiopische Botschaft in Moskau
ምስል Ethiopian Embassy

 “ይህንን ልጅ እንደወለድኩት ያህል እቆጥረዋለሁ። ወደ አውሮጳ ሄዶ እንዲማር ካሰብኩ ብዙ ጊዜ ነው። የታመነ ሰው እስታገኝ ስጠብቅ ቆየሁ። እርስዎን አምኖታለሁና አደራ ሰጥቼዎታለሁ። ደህና አድርገው ያስተምሩልኝ።…” ሲሉ ራስ መኮንን ሌዎንቴፍ ለተባለ የሩሲያ ተወላጅ ይነግሩና፤ ራስ መኮንን ተክለሃዋርያትን ስመውና ተሰናብተው ለሌዎንቴፍ ያስረክባሉ። ሌዎንቴፍም ተክለሃዋርያትን ጭኖ ባህር አሻግሮ ከአድማስ ወዲያ ወሰደው፤ ሩሲያ። የሕይወቴ ታሪክ ከተሰኘ መጽሐፍ፤ ፊታውራሪ ተክለሃዋርያት ተክለማርያም በ 1946 ዓ.ም የፃፉት የሕይወት ገጠመኝ የተቀዳ ጽሑፍ ነዉ። የመጀመርያዉን የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ያረቀቁት ፊታውራሪ ተክለሃዋርያት ተክለማርያም በሩስያ የከፍተኛ ትምህርታቸዉን የተከታተሉ ኢትዮጵያዊ ናቸዉ። ወጣቱ ተክለሃዋርያት አስራአንድ ዓመት በሩሲያ ኖሯል። ትምህርቱን የተከታተለውም አስር ዓመት ነበር። የኢትዮጵያ ሩስያ ይፋዊ ዲፕሎማስያዊ ግንኙነት በተለያዩ ዝግጅቶች እየታሰበ እና እየተከበረ መሆኑን በሩስያ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ግሩም አባይ ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልፀዋል።

Äthiopische Botschaft in Moskau
ምስል Ethiopian Embassy

ፊታውራሪ ተክለሃዋርያት በሩሲያ የተመረቁት አስቀድሞ በካዴትነት ማለት «በጦር መኮንንነት» ከምረቃ በዃላ ደግሞ በሩሲያ ብቸኛው የመድፈኛ አካዳሚ ከሆነው ‘የሚካኤል የመድፈኝነት ት/ቤት’ በዲፕሎማ ተመርቀዋል። በጦር መኮንንነና በመድፈኝነት ስላሳለፏቸው የትምህርት ዓመታትና ስላጋጠሟቸው ሁሉ  የሕይወቴ ታሪክ በተሰኘዉ መጽሐፍ ተጠቅሶአል። የኢትዮጵያ ሩስያ 120ኛ ዓመት ዴፕሎማስያዊ ግንኙነት በተመለከተ ሞስኮ ላይ ስለተካሄደዉ ዝግጅት በሳይንስ ረገድ ስብሰባ መካሄዱ የዜና ማሰራጫዎች ዘግበዋል። ይህን በተመለከተ አምባሳደር ግሩም አባይ፤ «ስብሰባዉ የሳይንሳዊ ኮንፈረንስ ተባለ እንጂ በዉስጡ የነበሩት ይዘቶች የተለያዩ ነጥቦችን የያዘ ነበር። አንዱ ለምሳሌ በሁለቱ ሃገራት መካከል የግንኙነት መሰረት የነበሩ ግዛቶች የቶቹ ነበሩ የሚለዉ ይገኝበታል። ይህ የጋራ እሴቶች ምንድን ናቸዉ የሚለዉን በተመለከተ ነዉ። ሌላዉ ሩስያ የኢትዮጵያን የሰዉ ኃይል ከማዳበር አኳያ በሽዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደተማሩ ይታወሳል፤ የሩስያ አስተዋፆ የተማረን የሰዉ አቅም ከማዳበር አኳያ ምን ያህል ተጫዉታለች የሚልጽሑፍ ነበር። በኢትዮጵያና በሶማልያ ጦርነት ወቅት የሩስያ አቋም ምን ነበር የሚልም ጽሑፍ ቀርቦአል። ከሩስያ ቤተ/ክርስትያን ሃይማኖት ነክ ነገሮች የቀረቡበት ጽሑፍም ነበር።»   

«የፊታችን መጋቢት ወር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የምታስተናግደዉ ሩስያ ዝግጅቷን በመጀመርዋ ለማግኘት የምንፈልጋቸዉን ሰዎች ምናልባትም ማግኘት ስለማንችል ባህላዊ ዝግጅቶቻችንን  በተመለከተ የሚዘጋጀዉ የተለያየ ትርዒት ከምርጫዉ በኋላ መረሐግብር እንደሚዘጋጅለት አምባሳደር ግሩም አባይ ተናግረዋል»

ፊታውራሪ ተክለሃዋርያት ተክለማርያም የጦር መኮንንነት ትምህታቸዉን ሲከታተሉ ያጋጠማቸዉ  የሕይወቴ ታሪክ በተሰኘዉ መጽሐፍ ላይ እንዲህ ይነበባል።  

“ለካዴቶች ብርቅ ሆንኩባቸው።ለጦር መኮንንኖቹ ማለታቸዉ ነዉ።  አንድ የኢትዮጵያ ተወላጅ በመካከላቸው መኖሩ ትልቅ ክብር መስሎ ታያቸው። በደስታ በፍቅር ተቀበሉኝ። በፈተና ላይ ብልጫ በማግኘቴ፤ በቋንቋቸው አሳምሬ በመናገሬ አከበሩኝ። ‘የንጉስ ልጅ ነው’ ተብሎ ተወርቶ ኖሮ ፕሪንስ ማለትም «ልኡል» እያሉ ይጠሩኝ ጀመር። ያንጊዜውኑ አወጅሁ። ‘ፕሪንስ አይደለሁም፤ የቄስ ልጅ ነኝ’ አልኳቸው። ስለዚህም አልናቁኝም፤ ይልቅ አከበሩኝ። እነሱ በአምስት ዓመቶች ውስጥ የተማሩትን፤ እኔን በሦስት ዓመቶች ውስጥ አጥንቼ ስለደረስኩባቸው። ስለዚህ አከበሩኝ። በካዴትነት ስማር አራት ዓመቶች አሳለፍኩ። በእድሜዬ ባጋጠመኝ እድሌ ሁሉ ይበልጥ ሆኖ የሚታየኝ፤ የማይዘነጋኝ፤ የሚያኮራኝም የካዴትነት ወቅት ነው። ስለምን ይሆን? ከአበባነት ወደ እንቡጥነት የተዘዋወርኩበት ጊዜ ስለሆነ ነው ይመስለኛል።…” ይላል ። በቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ትምህርታቸዉን የተከታተሉ ኢትዮጵያዉያን አብዛኞቹ ስለሩስያ ያላቸዉን ፍቅር ገልፀዉ አያበቁም። ኢትዮጵያ ሶቭየት ሕብረት ከመመስረቱ በፊት ጀምሮ  18ኛዉ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የወዳጅነት ግንኙነት እንደነበራት፤ እና ይፋዊ ግንኙነቱ ግን ከአፄ ሚኒሊክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እንደነበር አምባሳደር ግሩም አባይ ይገልፃሉ።

Äthiopische Botschaft in Moskau
ምስል Ethiopian Embassy

«ከቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ጀምሮ በሩስያ የተማሩ ኢትዮጵያዉያን የከፍተኛ ትምህርታቸዉን እንደተከታተሉ ባይታወቅም ከ 20 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዉያን ማለት ይቻላል። በአሁኑ ወቅት ተማሪዎች ማለት በመንግሥት ለመንግሥት ስምምነት የመጡ ተማሪዎች ቁጥር ወደ 130 የሚሆኑ አሉ። እዚህ ሩስያ ዉስጥ የሚኖረዉን ኢትዮጵያዊ  እና  ትዉልደ ኢትዮጵያዊ የምናየዉ ከሆነ በኛ ቆንስላ ኤንባሲ ባለን መረጃ መሰረት ባጠቃላይ ወደ 275 ኢትዮጵያዉያን ይገኛሉ። ሁለት ኢትዮጵያ ምግቤቶች ይገኛሉ» ሲሉ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያና በሩስያ መካከል ያለዉ የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ መሆን የገለፁት አምባሳደር ግሩም  በተለይ የአበባ ንግድ የጥራጥሪ ንግድ መኖሩን ገልፀዋል።

 የቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ከመፈራረሱ በፊት ኢትዮጵያዉያን በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የክፍተኛ ትምህርት ይከታተሉ ነበር። በቤላ ሩስያ በካዛኪስታን በዩክሬይን በሌሎችም አካባቢዎች ። ሃገሪቱ ከተፈረካከሰች በኋላም አሁንም በነዚህ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን አሉ። በተለይ በዩክሬይን በኦዴሳ በኪይቭ እንዲሁም በሌሎች የዩክሬይን ከተሞች አሁንም ኢትዮጵያዉያን ይኖራሉ እንዳዉም በዩክሬይን ችግር እንዳለባቸዉ በማኅበራዊ መገናኛ እየገለፁ ነዉ። አምባሳደር ግሩም በዩክሬይን ኢትዮጵያዉያን ችግር ገጥሞአቸዋል ስለተባዉ ጉዳይ ኤንባሲዉ ምንም አይነት መረጃ እንዳልደረሰዉ ገልፀዋል።

Äthiopische Botschaft in Moskau
ምስል Ethiopian Embassy

«አዲስ አበባ ካፊ»የተሰኘዉ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብ ቤት ፎቶግራፍ ልኮልናል። በቀጣይ በባህል መድረካችን ይዘን ልንቀርብ እንሞክራለን።  የቦልሸቪኩ አብዮት ፤ የደስታየቪስኪ ማክሲም ጎርኪ በተለይ በተለይ ደግሞ እንደ አሳ በባህር እንደሰዉ በምድር የተሰኙት ድርሰቶች በአማርኛ ተተርጉመዉ በቀዝቃዛዉ ጦርነት የሶቭየትኅብረት ኢትዮጵያ ወዳጅነት ዘመን ከማይጠፉ ትዝታዎች በጣም ጥቂቶቹ ናቸዉ።

Äthiopische Botschaft in Moskau
ምስል Ethiopian Embassy

ሩስያዉያን በጥንት ጊዜ ጥቁር ሕዝቦችን ኢፍዮፕ ነበር እንደሚሉ የታሪክ መዝገባት ያሳያሉ። ኢትዮጵያንም ሲጠርዋት ኢፍዮፕያ ይሉዋታል በቋንቋቸዉ። የእዉቁ ሩስያዊ ደራሲ የአሌክሳንደር ሰርጌቪች ፑሽኪን አያት አብርሃም ጋኒባልም ኢትዮጵያዊ ነዉ ይባላል።  አሁን አሁን ደግሞ በአፍሪቃ ኢትዮጵያን ጨምሮ ዘጠኝ የአፍሪቃ ሃገራት ታዋቂዉ የሩስያ ደራሲ ከአኛ ነዉ ይላሉ። ካሜሩን መካከለኛዉ አፍሪቃ በተለይ ደግሞ ኤርትራ። በዚህ ነጥብ ላይም አምባሳደር ግሩም ማብራርያ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ግሩም አባይ ለቃለምልልሱ ስለተባበሩን እያመሰገንን ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።  

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ፡