1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

10 ሚሊየን ዩሮ ለናሚቢያ ካሣ?

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 9 2012

በጀርመን እና በናሚቢያ መካከል የሁለትዮሽ ድርድርና ውይይት እየተካሄ ቢሆንም ከወር በፊት የናሚቢያ ፕሬዝደንት ሃገ ጌንጎብ ሀገራቸው በቅኝ ግዛት ዘመን ለተፈጸመባት የዘር ፍጅት በካሣነት 10 ሚሊየን ዩሮ ከጀርመን ሊሰጣት መታሰቡ ለናሚቢያ ስድብና ተቀባይነት የሌለው ነው ማለታቸው መደናገርን ፈጥሯል።

https://p.dw.com/p/3gzlP
Namibia Windhuk | Denkmal zur Erinnerung an den Völkermord an den Herero und Nama
ምስል picture-alliance/dpa/J. Bätz

«የጀርመንና የናሚቢያ ውዝግብ»

ጀርመን ከጎርጎሪዮሳዊው 1884  እስከ 1915 ዓ,ም ድረስ የቅኝ ግዛትዋ ከነበረችው ናሚቢያ ጋር የገባችበት የካሣ ውዝግብ ዛሬም አልተቋጨም። የታሪክ ሰነዶች እንደሚያሳዩት በወቅቱ የጀርመን ደቡብ ምዕራብ አፍሪቃ ተብላ ትጠራ በነበረችው ናሚቢያ ይካሄድ በነበረው የተቃውሞ አመፅ ቅኝ ገዥዋ ምዕራባዊ ሀገር በሰላም አልቆየችም። በተለይም በ1904 በዚሁ የዘመን ቀመር የሄሬሮ ጎሳ በዚያ በሰፈሩት ላይ ጥቃት ሰንዝሮ ከአንድ መቶ በላይ ጀርመኖች ከተገደሉ በኋላ ከ1904 እስከ 1908 ድረስ በሄሬሮና ናማ ጎሳዎች የዘር ፍጅት መፈጸሙ ተመዝግቧል። በወቅቱም በእስራት፣ በውኃ ጥም፣ በጥቃትና በርሸና እስከ 80,000 የሄሬሮና ናማ ጎሳ ሰዎች አልቀዋል። ከረዥም ዓመታት ውዝግብና ድርድር በኋላ የጀርመን መንግሥት በጎርጎሪዮሳዊው 2015ዓ,ም ነው ጀርመን ለ31 ዓመታት በቅኝ ግዛትነት በያዘቻት ናሚቢያ ዜጎች ላይ የዘር ፍጅት መፈጸሙን በይፋ ያመነው።  ጀርመን ምንም እንኳን የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ናሚቢያ ውስጥ ብታከናውንም ተገቢ የካሣ ክፍያ አልተፈጸምም፤ ለድርጊቱም በአደባባይ ይቅርታ ባለመጠየቋ እየተወቀሰች ነው። በጀርመን እና በናሚቢያ መካከል ይህንኑ አስመልክቶ የሁለትዮሽ ድርድርና ውይይት እየተካሄ ቢሆንም ከወር በፊት የናሚቢያ ፕሬዝደንት ሃገ ጌንጎብ ሀገራቸው በተጠቀሱት ዓመታት ለተፈጸመባት የዘር ፍጅት በካሣነት 10 ሚሊየን ዩሮ ከጀርመን ሊሰጣት መታሰቡ ለናሚቢያ ስድብና ተቀባይነት የሌለው ነው ማለታቸው መደናገርን ፈጥሯል። በእርግጥ ይህ ገንዘብ ለተፈጸመው የዘር ፍጅት ካሣ ይሆናልን በማለት የናሚቢያው ጋዜጣ ዘናሚቢያን የፕሬዝደንቱን ቃል አቀባይ ጠቅሶ የጻፈው ዘገባም የብዙዎችን ትኩረት ስቧል። የዶቼ ቬለ የአፍሪቃ ቋንቋዎች ክፍል ኃላፊ ክላውስ ሽቴከርም ይህን አስመልክቶ በጻፈው ሀተታ የተጠቀሰው የካሣ መጠን ይህ ከሆነ ጀርመን ጉዳዩን ከምር መያዟን የሚያጠያይቅ ነው ይላል።  

የናሚቢያ ፕሬዝደንት ሃገ ጌንጎብ
ምስል AFP/R. Bosch

«ግንኙነቱን መልሶ መልካም ማድረግ» በሚል የሚገለጸው የጀርመን አቀራረብ አሁን 116 ዓመት ለሞላው የ20ኛው ክፍለ ዘመን የዘር ማጥፋት የሚል ስያሜ ለተሰጠው ድርጊት 10 ሚሊየን ዩሮ በእርግጥም በጣም ትንሽና አሳፋሪ ነው። ድርድሩ በየመሃሉ እየተቋረጠም ቢሆን ለአምስት ዓመታት ዘልቋል። ምንም እንኳ የዘር ፍጅቱና  የሰለባዎቹም ቁጥር እንደየአቅራቢው የሚለያዩበት አጋጣሚ ቢኖርም ድርድሩም ሆነ በይፋ ስለተፈጸመው ይቅርታ የመጠየቁ ነገር ረዥም ጊዜ ፈጅቷልም ባይ ነው።

በጎርጎሪዮሳዊው 2015 ዓ,ም ነበር በጉዳዩ ላይ የጀርመን ወገን ተደራዳሪ የሆኑት የክርስቲያን ዴሞክራት ፓርቲ አባሉ ሩፐረሽት ፖሌንስ በሁለቱ ወገኖች መካከል በሁለት ዓመት ውስጥ ስምምነት ላይ ይደረሳል ያሉት። አሁን በጭምጭምታ የሚሰማው ደግሞ ድርድሩ በመጪው 2021 ሊቋጭ እንደሚችል ይጠቁማል። ፖሌንስ ከዶቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ የድርድሩን ሂደት በምሥጢር ለመጠበቅ በመወሰኑ የ10 ሚሊየን ዩሮ ካሣው ጉዳይ ከየት እንደመጣ አላውቅም ነው ያሉት። ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ የመረጃ ምንጮች በበኩላቸው ለዚሁ ጉዳይ የተያዘበው በጀት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መሆኑን ይናገራሉ። ይህ ደግሞ በወቅቱ ከባድ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ለጤና፣ ለትምህርትና ለመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች የሚውል ይሆናል። የይፋዊው ይቅርታ ጉዳይ በመጨረሻ በፌደራል ፕሬዝደንቱ በኩል ይመጣል ተብሎም ይጠበቃል። ናሚቢያውያንም በእርግጥ ይህን መቀበል ይኖርባቸዋል። እንዲያም ሆኖ ጀርመን ጉዳዩን ምን ያህል ከምር እንደያዘችውም የሚታየው በድርድሩ ውጤት ነው።  ናሚቢያ ከፍተኛውን የልማት ርዳታ ከሚያገኙ የአፍሪቃ ሃገራት ዋናዋ ናት። ከቅኝ ተገዢነት ነጻ ከወጣችበት ከጎርጎሪዮሳዊው 1990 አንስቶ በቢሊየን የሚቆጠር ዩሮ ወደሀገሪቱ ቢፈስም የምንም አልፈየደም።

Aufstand der Herero in Südwestafrika 1904
ምስል picture-alliance/dpa/F. Rohrmann

እናም አሁን ጀርመን የያዘችውን አቋም ግልፅ በማድረጉ በኩል የተሻለ መሥራት ይጠበቅባታል። ይህ ካልሆነ ፕሬዝደንት  ሃገ ጌንጎብ  ጉዳዩን ለፖለቲካ ጥቅማቸው ሊያውሉት ይችላሉ። እስካሁን በርሊን ጉዳዩን አስመልክቶ «ስህተትን ለማረም» የሚለውን ቃል ከመጠቀም ተቆጥባለች። ከዚህ ይልቅ «በጋራ ባሳለፍናቸው ጊዜያት የተፈጠሩ ጉዳቶችን ማዳን» የሚለውን አገላለፅ መጠቀሟ ናሚቢያውያንን ይበልጥ አበሳጭቷል። 10 ሚሊየን ዩሮውም ቢሆን የወደመ ቁሳቁስ ካሣ ተገርጎ የሚታይ በመሆኑ በመጨረሻ የገንዘቡ መጠን ከፍ እንደሚል ይጠበቃል። ናሚቢያ ውስጥ ያሉ የጀርመን ተደራዳሪዎችም ይህን በሚገባ ያውቃሉ።

ሸዋዬ ለገሠ/ክላውስ ሽቴከር

አዜብ ታደሰ